የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ በሃምሳ ዓመት ዕድሜው የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ በሃምሳ ዓመት ዕድሜው  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የሰው ልጅ በማኅበራዊ ልማት ዕቅድ ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከተማ በመካሄድ ላይ ለሚገኝ የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከጥር 12-15/2012 ዓ. ም. ድረስ ለሚቆየው ዓለም አቀፍ ጉባኤ በላኩት መልዕክታቸው፣ በሕዝባዊ እና በግሉ ማሕበረሰብ አስተዳደር ላይ የሚገኙ መሪዎች፣ የሰውን ልጅ በሚያስቀድም ፖሊሲ በመመራት፣ ሁሉ አቀፍ ማኅበራዊ እድገትን እንዲያመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ለጉባኤው ያሰሙት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን መሆናቸው ታውቋል። በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከጥር 12-15/2012 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደው የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ፣ ዘላቂ እድገትን ለማምጣት በተለያዩ የሥራ እና የአገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው ግንባር ቀደም ሚናን የሚጫወቱ መንግሥታዊ ተቋማትን፣ የንግድ እና የባሕል ተቋማትን የግሉን ማኅበረሰብ ያሰባሰበ መድረክ መሆኑ ተነግሯል። በዳቮስ ላይ እየተካሄደ ያለው የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ፣ የተቋቋመበትን 50ኛ ዓመት እያከበረ መሆኑን ከሥፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል።

የተሻለ ዓለምን መገንባት፣

በዓለም የኤኮኖሚ መድረክ መነጋገሪያ ርዕሠ ጉዳይ ላይ በማትኮር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች ዘላቂ ልማትን ለማምጣት የተሰማሩት መንግሥታዊም ሆነ የግል ድርጅቶች፣ የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም የተሻለ ዓለምን ለመገንባት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ ብቸኝነትን፣ ራስ ወዳድነትን እና የቅኝ ግዛት ርዕዮተ ዓለምን በማስቀረት ማኅበራዊ ዕድገትን ለማምጣት በሚያስችሉ ወይይቶች ላይ ለማትኮር መልካም ዕድልን የሚያመቻች መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው በዓለማችን የተመዘገቡ የኤኮኖሚ፣ የሥራ፣ የቴክኖሎጂ ዕድገቶች እና የአካባቢ ለውጦች ለሰው ልጅ በርካታ ጥቅሞችን ያስገኙ መሆኑ ቢታወቅም በሌላ ወገን በልማት ላይ አንዳንድ ተጽዕኖችን መፍጠራቸው አልቀረም ብለዋል።

ሁሉን የሚያሳትፍ ማኅበራዊ እድገትን ማምጣት፣

የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለዓለም የኤኮኖሚ መድረክ በላኩት መልዕክት፣ ሁላችንም የአንድ ቤተሰብ አባላት በመሆናችን አንዳችን ለሌላው የመጨነቅ እና የመተሳሰብ ሞራላዊ ግዴታ አለብን ብለው፣ ሥልጣንን ወይም ትርፍን ለመሰብሰብ ከሚደረግ ጥድፊያ ይልቅ ለሰው ልጅ ቅድሚያን በሰጡ ማሕበራዊ የልማት ዕቅዶች ላይ ማትኮር እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም ይህ ጥረት የቴክኖሎጂ እና ኤኮኖሚ እድገቶች ለማምጣት ከሚደረጉ የአጭር ጊዜ ውጥኖች በተጨማሪ አሁን ለሚያጋጥሙን ማኅበራዊ ችግሮች መፍትሄን ለማፈላለግ እና በሥራ ላይ ለሚውሉ የወደ ፊት ጥረቶች መልካም መንገድ የሚያመቻች መሆኑን አስረድተዋል።   

የጋራ ጥቅምን ማስቀደም፣

በራስ ወዳድነት፣ በፍቅረ ንዋይ ላይ ያተኮሩ አመለካከቶች መኖራቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እነዚህን የመሰሉ  አመለካከቶች የሚያመሩት ማኅበራዊ ጥቅምን ሳይሆን ለግል ጥቅም ቅድሚያን የሚሰጡ መሆናቸውን አስረድተው ውጤቱም ሰዎችን የዚህ ዓላማ ማራመጃ መሳሪያ ከማድረግ ባሻገር በሰዎች መካከል ሊኖር የሚገባውን የአንድነት እና የቸርነት ዓላማን በማስወገድ ወደ ኢ-ፍትሃዊነት ሥርዓት ይመራል ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም እውነተኛ የሰው ልጅ እድገት ሊመጣ የሚችለው በሰብዓዊ ቤተሰብ መከከል መለያየት ሳይታይበት፣ ለጋራ ጥቅም እያንዳንዱ የበኩሉን አስተዋጽዖን ሲያበረክት ነው ብለዋል። እውነተኛ ሰብዓዊ እድገት ለማምጣት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሌላውን ሰው ክብር ለመረገጥ የሚደረግ ሙከራ የራስን ክብር የማዳከም መሆኑን ቅዱስነታቸው ለዓለም የኤኮኖሚ መድረክ አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ሥነ ምህዳርን አስመልክተው ባቀረቡት ሃሳብ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን  እንክብካቤን እና ጥበቃን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ በሃምሳ ዓመት ዕድሜው የተቀዳጃቸው መልካም ውጤቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጠቅላላ ዕድገት ለምማጣት፣ በተለይም ለመጭው ትውልድ መልካም ዓለምን ለመገንባት እያንዳንዳችን ትልቅ ሞራላዊ ሃላፊነት አለብን ብለው፣ በዚህ ሃላፊነት በመመራት፣ አንድነትን በማሳደግ፣ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ፍትህን ተነፍገው በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙት ወደ ተሻለ ሕይወት እንደሚደርሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
22 January 2020, 14:23