ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለአካል ጉዳተኞች ሰላምታቸውን ሲያቀርቡ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለአካል ጉዳተኞች ሰላምታቸውን ሲያቀርቡ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የሰው ልጅ ነፍስ የተቀደሰ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጭው የካቲት 3/2012 ዓ. ም. ለ28ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው የሰው ልጅ ሕይወት ከተወለደበት ዕለት አንስቶ እስከ ዕለተ ሕልፈቱ ድረስ ጥበቃ እንዲደረግለት አሳስበው፣ በተለይም ለድሆች የሚደረግ እንክብካቤ ዋስትና ያለው መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በማቴ. 11.28 ላይ  “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ” በሚለው የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ ላይ በማስተንተን መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ወደ እኔ ኑ” የሚለው የወንጌሉ ጥቅስ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በሙሉ ያሳየውን የምሕረት መንገድ የሚያስታውሰን መሆኑን ገልጸው፣ ምሕረቱንም የገለጸው ርህራሄ በተሞላበት መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለውም ለአንድ ታማሚ የሚደረግ የፈውስ አገልግሎት ከእርሱም አልፎ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ጥረት ባምድረግ ለሚገኙት ቤተሰቦችም ጭምር መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። ይህን በማስታወስ ቅዱስነታቸው ለሕክምና ባለሞያዎች በሙሉ ባስተላለፉት መልዕክታቸው የሕክምና ሳይንስ ከሚፈቅደው ሞያዊ ግዴታ በተጨማሪ ለሰው ልጅ ሕይወት የሚገባውን አክብሮት በመስጠት ሞያዊ አገልግሎታቸውን እንዲያበረክቱ አደራ ብለዋል። ለመንግሥታት እና መንግሥታዊ ተቋማት ባቀረቡት ጥሪ፣ በድህነት ሕይወት ለሚገኙ ሕሙማን የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት ማሕበራዊ ፍትህን የተከተለ እና ዋስትና ያለው እንዲሆን በማለት ጥሪያቸውን አቅርበው፣ የመልካም ሳምራዊ ምሳሌን በመከተል፣ ለሕሙማን ያላቸውን ርህራሄ እና ፍቅር በመግለጽ፣ የሕክምና አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ ለሚገኙ የበጎ ፈቃደኞች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ኢየሱስ ምሕረቱን ይልካል፣

ኢየሱስ ክርስቶስ በሕመም ለሚሰቃዩት ምሕረቱን እንደሚያወርድላቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ደሆችን፣ ሕመምተኞችን፣ ኃጢአተኞችን፣ በማሕበራዊ የጭቆና አገዛዝ የሚሰቃዩትን በሙሉ እንደሚያስባቸው እና ከእርሱ ዘንድ የፈውስ እና የነጻነት ተስፋን የሚያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች ውስጥ ወድቀው ለሚሰቃዩት ምሕረቱን የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።

የደከሙት መጽናናትን ያገኛሉ፣

ስቃይ እና መከራ የደረሰባቸው በሙሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጽናናትን አግኝተው ለሌሎች ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ድጋፍ ይሆናሉ በማለት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ቅዱስነታቸው፣ በመሆኑም ለሕሙማን የሚደረግ የፈውስ አገልግሎት ሙሉ እንዲሆንያስፈልጋል ብለዋል። ለሕሙማን የሚሰጥ የፈውስ አገልግሎት ስጋዊ ብቻ መሆን የለበትም ያሉት ቅዱስነታቸው የፈውስ አገልግሎቱ መንፈሳዊ፣ ስሜታዊ፣ አእምሮአዊ እና የወዳጅነት መሆን ያስፈልጋል ብለው፣ የፈውስ አግልግሎቱ ከሕሙማኑ በተጨማሪ በማስታመም አገልግሎት ላይ ተሰማርተው ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸውም ፍቅር የሚገለጽበት መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

ቤተክርስቲያን የመልካም ሳምራዊ ሰው ምሳሌ ናት፣

በሕመም የሚሰቃዩት በሙሉ ትዕግሥትን የሚያገኙበትን ኃይል በመስጠት ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ይሆናቸዋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤተክርስቲያንም በሕመም ለሚሰቃዩት የመልካም ሳምራዊ ሰው ምሳሌ በመሆን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕርት ትመሰክራለች ብለዋል። ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን ምሕረት ለተቀበሉት ሰዎች የመሰብሰቢያ ሥፍራ ናት ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በሕመም የሚሰቃዩት ሰዎች መስቀላቸውን በመሸከም ከሕመማቸው ባሻገር የኢየሱስ ክርስቶስን የፈውስ ብርሃን ወደ ሌሎች ሰዎች ዘንድ ማድረስ ይችላሉ ብለዋል።

