ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ክርስቲያን መለያው ጠላትን መውደድ እና ይቅርታን ማድረግ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ የካቲት 15/2012 ዓ. ም. የደቡብ ጣሊያን ከተማ ወደ ሆነች ባሪ ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ባሪ ከተማ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ከአካባቢው ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳትና መነኮሳን፣ እንዲሁም በርካታ ምዕመናን ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት አሳርገዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ በዘመናት ታሪክ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ያመጣው ከፍተኛ ለውጥ፣ ጠላትን ማፍቀር እና ይቅር ማለት እንዳለብን፣ ለተቸገሩት የቸርነት ተግባራትን ማከናወን፣ ጠላትን ማፍቀር እና ይቅር ማለት እንዳለብን መጠየቁን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በደቡብ ጣሊያን፣ ባሪ ከተማ ውስጥ ከሚገኝ የቅዱስ ኒኮላ ባዚሊካ ተነስተው፣ በከተማዋ መካከል የሚገኘውን የንጉሥ ቪቶሪዮ ዳግማዊ ጎዳናን አቋርጠው፣ በርካታ ቁጥር ባለው የከተማዋ ምዕመናን በመታጀብ የመሰዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ወደሚፈጸምበት ሥፍራ ደርሰዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ከይተገኙ በርካታ የጣሊያን መንግሥት ከፍተኛ ባለ ስልጣናት መካከል የአገሪቱ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሴርጆ ማታሬላ መገኘታቸው ታውቋል።

ከማቴ. 5:38-48 ላይ ተወስዶ በተነበበው በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን፣ ጠላትን ማፍቀር እና ይቅርታንም ማድረግ እንዳለባቸው ማስተማሩን አስታውሰዋል። በስብከታቸው መካከል በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰውን የሙሴን ሕግ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ዐይን ስለ ዐይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ የሚለው የሙሴ ሕግ በራሱ፣ በጠላት ላይ ሊወሰድ የሚችለውን ከፍተኛ የአጸፋ ምላሽ የሚገድብ መሆኑን አስረድተዋል። ኢየሱስ ግን ሌላ ሕግ ማስተዋወቁን የገለጹት ቅዱስነታቸው እርሱም ክፉዎችን ላለመቃወምና ዓመፅን አለማስቀረት መሆኑን አስረድተዋል። ይህንንም ሲያስረዱ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት፣ ምንም እንኳን ክፉዎችም በመጨረሻ ክፋታቸውን የሚያቆሙ ቢሆንም፣ ኢየሱስ እነዚህን ክፉ አድራጊዎችንም እንድናፈቅራቸው የሚያዘን ዋናው ምክንያት፣ እግዚአብሔር አባታችን ሁላችንንም ዘወትር እንደሚወደን፣ ለክፉዎችም ሆነ ለደጎች ፀሐዩን የሚያበራልን እንዲሁም ለደጋግ ሰዎች እና ለኃጢአተኞች ዝናቡን ስለሚያዘንብ ነው ብለዋል።

ኢየሱስ በነጻ እንዳፈቀረ እኛም እርስ በእርስ እንፈቃቀር፣

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በመስቀል ላይ ሰቅለውት፣ በሚስማር ወግተውት እንዲሞት ያደረጉትን እና የፈረዱበትን፣ እጁን ዘርግቶ ይቅር በማለቱ፣ ክርስቲያን የሆንን ሁላችን የምንመራበት ቀዳሚ ምሳሌ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ከፈለግን፣ ክርስቲያኖች ነን ማለት ከፈልግን፣ መከተል ያለብን ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየን የይቅርታ እና የምሕረት መንገድ ነው ብለዋል። እግዚአብሔር የወደደን፣ ሌሎችንም ለመውደድ የተጠራን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን ያገኘን፣ እኛም ለሌችን ይቅር እንድንል የተጠራን፣ በእርሱ እውነተኛ ፍቅር የተያዝን በመሆናችን ሌሎች እስኪያፈቅሩን ድረስ ሳንጠብቅ እንድናፈቅር ተጠርተናል ብለው፣ እግዚአብሔር በነጻ ያዳነን በመሆናችን ለምናደርገው መልካም ነገር ውለታን መጠበቅ የለብንም ብለዋል።

ጠላትን መውደድ የክርስቲያን መለያ ነው፣

በክርስትና ሕይወት መካከል ፈተና ውስጥ ሊከተን የሚችል ነገር ቢኖር “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ ለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ የሚል የኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሲናገር ግልጽ እና በማያሻማ ቋንቋ መናገሩን አስታውሰው፣ ጠላትን መውደድ ለክርስቲያን የተሰጠ አዲስ ትዕዛዝ ነው ብለው፣ የክርስቲያን መለያው ጠላትን መውደድ እና ለሚያሳድደውም መጸለይ ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ገደብ የለውም ብለው እርሱም ይህን ፍቅሩን ሳንሰስት ለሌሎች እንድናሳይ ይጠይቀናል ብለዋል። ስንት ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕዛዝ ጥሰናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር ትዕዛዝ የቅዱስ ወንጌል መልዕክት መሠረት ነው ብለዋል። ለሌሎች ማሳየት ስለሚገባን ፍቅር ምንም ጥያቄ ሊኖረን አይገባም ብለው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱን የፍቅር መንገድ በመከተል ቸርነትንም እንገልጻለን ብለዋል።

