ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር ላጋጠማቸው ቤተሰቦች እንጸልይ አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 14/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ መግቢያ ላይ በአሁኑ ወቅት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በርካታ የሥራ ዘርፎች በመዘጋታቸው የተነሳ ለኢኮኖሚ ቀውስ ለተጋለጡ ቤሰቦች ጸሎት ማደረግ እንደ ሚገባ የገለጹ  ሲሆን እውነተኛ ጸሎት እምነት ፣ ጽናት እና ብርታት እንደ ሚጠይቅ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ሀ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደረጉት ስብከት እንደ ገለጹት “በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ችግር ላጋጠማቸው ሰዎች እንጸልይላቸው” በማለት መናገራቸው የተገለጸ ሲሆን የኢኮኖሚ ቀውስ በቤተሰቡ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፣ በመሆኑም የእዚህ ዓይነት ችግር ላጋጠማቸው ሰዎች እንፀልያለን ” ብለዋል።

ምልክቶችን ካላዩ በቀር…

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ከዮሐንስ 4፡43-54 ተወስዶ በተነበበው በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ በተጠቀሰው “ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደ ረገበት፣ በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ ዳግመኛ መጣ፤ በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ፤ ይህም ሰው ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እርሱ ሄደና በሞት አፋፍ ላይ የነበረውን ልጁን መጥቶ እንዲፈውስለት ለመነው” ኢየሱስም የሹሙን ልጅ ፈወሰ በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል መሰረቱን ያደረገ ስብከት እንደ ነበረ ይተገለጸ ሲሆን የመንግሥት ሹም የነበረው ሰው ጌታ በጥቂቱ ቢሆንም እንደ ገሰጸው የገለጹ ሲሆን የመንግሥት ሹም የነበረው ሰው ዝም ከማለት ይልቅ 'ጌታ ሆይ ፣ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህን ድረስለት” ብሎ እንደ ተማጸነው ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ከዛም ልጁ በሕይወት እንደ ሚኖር ከኢየሱስ ማረጋገጫ እንደ ተሰጠው ገልጸዋል።

እምነት

“እውነተኛ የሆነ ጸሎት” ለማድረግ የሚያስፍልገው የመጀመሪያ መስፈርት  እምነት ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ብዙ ጊዜ ጸሎታችን የሚወጣው ከአፋችን ብቻ ነው፣ ነገር ግን የእዚህ ዓይነቱ ጸሎት ከልብ የሚመነጭ አይደለም ፣ ወይም ደካማ በሆነ እምነት የሚደረግ ጸሎት ነው” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ተናገሩት በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰውና “ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ አድሮበት ድዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም” (ሉቃስ 9፡17-18) የሚለውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል ያስታወሱ ሲሆን የልጁ አባት፣ “አምናለሁ፤ አለማመኔን ርዳው!” በማለት ከጮኸ በኋላ ርኩስ መንፈስ ያለበትን ልጅ ኢየሱስ እንደ ፈወሰ ገልጾ እምነት ላላቸው ሰዎች በሙሉ የጠየቁት ነገር እንደ ሚሳከ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። ይህንን በተመለከተ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . .

“እምነት እና ጸሎት; በእምነት መጸለይ ያስፈልጋል።  እኔ ጸሎት የማደርገው በእምነት ነው ወይስ እንዲያም ጸሎት የማደረግ ባህሪ ስላለኝ ብቻ ነው? ጸሎት በምናደርግበት ወቅት ማስተዋል ይኖርብናል፣ ከጌታ ጋር እየተነጋገርን መሆኑን እና እርሱ ችግሮችን መፍታት እንደሚችል በመገንዘብ በንቃት መጸለይ ይኖርብናል።

ጽናት

እውነተኛ ጸሎት ለማድረግ ከሚጠቅሙን መስፈርቶች መካከል በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ጽናት መሆኑን በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ራሱ “ተግታችሁ ጸልዩ” ብሎ እንዳስተማረ አክለው ገልጸዋል። ይህን በተመለከተ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . .

“አንዳንድ ሰዎች በጸሎት ይተጋሉ ነገር ግን የጠየቁት ጸጋ በወቅቱ ላይመጣ ይችላል። በአዚህ ወቅት ጸሎት ማደራጋቸውን ያቋርጣሉ። እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች ጽናት የላቸውም፣ ምክንያቱም የጠየቁትን ነገር እጅግ በጣም አይፈልጉትም ይሆናል ወይም እምነት ስለሌላቸው ይሆናል”።

ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት ኢየሱስ ጽናትን በተመለከተ ካሳተማራቸው ነገሮች ውስጥ ምሳሌዎችን መጥቀሳቸው የተገለጸ ሲሆን -ጎረቤቱን በእኩለ ሌሊት ከእንቅልፉ ቀስቅሶ እንጀራ እንዲያውሰው የጠየቀውን ሰው ምሳሌ እና እንዲሁም ፍትሐዊ ባልሆነው ዳኛ ፊት በመመላለስ ፍትህ ይሰጣት ዘንድ ስትጠይቅ የነበረችውን መበለት ምሳሌ ቅዱስነታቸው አንስተዋል። ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ  የሚከተለውን ብለዋል . . .

“እምነት እና ጽናት አብረው ይሄዳሉ ምክንያቱም እምነት ካለህ ጌታ የጠየከውን እንደሚሰጥህ እርግጠኛ ትሆናለህ።  ጌታ እንዲትጠብቅ ካደረገ እንኳን እንደ ገና ደጋግመህ ታንኳኳለህ። በመጨረሻ ጌታ ፀጋውን ይሰጣል።

ጌታ እንድንጠብቀው የሚያደርገን ለገዛ ጥቅማችን ሲል እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው ጌታ የእያንዳዳችንን ጸሎት በቁምነገር እንደ ሚመለከት ገልጸዋል።

ብርታት

እግዚአብሔር በርትተን እንድንጸልይ ይፈልጋል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ ደሞ ጽሎት ለማደረግ የሚረዳን ሦስተኛው መስፈርት ነው ብለዋል ፡፡ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . .

‘ለመጸለይ ብርታት ያሰፈልጋል ወይ?’ ብሎ አንድ ሰው ሊጠይቅ ይችል ይሆናል። በጌታ ፊት በብርታት መቆየት፤ አዎን አስፈላጊ ነው። መናፍቅ መሆን አልፈለግም ግን ይብዛም ይነስም ጌታን የማስፈራራት ያህል ነው። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማጥፋት በፈለገ ጊዜ ሙሴ ያሳየውን ብርታት እንሳስታውስ፣ እግዚአብሔር የሰዶምን ከተማ ሊያጠፋ በፈለገበት ወቅት አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር በብርታት ያደርገውን ንግግር እናስታውሳለን። ሰላሳ ቅዱስና ቢኖሩስ? 20 ቢኖሩስ? እያለ በብርታት ያቀረበውን መማጸኛ እናስታውስ። የእዚህ ዓይነቱ ብርታት ለሐዋርያዊ ተግባራት ብቻ የሚውል ሳይሆን ለጸሎትም ይህ ብርታት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።

እምነት ፣ ጽናት እና ብርታት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት “በእምነት፣ በጽናት እና በብርታት” በእነዚህ ቀናት ውስጥ የበለጠ መጸለይ ያስፈልጋል ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን አሁን የተጋረጠብንን ፈተና በተገቢው ሁኔታ ማለፍ ይቻል ዘንድ በእምነት፣ በጽናት እና በብርታት ጸሎታችንን ማደረግ መቀጠል ይኖርብናል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
23 March 2020, 17:08