የሕክምና አገልግሎት ሰብዓዊ ክብርን ያገናዘበ አገልግሎት ነው፣

በሕክምና አቅርቦት እና በጤና አስተዳደር ላይ የተሰማሩ ሰዎች አገልግሎት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያለው እንደሆነ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ አገልግሎት ላይ የተሰማሩት የጤና ባለሞያዎች በሥራቸው አማካይነት የኢየሱስ ክርስቶስ እርዳታ በተግባር እንዲታይ ያደርጋሉ ብለዋል። በሚያበረክቱት አገልግሎትም ቅድሚያን ለሰው ልጅ ክብር መስጠት እንዳለባቸው ቅዱስነታቸው አሳስበው ይህ የፈውስ አገልግሎት የሕሙማንን እስከ ሕልፈታቸው ድረስ መደረግ በሚጋባው እንክባካቤ እና እርዳታ ላይ ያተኮረ እንጂ ዘመኑ ባመጣው የሕክምና አሰጣጥ ዜዴ በመታገዝ ነፍስን ከስጋ መለየት መሆን የለበትም ብለዋል።

የሰው ልጅ ሕይወት ቅዱስ ነው፣

የህክምና ሙያ የሰው ልጅ ያካበተውን የሕይወት ልምድ በማገናዘብ ምሕዳሩን የበለጠ ማስፋት አለበት ያሉት ቅዱስነታቸው የሰው ልጅ ሕይወት የተቀደሰ የእግዚአብሔር ስጦታ በመሆኑ ክብሩ ምን ጊዜም የማይጣስ ነው ብለው፣ በመሆኑም ወደ ዓለም ከመጣበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዕለተ ሕልፈቱ ድረስ እንክባካቤ፣ ጥበቃ እና ክብር ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። የሰው ልጅ ሕሊናም ለዚህ መለኮታዊ ትዕዛዝ በመገዛት የሰውን ልጅ ሕይወት ከጉዳት ለመካላከል እና ተገቢውን እንክብካቤ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። በዓለማች ውስጥ ጦርነቶች እና አመጾች በሚቀሰቀሱ ወቅት የሕክምና ባለሞያ ሕይወትም በአደጋ ላይ የሚወድቅ መሆኑን ያስታወሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የፖለቲካ መሪዎችም የሕክምና አገልግሎት አቅርቦትን ለፖለቲካ ዓላማ ማስኬጃ በማዋል፣ ለሕክምና ባለሞያዎች ሊደረግ የሚገባው ሕጋዊ የሕይወት ዋስና እንዳይሰጣቸው ያደርጋሉ ብለዋል።

ሕክምናን የማግኘት መብት ሊረጋገጥ ይገባል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጭው የካቲት 3/2012 ዓ. ም. ለ28ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በድህነት ሕይወት የሚሰቃይ ማሕበረሰብ የተነፈገውን የሕክምና አገልግሎት በሙላት እንዲያገኝ አሳስበው፣ የዓለም መንግሥታት እና መንግሥታዊ የሕክምና ተቋማት፣ በሕመም የሚሰቃይ ድሃ ማሕበረሰብ፣ የተሟላ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን መብት እንዲያረጋግጡላቸው አደራ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጎርጎሮሳዊያኑ 2017 ዓ. ም. በዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን ባስተላለፉት መልዕክታቸው ለታማሚ ቤተሰብ የሚደረግ የሕክምና አገልግሎት የእግዚአብሔር ርሕራሄ የሚገለጥበት አገልግሎት በመሆኑ በፖለቲካ ዘርፍም ቢሆን እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የፈውስ አገልግሎት በመሳተፍ፣ በሕመም ስቃይ ላይ ለሚገኙት ርህራሄን እና ፍቅርን በማሳየት የሕክምና አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ ለሚገኙት የሕክምና ባለሞያዎች እና የጤና ተቋማት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
04 January 2020, 14:58