የክርስትያን መለያው ፍቅር ነው ብለዋል።

እያንዳንዳችን ልባችንን በመመልከት፣ ጠላቶቻችንን መውደድ እንደሚያስፈልግ የጠየቁን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለሚያሳድዱን ለሚያስጨንቁን ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ገልጠን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል። እግዚአብሔርን በእውነተኛ ልብ ማምለክ የጥላቻን መንገድ መቃወማችንን ያመለክታል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጥላቻ ባሕል መቃወም ወይም ማስወገድ የምንችለው የቅሬታን ባሕል ስናስወግድ ነው ብለዋል። ከፈጣሪ ዘንድ ለምንጠይቀው ጥያቄ መልስ ሳናገኝ ስንቀር፣ ነገሮች በምንፈልገው መንገድ ሳይሄዱ ሲቀሩ፣ ስንት ጊዜ እናማርራለን ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ነገሮች በምንመኘው መንገድ አለመሄዳቸውን፣ ሰዎች እንደሚጠሉን እና እንደሚያሰቃዩን፣ ሌሎች በርካታ ነገሮች እኛ በማንፈልገው መንገድ በእኛ ላይ መከናወናቸውን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገባ ያውቀዋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ማድረግ ያለብን መጸለይ እና ፍቅራችንን መግለጽ እንዳለብን ኢየሱስ ያስተምረናል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሙሴ ሕግ ላይ ያመጣው ለውጥም የጠላንን ከመጥላት ይልቅ የጠላንን መውደድ፣ አይበቃኝም ብሎ ከማማረር ባሕል ይልቅ ስጦታን የመለገስ ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስረድተው የኢየሱስ ክርስቶስ ከሆንን ብቸኛው የጉዞ መንገዳችንም ኢየሱስ ክርስቶስ የተጓዘበት መንገድ ነው ብለዋል።

ፍቅር እና ይቅር ባይነት በእግዚአብሔር ፊት አሸናፊነትን ያስገኛሉ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስብከታቸውን በመቀጠል እንዳስረዱት፣ አንድ ሰው ሊያቀርብ የሚችላቸውን ተቃውሞዎች በማስተወስ እንደገለጹት ፣ ሃሳብ እና የሕይወት አካሄድ የተለያዩ ነገሮች ናቸው ብለው፣ “በዚህች ምድር ላይ የዋህነትን እና ፍቅርን የማበዛ ከሆነ ትርፍ ማግኘት አልችልም” የሚል አስተሳሰብ አለ ብለው፣ ይህ አስተሳሰብ በምድራዊ ሕይወት ትርፍ የሌለው ቢሆንም፣  ሌሎችን ማፍቀር እና ይቅር ባይነት በእግዚአብሔር ፊት አሸናፊነትን ያገኛሉ ብለዋል። በማከልም ቅዱስ ጳውሎስ “የዚህ ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነው” ማለቱንም አስታውሰዋል። “ሌሎችን መውደድ እና ይቅርታን ማድረግ የአሸናፊዎችን ሕይወት መኖር ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በጌቴሴማኒ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለጴጥሮስ “ሰይፍህን ወደ ኪሱ ውስጥ መልስ” በማለት የተናገረውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ዛሬ በምንኖርበት ዓለም፣ ግድ የለሽነት እና ኢፍትሃዊነት በነገሠበት፣ የተስፋ ጩኸት በሚሰማበት በዛሬው ዓለማችን ውስጥ አንድ ክርስቲያን፣ እንደነዚያ መጀመሪያ ሰይፋቸውን እንዳነሱ፣ ከዚያ በኋላ እንደሸሹ ደቀመዛሙርት መሆን አይቻልም ብለዋል። ሰይፍ ማንሳት ወይም ከሚደርስብን መከራ ለማምለጥ የችግሩ መፍትሄ ሊሆን አይችልም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ መፍትሄው ኢየሱስ ክርስቶስ ባዘጋጀው የፍቅር መንገድ እስከ መጨረሻ መጓዝ ነው ብለዋል።

የፍቅርን እና የጥንካሬን ጸጋ ከእግዚአብሔር እንለምን፣

ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጠይቀን ወይም የሚያዘን ከአቅማችን በላይ ሆኖ ቢገኝም ግማሹን እንኳን ማከናወን የሚያስችለንን ጸጋ ከእግዚአብሔር እንጠይቅ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እግዚአብሔር አምላካችንን የምንለምነው ፍቅርን እና ይቅርታን እንዲያስተምረን ነው ብለዋል። ሌሎች ሰዎችን እንደ እንቅፋት እና ችግር ፈጣሪዎች አድርገን ከመቁጠር ይልቅ  እንደ ወንድም እና እህት አድርገን የምናይበትን ጸጋ እንዲሰጠን መለመን ያስፈልጋል ብለዋል። ብዙን ጊዜ ለግላችን የሚሆኑ ሌሎች ነገሮችን በጸሎት ስንጠይቅ እንደምንገኝ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ፍቅሩን እንዲያስተምረን፣ በወንጌል ቃሉ እንድንመራ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆን እንድንችል ብለን የምናቀርበው ጸሎት ጥቂት ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ የካቲት 15/2012 ዓ. ም. የደቡብ ጣሊያን ከተማ ወደ ሆነች ባሪ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዕለት ያሰሙትን ስብከት ከማጠቃለላቸው አስቀድመው እንደተናገሩት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጓዘበት የፍቅር ጉዞ መስዋዕትነትን የሚያስከፍል ቢሆንም ራሳችንን በዓለማዊ አስተሳሰብ ሳናስገዛ ፣ የኢየሱስን ስቃይ በመጋራት፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመሆን፣ ዓለማችን የሰው ልጅ በሙሉ በፍቅር የሚኖርባት ማድረግ እንችላለን ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
24 February 2020, 16:26