ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የብጽዕና መንገዶች፣ የሰው ልጆች በሙሉ እንዲጓዙባቸው የተዘጋጁ ናቸው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በዛሬው ዕለት ማለትም በጥር 20/2012 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፣ በማቴ. 5: 1-11 ላይ በተጻፈው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማትኮር አስተምሮአቸውን አቅርበዋል። ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥር 20/2012 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን ትርጉመን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአችንን በማቴ. 5:1-11 ላይ በተጻፈው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስተንተን እንጀምራለን። ይህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ኢየሱስ ክርቶስ በተራራ ላይ ያቀረበውን ስብከት በማቅረብ፣ ለበርካታ ክርስቲያኖች እና ክርስቲያን ላልሆኑትም ጭምር የሕይወታቸው ብርሃን ሆኖ እናገኛለን። በዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስብከት ሳይማረኩ መቅረት አስቸጋሪ ነው። ከዚህም ጋር በተያያዘ ይህን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ወይም ስብከት መልዕክት በሚገባ ለመረዳት ያለን ፍላጎትም ከፍተኛ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን የምድራችን ብጹዓን ሕይወት ታሪክ የማንነታችን ወይም የክርስቲያንነታቸን ዋና መለያ ናቸው። ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት፣ የእርሱን የሕይወት አካሄድ ስለሚገልጹ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የተናገራቸውን ቃላት፣ በሚቀጥሉት የጠቅላላ የትምርተ ክርስቶስ አስተምሮ፣ አንድ በአንድ ወስደን ለመመልከት እንሞክራለን። በመጀመሪያ ፣ ይህ መልእክት የቀረበበትን ወይም ለሕዝቡ የተነገረበትን መንገድ እና ዘዴ ማጤኑ አስፈላጊ ነው። በርካታ ሕዝብ እርሱን እንደሚከተሉት በተመለከት ጊዜ በገሊላ ሐይቅ ዙሪያ ባለው ከፍታ ቦታ ላይ ወጣ ፣ በዚያም ተቀመጠ ፣ እርሱን የሚከተሉት ደቀ መዛሙርትን ማስተማር ጀመረ። ኢየሱስ በሥፍራው ለተገኙት ያቀረበው ትምህርት ደቀ መዛሙርቱን ይመልከት እንጂ ከደቀ መዛሙርቱ በተጨማሪ ትምህርቱን የሚካፈሉ ሌሎች በርካታ የዓለማችን ሰዎች መኖራቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሥፍራው ለተገኙት በርካታ ሰዎች ያስተማረው ትምህርት ወይም ያስተላለፈው መልዕክት ለሰው ልጅ በሙሉ የቀረበ መልዕክት  ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥፍራው ለተገኙት በሙሉ ትምህርቱን ያቀረበበት ከፍታ ሥፍራ፣ እግዚአብሔር አስሩን ትዕዛዛት ለሙሴ የሰጠበትን የሲና ተራራ ያስታውሰናል። ኢየሱስ በገሊላ ሐይቅ ዙሪያ ባለው ከፍታ ቦታ ላይ ያስተማረው ትምህርት አንድ አዲስ ሕግ ይዞ ቀርቧል፤ ይህ አዲስ ሕግ ደሃ መሆንን፣ የዋህ፣ ርህሩህ እና ይቅር ባዮች መሆንን ያስታውሰናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማራቸው አዲሶቹ ትእዛዛት የኑሮ ደንቦች በማስተማር ረገድ አስፈላጊዎች ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን አዳዲስ ትዕዛዛት ሲያስተዋውቅ ግዴታን በማከል በሰዎች ሕይወት ውስጥ ጫናን ለመፍጥረ ሳይሆን ነገር ግን ትክክለኛ ደስታ የሚገኝበትን የራሱን መንገድ፣ “ብጽዓን ናቸው” በማለት ስምንት ጊዜ ደጋግሞ በመንገር ለማስገንዘብ ነው።

