ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ማዕረገ ክህነት የተቀበሉበትን 50ኛ ዓመት አከበሩ!

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የክህነት ሕይወት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት ዛሬ ታኅሳስ 3/2012 ማክበራቸው ይታወሳል። በሰላሳ ሦስት ዓመት ዕድሜአቸው የክህነት ማዕረግ የተቀበሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ራሳቸውን ያዘጋጁት የእግዚአብሔርን ምሕረት አውቀው ቆራጥ ውሳኔን ባደረጉበት ወቅት እንደ ሆነ ተገልጹዋል።  

የእዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በትውልድ አርጄንቲናዊ የሆኑት ካርዲናል ጆርጅ ማሪዮ በርጎሊ በመጋቢት 13/2013 ዓ.ም. 266ኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው በተመረጡበት ወቅት በ13ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው እና የድኾች አባት በመባል የሚታወቀው፣ እንዲሁም የፍራንችስካዊያን ማሕበር መስራች የነበረው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ፣ በሕይወቱ ዘመን ልድኾች ባሳየው ትህትና፣ ክብር፣ ፍቅር እና ልገሳ እርሳቸው በጣም ከሚያደንቁዋቸው የካቶሊክ በቴክርስቲያን ቅዱሳን አንዱ በመሆኑ የተነሳ እርሳቸውም ይህንን የቅዱስ ፍራንቸስኮን አብነት በመከተል በጵጵስናቸው ዘመናቸው ለድኾች፣ ለስደተኞች፣ በዝቅተኛ ደረጃ ለሚኖሩ የማሕበረሰብ ክፍሎች፣ በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ እኩልነት እና ፍታዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር በማሰብ በእዚህ መሰረት የቅዱስ ፍራንቸስኮን ስም የጵጵስናቸው ዘመን መጠሪያ እንዲሆን በማሰም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መጠሪያ ስማቸው እንዲሆን መምረጣቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው በተመረጡ በእነዚህ 6 ዓመታት የሊቃነ ጳጳስነት ዘመናቸው በተለይ ቤተ-ክርስቲያን ሚስዮናዊ የሆነ ተግባሯን አጠናክራ እንድትቀጥል እና ለሁሉም የሰው ልጆች በቅዱስ ወንጌል የሚገኘውን ደስታ እንድትመሰክር፣ በማንኛውም የቅዱስ ወንጌል የማብሰር ሂደት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በቀጥታ ተሳታፊ ይሆን ዘንድ በመፈቅድ ማከናውን እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው አበክረው መንገራቸው እና አሁንም ቤተክርስቲያን በእዚሁ መንገድ እንድትቀጥል ማሳሰባቸውን በፍጹም አላቋረጡም።

ቅዱስነታቸው በእነዚህ ስደስት ዓመታት ውስጥ በላቲን ቋንቋ Lumen Fidei በአማሪኛው የእመንት ብርሃን የተሰኘ እና በእመንት ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ እና Laudato si በአማሪኛው ውዳሴ ለአንተ ይሁን በሚል አርእስት የጋራ መኖሪያ ቤታችንን ስለ መንከባከብ (የአየር ንብረት ለውጥ) በማስመልከት የጻፉት ደግሞ ሁለተኛው ሐዋርያዊ መልእክት እንደ ነበረ ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በእነዚህ ስድስት ዓመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ሁለት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ለንባብ ማብቃታቸው የሚታወቅ ሲሆን እነዚህም Evangelii Gaudium በአማርኛ ሲተረጎም በወንጌል የሚገኝ ደስታ የሚለው በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን በእዚህም ቃለ ምዕዳን ቤተክርስቲያን በጉዞ ላይ መሆን እንዳለባት እና ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን ለማከናወን እና ሰዎችን ወደ እግዚኣብሔር ለመመለስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደ ሕዝቡ መሄድ እንዳለባት የሚያሳስብ ቃለ ምዕዳን ሲሆን በሁለተኛነት ደግሞ amoris laetitia በአማርኛው የፍቅር ሐሴት በሚል አርእስት ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር፣ በቤተሰብ ውስጥ ስለሚታዩ ተግዳሮቶች፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለቤተሰብ ማድረግ ሰለሚጠበቅባቸው ሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚያወሳ ድዕረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል። በእዚህ ቃለ ምዕዳን በተለይም የሐይማኖት መሪዎች እና አባቶች በቤተሰብ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በጥንቃቄ እና ብስለት በተሞላበት መልኩ፣ በመመርመር በቤተሰብ ውስጥ የሚያግጥሙ ችግሮችን በችኮላ ከማውገዝ ይልቅ በእግዚኣብሔር ምሕረታዊ ጸጋ በመታገዝ የመፍትሄ ሐሳቦችን መጠቆም እንደ ሚገባቸው እና ይህንንም ክህሎት ማዳበር እንድችሉ ቤተሰብን የተመለከተ ትምህርቶች ከዘረዓ ክህነት ጀምሮ መስጠት አስፍላጊ መሆኑን የሚገልጽ ቃለ ምዕዳን ነው።

