ቅዱስነታቸው ከምዕመናኑ ጋር ሆነው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል ቅዱስነታቸው ከምዕመናኑ ጋር ሆነው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል 

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሶርያን ጦርነት የሚያስቆም የጋራ ውይይት እንዲኖር ያስፈልጋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ በተነበቡት ቅዱሳት መጽሐፍት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ካቀረቡ በኋላ ከምዕመናኑ ጋር ሆነው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል። ቀጥለውም በሥፍራው ለተገኙት፣ ከሮም ከተማ፣ በጣሊያን ከተለያዩ ቁምስናዎች እንዲሁም ከተለያዩ አገሮች ለመጡት ምዕምናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ሀገር ጎብኚዎች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ የሰላምታ ንግግራቸው ቅዳሜ ጥር 30/2012 ዓ. ም. ታስቦ የዋለውን ዓለም አቀፍ ጸረ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የጸሎት ቀንን አስታውሰው በዕለቱ በተደረገው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሰለባ ለሆኑት ባልደረባ ወደ ሆነች ቅድስት ባኪታ ጸሎት መቅረቡን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምዕመናን በያሉበት ሆነው በጸሎታቸው እንዲተባበሯቸው የሚያግዝ ወርሃዊ የጸሎት ሃሳባቸውን በቪዲዮ መልዕክታቸው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። በዚህ የጸሎት ሃሳባቸው፣ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እጅ ወድቀው በስቃይ ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው፣ ጩሄታቸውንም መላው የዓለም ሕዝብ እንዲያዳምጥ አደራ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በዓለማችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኛ ወንዶች እና ሴቶች በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተጠውቁ እና በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰው ይህን የማኅበረሰባችን አስከፊ ገጽታ በጽኑ መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።   

“ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል እውነተኛ የዓለማችን መቅሰፍት ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከዚህ አደጋ ማምለጥ ያልቻሉ በርካታ አቅመ ደካሞችን ነጻ የማውጣት ተግባር የተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የማሕበራት እና የትምህርት ተቋማትንም የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል። ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች የተራቀቁ እና ዘመናዊ የመገናኛ መንገዶች እንደሚጠቀሙ እና በዚህም ብዙዎችን ማታለል እንደቻሉ ጥናቶች አረጋግጠዋል ብለዋል።   

እነዚህን ዘመናዊ የመገናኛ መሣሪያዎችን በአግባቡ እና በትክክለኛው መንገድ መጠቀም እንዲቻል በቂ ትምህርት ሊሰጥበት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመገናኛ መስመሮችን የሚፈቅዱም ቢሆኑ ሃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ትናንት ባስተላለፉት መልዕክትም በሶርያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው ከባድ ጦርነት ምክንያት የብዙዎች ሕይወት አደጋ ውስጥ መውደቁን የተለያዩ ዜና ማሰራጫዎች ይናገራሉ ብለው፣ በተለይም እናቶች እና ሕጻናት በስቃይ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ይህ አሰቃቂ ጦርነት ያበቃ ዘንድ፣ የጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት በሙሉ ወደ ጋራ ውይይት ተመልሰው እርቅን እና ሰላምን እንዲያወርዱ በማለት ያቀረቡትን ጥሪ በመድገም፣ የሰላማዊ ሰዎች ህይወት በከንቱ እንዳይጠፋ እና የሰብዓዊ መብት ሕጎችም እንዲከበሩ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበው በጦርነት እና በአመጽ ውስጥ የሚገኘውን የሶርያ ሕዝብ በጸሎት እናስታውስ በማለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ሆነው ቅዱስነታቸው የጋራ ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ አድርሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም በጣሊያን ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የልዩ ልዩ መንፈሳዊ ባሕበራት አባላት ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ከጣሊያን ውጭ ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ሰላምታቸውን አቅርበው፣ መልካም ዕለተ ሰንበትን ከተመኙላቸው በኋላ በአደባባዩ የተገኙት በሙሉ ሳይዘነጉ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ በማለት የዕለቱን ሐዋርያዊ አስተምህሮአቸውን አጠቃልለዋል። 

10 February 2020, 18:14