ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በአሸባሪዎች እጅ የተገደሉትን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እሑድ ታኅሳስ 19/2012 ዓ. ም. በዕለቱ በተነበቡት ቅዱሳት መጽሐፍት ላይ በማስተንተን ካቀረቡት ስብከት ቀጥለው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናኑ ጋር በመሆን የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል። በጣሊያን ውስጥ ከተለያዩ ቁምስናዎች ለመጡት እና ለተለያዩ አገሮች ምዕምናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ሀገር ጎብኚዎች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ውስጥ በአሸባሪዎች ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡ ከ70 በላይ ነፍሳትን፣ በአደባባዩ ከተሰበሰቡ ምዕመናን ጋር ሆነው በጸሎታቸው አስታውሰዋቸዋል። ቅዱስነታቸው በሐዘን ለወደቁት ወላጅ ቤተሰቦች እና ዘመዶቻቸው መጽናናትን በመጠየቅ ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም የሮም ከተማን ጨምሮ በጣሊያን ከሚገኙ የተለያስዩ ሃገረ ስብከቶች ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ መንፈሳዊ ማሕበራት እና ወጣቶች በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በአደባባዩ ለተገኙት ቤተሰቦች በሙሉ ልባዊ ሰላምታቸውን አቅርበው፣ እቤታቸው ሆነው በብዙሃን መገናኛዎች የክብረ በዓሉን ሥነ ሥርዓት ለተከታተሉት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ወቅት እንዳስረዱት ቤተሰብ ዘወትር እገዛ -ኣና ድጋፍ የሚያስፈልገው የማሕበረሰብ እና የአገር ውድ ሃብት መሆኑንም ገልጸው ለቤተሰቦች ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።
ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በሙሉ መልካም ዕለተ ሰንበት ተመኝተው፣ በመገባደድ ላይ ያለውን የአውሮፓዊያኑን 2019 ዓ. ም. በማስታወስ በሰላም እንዲጠናቀቅ ተመኝተው በቤተሰብ መካከል መወያየት እና መመካከር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ከምዕመናን በኩል ለሚቀርብላቸው የጸሎት ድጋፍ እና መልካም ምኞት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በአደባባይ የተገኙ ምዕመናን በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ካሉ በኋላ መልካም ዕለተ ሰንበትን በመመኘት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።