23 የሚሆኑ በላቲን ቋንቋ Motu proprio በአማሪኛው በግርድፉ ሲተረጎም (አንድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እንደራሴ በመሆኑ፣ በእዚህ በተሰጠው መንፈሳዊ ስልጣን በራሱ ተነሳሽነት ወቅታዊ ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባ መልኩ የሚጽፋቸው ሰነዶች፣ የሚያደርጓቸው ሹመቶች፣ ውሳኔዎችን የተመለከቱ ጉዳዮችን ያመለክታል) በእዚህም መሰረት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በራሳቸው ተነሳሽነት 23 ሐዋርያዊ ሕግ-ጋቶችን ያዘሉ መልእክቶች መጻፋቸው ያታወሳል። እነዚህም በእርሳቸው የግል ተነሳሽነት የተጻፉ 23 ሐዋርያዊ ሕግጋትን የያዙ መልእክቶች ወይም ባላቲን ቋንቋ ሞቱ ፕሮፕሪዮ መልእክታቸው “የቅድስት መንበር የበላይ የመስተዳድር አካላት እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የቅርብ የሥራ ተባባሪዎች መማክርት ጥልቅ ታድሶ እንዲያደርጉ የሚያሳስቡ መልእክቶች፣ በቅድስት መንበር ውስጥ በተለይም ደግሞ በፋይናንስ እና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያሳስቡ መልእክቶች፣ በአንድ ባል እና በአንድ ሚስት መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን እንዴት ለመፍታት እንደ ሚቻል እና እንዲሁም ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ማስቀመጥን የተመለከተ መልእክት፣ ለስርዓተ አምልኮ አገልግሎት ጥቅም ላይ የሚውሉ መጸሐፍት በእያንዳንዱ ሀገር ብጹዕን ጳጳሳት እውቅና አሁን ካለው ሁኔታ ጋር በሚመጣጠን መልኩ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ የታለመላቸውን ግቦች ይመቱ ዘንድ ክለሳ እንዲደረግባቸው የሚጠይቅ መልእክት፣ እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ አርእስቶችን ያቀፉ 23 ሞቱ ፕሮፕሪዮ በራሳቸው ተነሳሽነት በጣም ተጨባጭ እና ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ገንቢ የሆኑ ሐሳቦችን በማንሳት ለመፍቴ ማቅረባቸው ያታወሳል።

ቅዱስነታቸው በእነዚህ ስድስት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘመናቸው ቤተሰብን በተመለከት ሦስት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የብጹዐን ጳጳሳት ጉባሄዎች እንዲካሄዱ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በእዚህም ወቅታዊ በሆነ መልኩ በቤተሰብ መካከል አሁን ስለሚታዩ ተግዳሮቶች በማንሳት እና ትኩረት በመስጠት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በቤተሰብ ጉዳይ እንዲመክሩ በማድረግ ወቅታዊ ለሆኑ ችግሮች ወቅታዊ የሆነ ምላሽ በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚሰጥበትን የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲ ቀይስ በር መክፈታቸው ያታወሳል፣ በተመሳሳይ መልኩም በወጣቶች ዙሪያ የሚመክር የብጹዕን ጳጳሳት ጉባሄ እንዲደረግ፣ እንዲሁም “አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር”  በሚል መሪ ቃል በቅርቡ በአማዞን አከባቢ በሚኖሩ ሕዝቦች እና በአማዞን ጥቅጥቅ ደን ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ከፍተኛ ውድመት በተመለከተ ጉባሄ ባቫቲካን እንዲካሄድ ማድረጋቸውም ይታወሳል።

