ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በጦርነት ለተጎዱ ሕፃናት ክርስቶስ ብርሃኑን እንዲሰጣቸው እንደሚጸልዩ ገለጹ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በሚከበርበት በገና በዓል እና እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት የትንሳሄ በዓል በመሳሰሉ ታላላቅ የቤተክርስቲያን በዓላት በሚከበሩበት ወቅት በላቲን ቋንቋ  Urbi et Orbi በአማሪኛው ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም የተሰኘ መልእክት እንደ ሚያስተላልፉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት በታኅሳስ 15/2012 ዓ.ም የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የተከበረውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ምክንያት በማደረግ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በእለቱ ባስተላለፉት መልእክት “በጦርነት ለተጎዱ ሕፃናት ክርስቶስ ብርሃኑን እንዲሰጣቸው እንደሚጸልዩ” መግለጻቸው ተዘግቡዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያስተላለፉትን መልእክት ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

“በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ”(ኢሳ 9፡ 1)

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ!

እናት ከሆነችው ከቤተክርስቲያን ማህፀን ጀምሮ የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ ለብሶ እንደ ገና ተወልዶልናል።  ስሙ ኢየሱስ ይባላል፣ ይህም ማለት “እግዚአብሔር ያድናል” ማለት ነው። የአባቱ የማያልቀው እና ዘላለማዊ የሆነ ፍቅር ዓለምን እንዲኮንን ሳይሆን እንዲያድነው ወደ ዓለም ልኮታል (ዮሐ 3፡ 17)። አብ በታላቅ ምሕረት ለእኛ ሰጠን። እርሱን ለዘላለም ሰጠን። ወልድ በሌሊት ቀዝቃዛ እና ጨለማ ውስጥ እንደ አንድ ትንሽ ቀላል ነበልባል ብርሃን ሆኖ ተወለደ።

ከድንግል ማርያም የተወለደው ይህ ልጅ የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ሆነ። የአብርሃምን ልብ የመራ እና ወደ ተስፋይቱ ምድር የወሰደው ይህ ቃል በተጨማሪም በእግዚአብሔር ተስፋ በማድረግ የሚታመኑትን ሁሉ ወደ ራሱ ለመሳብ የሚችል ቃል ነው። ከግብፅ ባርነት ወደ ነፃነት በሚጓዙበት ወቅት ዕብራውያኑን የመራው ይህ ቃል እኛን ጨምሮ በሁሉ ዘመን ውስጥ በባርነት ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች በመጥራት ከእስራታቸው ነጻ የሚይያደርግ ቃል ነው። እርሱ ከፀሐይ የበለጠ ብሩህ የሆነ ቃል ነው ፣ ትንሽዬ በሆነ የሰው ልጅ ውስጥ ሥጋ ለብሶ የገባ ቃል ነው፣ ኢየሱስ የዓለም ብርሃን ነው።

ለዚህ ነው ነቢዩ “በጨለማ የሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን አዩ” (ኢሳ 9 1) በማለት የተናገረው። በሰው ልብ ውስጥ ጨለማ አለ፣ ነገር ግን የክርስቶስ ብርሃን አሁንም ከእዚህ ጨለማ የበለጠ ነው። በግል ፣ በቤተሰብ እና በማህበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ጨለማ አለ፣ ነገር ግን የክርስቶስ ብርሃን ከእነዚህ ጨለማዎች የበለጠ ነው። በኢኮኖሚያዊ ፣ በጂዮፖሊካዊ እና ስነ-ምህዳራዊ ግጭቶች ውስጥ ጨለማ አለ ፣ ነገር ግን አሁንም የክርስቶስ ብርሃን ከእዚህ ጨለማዎች የላቀ ነው።

በመካከለኛው ምስራቅ እና በተለያዩ የዓለም ሀገሮች በጦርነት እና በግጭት ለተሰቃዩ ብዙ ሕፃናት ክርስቶስ ብርሃኑን ያመጣ። ላለፉት አስርት ዓመታት አገራቸውን ተከራይተው ጦርነት በሚያድርጉ የባዕድ አገራት በሚፈጥሩት ማለቂያ በሌለው ግጭት ምክንያት አሁንም ቢሆን በስደት ላይ ለሚገኘው የሶርያ ህዝብ ማጽናናትን ያምጣላቸው። ዛሬ በጎ ፈቃድ ያላቸውን ወንዶች እና ሴቶች ህሊና ያነቃቃ። የዚያ አካባቢ ሕዝቦች በሰላም እና ደህንነት አብረው እንዲኖሩ እና በቃላት ሊገለጽ የማይችለው ስቃያቸው በዘላቂነት እንዲያበቃ ግጭቱን ለማስቆም መንግስታት እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መፍትሄ ያፈላልጉ ዘንድ ዘንድ ይህ የእግዚኣብሔር ቃል እንዲረዳቸው እንጸልይ። የሊባኖስ ህዝብን በመደግፍ እና አሁን ያለውን ቀውስ ለማሸነፍ እንዲችሉ እንዲረዳቸው እና ሁሉም የነፃነት እና አብሮ የመኖር፣ የመቻቻል መልእክት መስካሪዎች ይሆኑ ዘንድ ይህ ቃል እንዲረዳቸው እንጸልይ።

