ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ጽንሰተ ማርያም እምነታቸውን ያጡትን፣ ተስፋ የቆረጡትንም ታጽናናለች”።

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በኅዳር 28/2012 ዓ.ም. የጽንሰታ ማርያም ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔታ መከበሩ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓመታዊው የጽንሰተ ማርያም ክብረ በዓል ላይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እምነታቸውን ያጡት እና ተስፋቸውንም የቆረጡትን በማጽናናት ረዳታቸው እንድትሆን በማለት ጸሎታቸውን ወደ ማርያም ዘንድ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ከሰዓት በኋላ በሮም ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ፣ ፒያሳ ስፓኛ ወይም ስፔን አደባባይ በመሄድ በሥፍራው በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ምስል ፊት ቀርበው ከከተማው ምዕመናን ጋር ጸሎታቸውን አቅርበዋል። በሥፍራው ለተገኘው የሮም ከተማ ነዋሪዎች ባደረጉት ንግግር ልበ ብልሹነት የሰዉን ልጅ ከሚደርስ አደጋ ሁሉ የካፋ ነው ካሉ በኋላ በጸጋ የተሞላች፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ድል አድራጊነት ዘወትር የምታስታውሰንን እናት ለሰጠን ቸሩ እግዚአብሔር ምስጋናችችን እናቅርብ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙትም በርካታ ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል በሕይወታች ሁሉ ለእግዚአብሔር የምንሰጠው ምላሽ የይሁንታ ሊሆን ይገባል ማለታቸው ታውቋል።

ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇ  ኢየሱስ ክርስቶስ በክፋት ላይ ድልን እንደተቀዳጀ ዘወትር ታስታውሰናለች ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኃጢአተኛ መሆን እና ልበ ብልሹ መሆን የተለያዩ ናቸው ብለው የኢየሱስ ድል አድራጊነት ከወደቅንበት ኃጢአት አንስቶን የእግዚአብሔርን ምሕረት እንድናገኝ ማድረጉን አስረድተው የልብ መበላሸት ውጫዊ ገጽታችንን አሳምሮ በልባችን ግን ብዙ ክፋቶችን ይዘን እንድንቀመጥ ያደርጋል ብለዋል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልበ ንጹሓን እንድንሆን ዘወትር ታስታውሰናለች ብለው በሕይወታችን ሊያጋጥመን ከሚችል አደጋ ሁሉ ከከፋው ከልበ ብልሹነት ተላቅቀን ነጻ መውጣት ያስፈልጋል ብለዋል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እምነታቸውን ላጡት እና ተስፋቸውንም ለቆረጡት በሙሉ መጽናናትን በመስጠት ረዳታቸው ናት በማለት ንግግራቸውን ያሰሙት ቅዱስነታቸው እምነታቸውን አጥተው የሚባዝኑ፣ እረፍትን ያጡ እና እፎይታን ያላገኙ ብዙ ናቸው ብለው ለእነዚህ በሙሉ የእመቤታችን ማርያም እርዳታ እንዲደረሳቸው በጸሎታችን እናግዛቸው ብለዋል። የሰዎችን ልብ አስሮ የሚገኝ የክፋት ሰንሰለት ሲበጣጠስ ማሕበራዊ ሕይወትም የተሻለ እንደሚሆን የሚተነፍሱትም አየር ንጹሕ ይሆናል ብለዋል።     

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ኅዳር 28 ቀን 2012 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኝ የስፔን አደባባይ ላይ ካቀረቡት የጸሎት ሥነ ሥርዓት በኋላ በስፍራው ለተገኙት በሙሉ እንዲሁም ከተለያዩ የጣሊያን ክፍለ ሀገራት ለመጡት የአካል ጉዳተኞች፣ ለበጎ ፈቃደኞች እና የተለያዩ ማሕበራዊ አገልግሎቶችን በማበርከት ላይ ለሚገኙ ድርጅቶች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
09 December 2019, 17:29