ከታኅሳስ 01/2008 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 11/2009 ዓ.ም. ደርስ ለ349 ቀናት ያህል የቆየ ልዩ ቅዱስ የምሕረት አመት ኢዩቤልዩ ማወጃቸው የሚታወስ ሲሆን ይህንን ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት በወቅቱ በክርስቲያኖች እና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ በተነሳው የእርስ በእርስ ግጭት ተጎሳቁላ በነበረች ሀገር በመገኘት የሁለቱንም የሐይማኖት ተወካዮች በአንድነት ፊት ለፊት አቀራርበው እንዲነጋገሩ በማድረግ እርቅ እንዲፈጥሩ መንገዱን በመክፈት በእዚያው በመካኛው የአፍሪካ ሪፖብልክ በባንጉዊ ከተማ በሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካቴድራል ተገኝተው ልዩ ቅዱስ የምሕረት አመት ኢዩቤሊዪ ማስጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን በእነዚህም 349 ቀናት ውስጥ ምዕመናን መንፈሳዊ እና አካላዊ የምሕረት ተግባራትን የሚፈጸሙበት ወቅት መሆኑን ገልጸው፣ በእዚህ ልዩ ቅዱስ የምሕረት አመት ክርስቲያኖች እርቅ እና ሰላም ይፈጥሩ ዘንድ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በስድስት አመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘማናቸው ከጣሊያን ውጪ 32 ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን የመጀመርያውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ካደረጉበት ከብራዚል አንስቶ በእስራኤል፣ በዮርዳኖስ፣ በፍልስጤም፣ በዮርዳኖስ፣ ድቡብ ኮሪያ፣ በአልባኒያ፣ በፈረንሳት፣ በቱርክ፣ ሲሪላንካ፣ ፊሊፒንስ፣ ቦሲኒያ ሄርዘጎቪና፣ ቦሊቪያ፣ ኤኳዶር፣ ፓራጉዋይ፣ በኩባ፣ በአሜሪካ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ የማካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብልክ፣ ሜክሲኮ፣ ግሪክ፣ አርሜኒያ፣ ፖላንድ፣ ጆርጂያ፣ ዘጠኝ መቶ የሚሆኑ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ብቻ የሚገኙባትን አዘረበጃን፣ ሲዊድን፣ ግብፅ፣ በፖቹጋል፣ በኮሎንቢያ፣ ማያንማር (የቀደሞ ስሟ በርማ)፣ ባግላላዲሽ፣ ፔሩ፣ ቺሊ፣ አየርላንድ፣ ታናማ፣ ሲውዘርላንድ፣ኢስቶኒያ፣ ላቲቪያ፣ ሉቱዋኒያ፣ በተባበሩት የአረብ ሄምሬትስ አቡዳቢ፣ በሞሮኮ፣ በሰሜን መቀዶኒያ፣ በሞዛንቢክ፣ በማድጋስካር፣ በሞሪሺዬስ በቅርቡ ደግሞ 32ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በታይላንድ እና በጃፓን በቅደም ተከተል ማደረጋቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉዋቸው መስዋዕተ ቅዳሴዎች ላይ ፉክክርን በተመለከተ የሚከተሉትን ተናግረው ነበር፦

ሌላው ቀርቶ ጭቅጭቅ የሚፈጠረው ከፉክክር ነው፣ ምክንያቱም ብዙ ሰዎች እነርሱ በማደግ ላይ መሆናቸው ሰለማይሰማቸው ነው፣ አንደኛው ከአንደኛው በተሻለ ሁኔታ ማደጉን ለማሳየት በሚያደርገው ፍክክር ጭቅጭቅ ይፈጠራል፣ ፉክክር ሰዎችን የሚያጠፋ አፍራሽ የሆነ ተግባር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ሚለው “በማነኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የተቀናቃኝነት መንፈስ አይኑር” ይላል። ፉክክር ሌላውን ለመጨቆን የሚደረግ ትግል ውጤት ነው። ፉክክር በጣም አስቀያሚ የሆነ ነገር ነው፣ ግጭት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ መፍጠር ይቻላል፣ ነገር ግን ሁልጊዜ ሌላውን ለማጥፋት እና እራስን ከፍ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው። እናም እኔ በሌሎች ፊት ጎበዝና በጣም ጥሩ ሆኜ ለመታየት በመፈለግ ሌሎችን አሳንሼ እመለከታለሁ። የራሴን ከፍታ ብቻ ጠብቄ እጓዛለሁ። ፉክክር የወደፊቱን የራሴን ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል መንገድ ነው።

የጦርነት ዜናዎችን ስናነብ፣ ለምሳሌም በየመን በረሃብ አረንቋ እየተገረፉ የምገኙትን ሕጻናት ጉዳይ ስንመለከት ይህ ጉዳይ የጦርነት ፍሬ እንደ ሆነ እንገነዘባለን፣ እነዚህ ምስኪን ሕጻናት ለመኖር ሲታገሉ እንመለከታለን. . . ለምንድነው እርሱ የሚበላ ነገር የሌላቸው? ነገር ግን በተመሳሳይ መልኩም በየቤታችን በየተቋሞቻችን በፉክክር የተነሳ ተመሳሳይ የሆኑ ጦርነቶች ይካሄዳሉ፣ ጦርነት የሚጀምረው ከዚህ ነው! ሰለዚህ በቅድሚያ ሰላም ማስፈን መጀመር የሚገባን ከዚህ ነው፣ ከቤተሰብ፣ ከቁምስና፣ ከተቋማት፣ ከሥራ ቦታ ሊጀመር ይገባል፣ ይህንንም የምናደርገው ሁል ጊዜ አንድ የሆነ ማኅበረሰብ ለመገንባት እና የራሳችንን ሳይሆን የማኅበረሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅ ሊሆን ይገባል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

13 December 2019, 15:30