ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የፊሊፒን ካቶሊካዊ ምዕመናን የክርስትና እምነታቸውን እንዲያስፋፉ ጥሪ አቀረቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ታኅሳስ 5/2012 ዓ. ም. በሮም ከተማ ለሚገኙ የፊሊፒን ካቶሊካዊ ምዕመናን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ በሮም ከተማ የሚኖሩ የፊሊፒን ካቶሊካዊ ስደተኛ ማሕበረሰብ ተካፋይ ሆነዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት በኢጣሊያ ውስጥ የሚገኙ የፊሊፒን ካቶሊካዊ ማሕበረሰብ ልዩ የወንጌል ተልዕኮ አደራ እንደተጣለባቸው ገልጸው ይህም በሚገኙባቸው ቁምስናዎች ውስጥ የእምነት ምስክርነትን መስጠት ነው ብለው፣ በባሕል እና በቋንቋ ልዩነት መካከል ያለውን አንድነት አጉልተው በማሳየት፣ ከሌሎች ልዩ ልዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር ያለውን የእምነት አንድ በግልጽ በማሳየት በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ያለውን ብዝሃነት እንዲገልጹ አደራ ማለታቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ አሌሳንድሮ ዲ ቡሶሎ የላከልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እምነትን የማስፋፋት እና የማሳደግ ተልዕኮዋቸውን በትጋት እንዲወጡ በማለት በቁጥር ወደ 7500 ለሚሆኑ የሮም ከተማ ነዋሪ ለሆኑት የፊሊፒን ካቶሊካዊ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት ምዕመናኑ በሚገኙበት ቁምስና እና በሚሳተፉባቸው መንፈሳዊ እንቅስድቃሴዎች ውስጥ ሊያበረክቱ የተጠሩበት ልዩ መንፈሳዊ ተልዕኮ እንዳለባቸው ገልጸዋል። በሮም የፊሊፒን ካቶሊካዊ ምዕመናን ሐዋርያዊ አስተባባሪ ካህን የሆኑት ክቡር አባ ሪክ ጄንቴ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር እንደገለጹት በሮም ከተማ የሚገኙ የፊሊፒን ካቶሊካዊ ምዕመናን በሚገኙባቸው ቁምስናዎች የእምነት ምስክርነት በመስጠት ለሌሎች መልካም ምሳሌ ሆነዋል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአንድ ወቅት በንግግራቸው የፊሊፒን ስደተኛ እናቶች በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ እምነትን ለሌሎች በመመስከር እና በማስተማር መልካም ምሳሌ እንደሆኑ መናገራቸውን ያስታወሱት ክቡር አባ ሪክ ጄንቴ፣ የአገራቸው ካቶሊካዊ ምዕመናን በሄዱበት አገር ሁሉ የእምነት እና የወንጌል ብርሃን ለሕዝቦች ሁሉ የሚያበሩ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ እምነትም ከ500 ዓመት በፊት የአውሮፓ ሚሲዮናዊያን የሰበኩላቸው የቅዱስ ወንጌል መልካም ዜና ነው ብለዋል።

የፊሊፒን ማሕበረሰብ በሮም እና አካባቢዋ ወረዳዎች 43, 000 ይደርሳሉ፣

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉት ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ በተጀመረው የስብከተ ገና ወቅት ሦስተኛ እሑድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ ከሚገኙ የፊሊፒን ካቶሊካዊ ምዕምናን ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሲያቀርቡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል። በሮም እና አካባቢዋ የሚገኙ የፊሊፒን ስደተኛ ቤተሰብ ቁጥር 43,000 ሲሆን ይህም በከተማዋ እና በአካባቢው ከሚኖሩት ሌሎች የውጭ አገር ስደተኛ ቁጥር ጋር ሲወዳደር በብዛት ሁለተኛ የሚያደርጋቸው መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ከትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 35 ተወስዶ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ ላይ በማስተንተን ባቀረቡት አስተንኖ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ስጋን በመልበስ ወደ ዓለም የመጣው ለሰው ልጅ በሙሉ ድነትን ይዞ እንደሆነ ገልጸው፣ በተለይም ለአቅመ ደካሞች እና በችግር ላይ ለሚገኙት በሙሉ ልዩ ርህራሄ እንዳለው ለማሳየት ነው ብለዋል።