እያንዳንዱ የብጽዕና መንገድ ሦስት ክፍሎች አሉት፤ በመጀመሪያው ክፍል “ብጹዓን ናቸው” በማለት ብጹዓን የሚገኙበትን ሕይወት ያብራራል፣ በመንፈስ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ፣ ስለ ጽድቅ ስደት እና መከራን የሚቀበሉ፣ ጽድቅን የሚራቡ እና የሚጠሙ፣ ፍትህም የሚጠማቸው፣ ወ. ዘ. ተ. በማለት ይተነትናቸዋል። ቀጥሎም በሁለተኛው ክፍል፣ ብጹዕ የሆኑበት ምክንያት ይገልጻል። ስምንቱም የብጽዕና መንገዶች በዚህ ዓይነት መንገድ ተዘርዝረው እናገኛቸዋለን። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠንን ይህን ሕግ በትክክል በአእምሮአችን እና በልባችን ውስጥ መያዝ እና ማስታወስ መልካም ነው።   

አንድ ነገር ልብ ማለት ይኖርብናል። ብጹዓን የመሆን ዋና ምክንያት አሁን በምንገኝበት ወይም በምንኖርበት ሁኔታ የምናገኘውን ሽልማት በማስታወስ ሳይሆን፣ ነገር ግን መንግሥተ ሰማይን ለመውረስ፣ መጽናናትን ለማግኘት፣ ምድርንም ለመውረስ ሚያስችለንን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘው ስጦታ መኖሩን ለማስታወስ ነው።

በሦስተኛው ክፍል፣ ደስተኞች የምንሆንበትን ምክንያት ያብራራል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ የወደፊት ሕይወትን በማስመልከት ይናገራል፤ ይህንንም መጽናናት ስለሚሰጣቸው፣ ምድርንም ስለሚወርሱ፣ ጽድቅን አግኝተው ስለሚረኩ፣ ምህረትን ስለሚያገኙ፣ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ፣ በማለት ያብራራል።

ስለ ብጽዕና ይህን ያህል ከተናገርን፣ ለመሆኑ ብጽዕና ምንድር ነው? የቃሉስ ትርጉም ምን ማለት ነው? ለምንድነው ስምንት ጊዜ “ብጹዓን ናቸው” በማለት የሚጀምረው? መሠረታዊ ትርጉሙ፣ የአንድ ሰው የተመቻቸ ሕይወት ምን እንደሚመስል የሚገልጽ ሳይሆን አንድ ሰው በእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ በመታገዝ የሚኖረው ሕይወት፣ የሚጓዝበት የእግዚአብሔር መንገድ ምን እንደሚመስል ይገልጻል። የትዕግስት ሕይወት፣ የድህነት ሕይወት፣ ሌሎችን ለማገልገል ሕይወትን አሳልፎ መስጠት የሚያስገኘውን የደስታ ሕይወት እና የብጽዕና ሕይወት ምን እንደሚመስል ያስረዳል።

እግዚአብሔር እራሱን ለእኛ ለመስጠት ብዙውን ጊዜ የማናስባቸውን እና የማንጠብቃቸው መንገዶችን ይመርጣል። የእኛን ውስንነት እና ደካማነት ይመርጣል፣ ሐዘናችንን እና ሽንፈታችንን ይመለከታል። የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ወንድሞቻችን እንደሚሉት የትንሳኤው ደስታ የኢየሱስን ሕያው የስቃይ ቁስሎችን እንድንመለከታቸው ያድርግ እንጂ የሞት ስልጣን በድል የተወገደበትን የእግዚአብሔር ኃይል የምናይበት መሆኑን ያስታውሰናል። የብጽዕና መንገዶች ወደ እውነተኛ ደስታ የሚመሩ ናቸው። በዛሬው ዕለት ከማቴ. በ5፡ 1-11 ወስደን ያነበብነውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል ደግመን ብናነበው፣ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በሳምንታት ውስጥ ደጋግመን ብናነበው፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያዘጋጀልንን የደስታ መንገድ የቱ እንደሆነ በትክክል እንድናውቅ ያግዘናል”።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
29 January 2020, 17:19