ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች ከዓለም ዙሪያ ደርሷቸዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 83ኛ ዓመት የልደት በዓል በማስመልከት ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች እየደረሱ መሆናቸውን እና የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን በጸሎት ማስታወሳቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ቸቺሊያ ሴፒያ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የያዝነው የጎርጎሮሳዊያኑ ታኅሳስ ወር ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልዩ መታሰቢያ ወር መሆኑን የገለጸው የቫቲካን ዜና አገልግሎት፣ ቅዱስነታቸው ያለፈው ታኅሳስ 3/2012 ዓ. ም. የክህነታቸውን 50ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓላቸውን አክብረው ማለፋቸውን አስታውሶ ቅዱስነታቸው የወንጌል አገልግሎታቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በማበርከት ላይ መሆናቸውን ገልጿል። መላው ዓለም በዛሬው ዕለት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ ጋር ሆኖ 83ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን አክብሮ መዋሉ ታውቋል። በሺዎች ከሚቆጠሩ ምዕመናን በኢሜይል አድራሻቸው በኩል የደስታ እና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች የደረሷቸው መሆኑ ታውቋል። በዚህ አድራሻቸው አማካይነት ከሕጻናትም በርካታ መልዕክቶች የደረሷቸው መሆኑ ሲታወቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በኢስታግራም ማሕበራዊ ሚዲያ በኩል “ፍራንቺስኩስ” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምስል ሥር መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል። ከሃያላን መንግሥታት መሪዎች፣ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛም የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት መድረሳቸው ታውቋል። ለልደት በዓላቸው ከደረሳቸው ስጦታዎች መካከል አንዱ እና ትልቁ በእርሳቸው ጥያቄ መሠረት በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ምዕመናን የቀረበላቸው ጸሎት ሲሆን ባለፈው ዓመትም በቅድስት መንበር ከካርዲናሎች መማክርት ጋር ሆነው ያቀረቡት የምስጋና እና የደስታ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መሆኑ ይታወሳል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
17 December 2019, 17:09