እግዚአብሔር የፍቅር ዓይኑን በተቸግሩት ላይ አድርጓል፣

ከትንቢተ ኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ተውስዶ በተነበበው ንባብ ላይ እና ከምዕመናን በኩል በቀረበው የምስጋና መዝሙር ላይም እንደተገለጸው የእግዚአብሔር ርህራሄ ለተቸገሩት፣ ለታወሩት፣ ለማይሰሙት እና አካለ ጎደሎ ለሆኑ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለተጨቆኑት፣ ለተራቡት እና ለተጠሙት፣ ለታሠሩት፣ ለተሰደዱት፣ ወላጅ አልባ ለሆኑት፣ ብቻቸውን ለቀሩት እናቶች በሙሉ ልዩ የእግዚአብሔር ፍቅር የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አስረድተዋል። ችግር ውስጥ የወደቁት በሙሉ ትናንትም ሆነ ዛሬ በማሕበረሰቡ መካከል ተዘንግተው እና ተገልለው የሚኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ እንደጻፈው፣ በእግዚአብሔር ምሕረት እና ፍቅር እውሮች እንደሚያዩ፣ አንካሶች ቆመው እንደሚሄዱ፣ ለምጻሞች እንደሚነጹ፣ ደንቆሮዎች እንደሚሰሙ፣ ሙታንም እንደሚነሱ የወንጌል ምስራችም ለድሆች መሰበኩን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማወጅ እነዚህ ምልክቶች በቂ ናቸው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማወጅ መለከትን መንፋት አያስፈልግም ብለው በኃጢአተኞች ላይ ከመፍረድ ይልቅ ከክፉ ሁሉ ነጻ በመውጣት የእግዚአብሔርን ምሕረት እና ሰላም ማወጅ እና መመስከር ያስፈልጋል ብለዋል።

የእግዚአብሔር የምሕረት መሣሪያዎች ነን፣

እግዚአብሔር በስጋ የተገለጠበትን ምስጢር ለማከበር በመዘጋጀት ላይ እንገኛለን በማለት ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፣ የእግዚአብሔር በስጋ መገለጥ እርሱ ለሕዝቡ ያሳየው የምሕረት መንገድ ነው ብለው በተለይም በማሕበረሰቡ መካከል አነስተኛ እና አቅመ ደካማ ለሆኑት ያሳየው የምሕረት ምልክት ነው ብለዋል። በእነዚህ ምልክቶች በመታገዝ የእግዚአብሔርን መንግሥት በሚገባ ማወቅ እንችላለን ብለዋል። ከሕብረተሰቡ መካከል የተገለሉት፣ የተረሱት እና ደጋፊ የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መምጣቱን ያስታወቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ለእነዚህ ሰዎች በሙሉ አዲስ ሕይወትን ይዞ እንዲመጣ በጸሎታችን እንጠይቅ ብለው እኛም በበኩላችን የእግዚአብሔር የፍቅር እና የምሕረት መሣሪያዎች እንድንሆንላቸው መጸለይ ያስፈልጋል ብለዋል።

በብዝሃነት መካከል አንድነትን የመገንባት ተልዕኮ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ ከሚገኙት የፊሊፒን ካቶሊካዊ ማሕበረሰብ ጋር ባሳረጉት  የመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት የፊሊፒን ካቶሊካዊ ምዕመናን የተሻለ ሕይወት ፍላጋ ከሚወዱት የትውልድ አገር የተሰደዱ ቢሆንም በስደት በሚደርሱበት አገር ሁሉ ልዩ የወንጌል ተልዕኮ የሚጠብቃቸው መሆኑን ገልጸዋል። ክርስቲያናዊ እምነታችሁ በሚገኙበት አገር ቁምስናዎች እና በሚኖሩበት ማሕበረሰብም መልካም ምሳሌ እንዲሆን ያስፈልጋል ብለው መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶቻቸውን ከሚኖሩበት ማሕበረሰብ ጋር እንዲጋሩ አደራ ብለዋል። በተመሳሳይ መልኩ ከሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎች የሚቀስሙት የሕይወት ልምድ ለቀጣይ ሕይወት የሚጠቅማቸው መሆኑን አስረድተዋል። በብዝሃነት ውስጥ ያለውን አንድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንድናሳድግ ተጠርተናል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ የተጀመረውን የእግዚአብሔር መንግሥት በጋራ ሆነን ለመገንባት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው የተሰጡንን የተለያዩ የቸርነት ጸጋዎችን አንድ ላይ በማስተባበር በመካከላችን የተቸገሩትን፣ የደሄዩትን፣ የተገለሉትን እና አቅመ ደካማ የሆኑትን ለማገልገል ተጠርተናል ብለዋል። ይህን በማድረግ የእግዚአብሔር መንግሥት የሚገለጥበትን ምልክት አጉልተን ማሳየት እንችላለን ብለዋል።

ወንጌል በተለያዩ ቋንቋዎች ይሰበክ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ታኅሳስ 5/2012 ዓ. ም. በሮም ከተማ ለሚገኝ የፊሊፒን ካቶሊካዊ ማሕበረሰብ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ያሰሙትን ስብከተ ወንጌል ከማጠቃለላቸው አስቀድመው እንደተናገሩት የድነታችን ምክንያት የሆነውን ቅዱስ ወንጌል በሕብረት መመስከር እንደሚያስፈልግ፣ በተቻለ መጠን ለሰው ልጅ በሙሉ በተለያዩ ቋንቋዎች መነገር እንደሚያስፈልግ አሳስበው በቅርቡ ልናከብር በዝግጅት ላይ የምንገኘው የሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት፣ ምስክርነታቸውን በደስታ መግለጽ እንዲችሉ ሃይልን እና ብርታትን እንዲሰጣቸው በማለት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።

16 December 2019, 18:28