ጌታ ኢየሱስ የሰው ልጅ አዳኝ ሆኖ ወደ ተወለደባት ቅድስት ምድር ብርሃንን ያመጣ፣ ብዙ ሰዎች - እየታገሉ የሚገኙበት፣ ነገር ግን አሁንም ድረስ ተስፋ ያልቆረጡበት የሰላም፣ የደህንነት እና የብልጽግና ጊዜ እንዲሆንላቸው ብርሃኑን ይስጣቸው። አሁን ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኘውን እና ይህ ማኅበራዊ ቀውስ እያየለ ወደ ከፋ ሰብአዊ ቀውስ እና ስቃይ እየተሸጋገረ በሚገኝባት ኢራቅ መጽናናትን ያምጣ።

በቤተልሔም ውስጥ የተወለደው ሕጻን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ብጥብጥ እያጋጠማቸው ያሉ መላውን የአሜሪካ አህጉር ተስፋን መልሶ ያለምልም። በፖለቲካዊ እና በማህበራዊ ውጥረታቸው ለረጅም ጊዜ ስቃይ እና ተሞክሮ ውስጥ የሚገኙትን ተወዳጅ የቬኒዝዌላ ሕዝቦችን ያበረታታ፣ የሚያስፈልጋቸውን እርዳት ያገኙ ዘንድ ይርዳቸው። ፍትህን እና እርቅን ለማስፈን እና የእያንዳንዱን ሰው ክብር የሚጎዱትን በርካታ ስቃዮችን እና ግጭቶችን እንዲሁም የተለያዩ ዓይንት የድህነት ገጽታዎችን ለመቅረፍ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን ሁሉ ይባርክ።

ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ተጨባጭ መፍትሄ ለሚናፍቀው ለተወዳጁ ዩክሬን ሕዝብ የዓለም አዳኝ ብርሀን ይስጣቸው።

በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ሁኔታዎች የተነሳ ብዙውን ጊዜ ግለሰቦች ከአገር እና ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በመውጣት እንዲሸሹ በሚገደዱባት አፍሪካ አዲስ የተወለደው ጌታ ለአፍሪካ ህዝብ ብርሀን ይስጣቸው። ግጭቶች በቀጣይነት በሚከሰቱባት የምሥራቅ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪብሊክ ውስጥ ለሚኖሩት ሰዎች ሰላሙን ይስጣቸው። በዓመፅ ፣ በተፈጥሮ አደጋዎች ወይም በበሽታ ወረርሽኝ ምክንያት ለሚሠቃዩ ሁሉ መጽናናትን ይስጣቸው። በሃይማኖታቸው የተነሳ በቡርኪና ፋሶ ፣ በማሊ ፣ በኒጀር እና ናይጄሪያ በሚገኙ አካሪዎች ምክንያት ስደት ለሚደርስባቸው በተለይም ሚስዮናውያን እና ምዕመናን እንዲህም በእምነታቸው የተነሳ የታገቱት ምዕመናን ምጽናንቱን ያስጣቸው።

ከሰማይ ወደ ምድር የወረደው የእግዚአብሔር ልጅ በእነዚህ እና በሌሎች ኢፍትሃዊ ምክንያቶች የተነሳ የተሻለ ሕይወት ለማግኘት ተስፋ በማደረግ ለመስደድ የተገዱ ሰዎች ሕይወት ይጠብቅ። የመቃብር ስፍራ የሆኑ ምድረ በዳዎችን እና ባሕሮችን አቋርጠው እንዲሰደዱ ያስገደዳቸው ኢፍትሃዊነት ነው። በቃላት ሊገለጽ የማይችል የሰቆቃ መአት፣ ሁሉንም ዓይነት ባርነት እና በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ የሆነ ኢሰባዊ ግፍ የሚፈጸምባቸው የእስረኞች ማጎሪያ ጣቢያዎች እየተበራከቱ የመጡት በእዚሁ በኢፍታዊ ተግባር የተነሳ ነው። ክብር ከተጎናጸፈ ሕይወት ተስፋ ሊኖሯቸው ከሚችሉባቸው ቦታዎች ተለይተው እንዲሰደዱ ያደረጋቸው ዞሮ ዞሮ ይህ ኢፍታዊ ተግባር ሲሆን ይህም ተግባር በግድዬልሽነት በተሞሉ ሰዎች በገነቡት ግድግዳ ፊት እንዲቆሙ አድርጉዋቸዋል።

አማኑኤል ለሰብአዊው ቤተሰባችን አባላት ሥቃይ ሁሉ ብርሃንን ያመጣላቸው። የእኛን ብዙውን ጊዜ ደንዳና እና በራስ ወዳድነት የተሞላው ልባችንን እንዲያስተካክል እና የእሱ የፍቅር መስመር እንዲሆኑ ያደርግልን። በድህነት በተሞሉ የፊት ገጽታዎቻችን ላይ ፈገግታን በመሙላት ተርሰተው ለሚገኙ እና ለተገለሉ የዓለም ልጆች ሁሉ ሰላሙን ማዳረስ እንችል ዘንድ ይርዳን። ደካማ በሆኑ እጆቻችን አማካይነት ለታረዙት ልብስን፣ ለተራቡት ምግብን እንድንሰጥ እንዲሁም የታመሙትን እንድንፈውስ ይርዳን። በእኛ በወዳጃጆቻቸው አማካይነት ወደ አዛውንቶች እና ብቸኝነት ያጠቃቸው ሰዎች፣ ወደ ስደተኞች እና ወደ ተገለሉ ሰዎች መቀረብ እንችል ዘንድ ጸጋውን ይስጠን። በዚህ አስደሳች የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በተከበረበት የገና ቀን ርህራሄውን ለሁሉም ያመጣ፣ የዚህን ዓለም ጨለማ ያብራ።

25 December 2019, 18:57