ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አምባሳደሮችን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አምባሳደሮችን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጋራ ውይይት እና መቻቻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ እንዲሆን ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ታኅሳስ 30/2012 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችን በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ጊዜ ዓለማችንን ያጋጠሙ የተለያዩ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ማለፍ እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ታውቋል። በዓለማችን ውስጥ ተረስተው የቀሩ ማሕበራዊ ችግሮች፣ ግጭቶች እና ጦርነቶች በርካታ መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ከእነዚህም መካከል በሕጻናት እና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ በአውሮፓ ማሕበረሰብ መካከል እየተዳከመ የመጣው የአንድነት እና የመተጋገዝ መንፈስ ከችግሮቹ መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣  በቅድስት መንበር ለተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዲሱን የጎርጎሮሳዊያን 2020 ዓ. ም. አስመልክተው በቅድስት መንበር ለተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ባስተላለፉት መልዕክት፣ በአዲሱ የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት ውስጥ በአንዳንድ አገሮች መካከል የጦርነት እና የአመጽ ስጋት ቢታይም፣ ይህ መጥፎ አጋጣሚ እንዳይከሰት ተስፋን ከማድረግ ወደ ኋላ ማለት አይገባም ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር አያይዘው በሁለቱ አገሮች፣ በሰሜን አሜሪካ እና በኢራን መካከል የተከሰተው ውጥረት ይረግብ ዘንድ ጥሪ አቅርበው፣ በሁለት አገሮች መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት እና መቻቻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ህጋዊነት እንዲኖረው በማለት አስገንዝበዋል።

በቅድስት መንበር የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ተወካይ የሆኑት፣ የቆጵሮስ አምባሳደር ክቡር አቶ ጆርጆ ፑሊደስ፣ ዲፕሎማቶችን በመወከል ለር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባቀረቡት የምስጋና ንግግራቸው፣ ያለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. በፖለቲካ መሪዎች እና በእምነት ተቋማት መሪዎች መካከል በርካታ የጋራ ውይይቶች የተደረጉበት መሆኑን አስታውሰው፣ በቅድስት መንበር የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ቀዳሚ ተልዕኮም ሰላምን እና ሁለ ገብ እድገትን ለሰው ልጆች በሙሉ ማዳረስ መሆኑን ገልጸዋል።    

ባለው የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ያስታወሱት የቆጵሮስ ክቡር አምባሳደር  አቶ ጆርጆ ፑሊደስ፣ ቅዱስነታቸው በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. ከግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም ከሆኑት ከአህመድ አል ጣይብ ጋር ያደረጉትን  የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ስምምነት ጠቅሰው፣ ወደ ሞሮኮ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውም፣ አንድነት እና የጋራ ውይይት ባሕል የሚታይበትን ማሕበረሰብ መገንባት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። ክቡር አምባሳደር አቶ ጆርጆ ፑሊደስ በማከልም ቅዱስነታቸው በልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን አንድት በማሳደግ ወንድማማችነት እና ፍቅርን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ በሮማኒያ፣ በቡልጋሪያ እና በሰሜን መቄዶኒያ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።

በሕፃናት ላይ የሚደርስ በደል መከላከል፣

ከጥር 14 እስከ ጥር 19 2011 ዓ. ም. ድረስ፣ በላቲን አሜሪካ አገር በሆነችው ፓናማ ለ34ኛ ጊዜ በተከበረው  ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቤተክህነትን አካትቶ በተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች በኩል በሕጻናት እና በወጣቶች ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ ክብር ጥሰቶች ጥቂቶች እንዳይደሉ ተናግረው በደሉ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን መሆኑን አስረድተዋል።

የትምህርት ስምምነት እና የቤተሰብ ቅድመ ሁኔታ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው እንደገለጹት በማሕበረሰብ ላይ የሚደርስ በደልን ለመከላከል አስቸኳይ የግንዛቤ ማስጨበት ሥራ መሰራት የሚያስፈልግ መሆኑን ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል በመጭው የጎርጎሮሳዊያኑ ግንቦት 14/2020 ዓ. ም. “ዓለም አቀፍ፣ ግንዛቤን የማስጨበጥ ተግባር ማጠናከር” በሚል ርዕሥ ጉባኤ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል። ለሌሎች ልብን ክፍት በማያደርግ ዓለም ውስጥ እንኖራለን ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የአቅመ ደካሞችን ሰብዓዊ ክብር ለማስጠበቅ እየሞከርን በሌላ ወገን አዲስ ለሚወለድ ትውልድ በቂ ዕድል እና ቦታ ሳንሰጥ ስንቀር፣ በዕድሜ እየገፋ የሚመጣውን የዓለማችን ሕዝብ፣ በተለይም የምዕራቡ ዓለም ሕዝብ መዘንጋት የለብንም ብለዋል።         

የሥነ ምህዳራዊ ለወጥ፣

በሥነ ምሕዳር ላይ የተከሰተውን ለውጥ ለየአገራቱ ፖለቲካ መሪዎች በማሳሰብ ላይ የሚገኘው ወጣቱ ትውልድ መሆኑ ያስታወቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የጋራ መኖሪያ ለሆነች ምድራችን ሊሰጥ የሚገባ እንክብካቤ እና ጥበቃ ሁላችንንም የሚያሳስብ መሆን አለበት ብለው፣ በሥነ ምህዳር ላይ የታየው ለውጥ ለማስተካከል የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ቅን ፍላጎት መታከል አለበት ብለዋል።

በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ የጋር ውይይት፣

ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. ውስጥ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. ከግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም ከሆኑት ከአህመድ አል ጣይብ ጋር ያደረጉትን  የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ስምምነት ጠቅሰው፣ ወደ ሞሮኮ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውም፣ አንድነት እና የጋራ ውይይት ባሕል የሚታይበትን ማሕበረሰብ መገንባት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን አንድት በማሳደግ ወንድማማችነት እና ፍቅርን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰዋል።

በሶርያ ሊደርስ የሚችል አስከፊ ቀውስ፣

ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ በሶርያ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት መዘንጋት የማይቻል መሆኑን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ የሰላም መፍትሄ በጋራ መፈለግ እና ሶርያን መልሶ መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ጎረቤት አገሮች የሆኑት ዮርዳኖስ እና ሊባኖስ ላበረከቱ ሰብዓዊ እርዳታ ቅድስት መንበር ለሁለቱም አገሮች ምስጋናዋን የምታቀርብ መሆኗን ገልጸዋል።

በሰሜን አሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚታይ ውጥረት፣

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሰሜን አሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚታየው ውጥረት አሳስቢ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት የተገነዘቡት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታት በሙሉ፣ ለጋራ ውይይት ቅድሚያን በመስጠት የጋራ ውይይቱ በአቀፍ ደረጃ ህጋዊ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
15 January 2020, 16:04