ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በቤተሰብ መካከል መተጋገዝ እና ውይይት እንዲኖር አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ታኅሳስ 19/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በዕለቱ በተነበቡት ቅዱሳት መጽሐፍት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባቀረቡት ስብከታቸው፣ ቤተሰቦች ቅዱስ ወንጌልን የሕይወታቸው መመሪያ በማድረግ፣ እንደ ናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ እርስ በእርስ መተጋገዝ  ያስፈልጋል ብለዋል። ክቡራት እና የዚህ ጽሑፍ አንባቢያን ከዚህ በታች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ትርጉም እንደሚከተለው አርቅርበንላችኋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ!

እጅግ መልካም በሆነው በዛሬው ዕለት የናዝሬቱን ቅዱስ ቤተሰብ ዓመታዊ ክብረ በዓል በማክበር ላይ እንገኛለን። የናዝሬቱ ቤተሰብ ቅዱስ ሆኖ መገኘቱ ከእግዚአብሔር ባገኘው ስጦታ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ ይህ ቤተሰብ በእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ ውስጥ የገባው በነጻነት እና ሙሉ ሃላፊነትን በማሳየት መሆኑን እንገነዘባለን። የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመኖር ራሱን ሙሉ በሙሉ ወደ ለእግዚአብሔር አቅርቧል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ታላቅ ሥራ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት እንድትሆን ስትመረጥ በደስታ መቀበሏ ሳይገርመን አይቀርም። በወቅቱ ማርያም ለምንድር ነው፣ ሌሎች የአካባቢዋ ወጣት ልጃገረዶች ለግል ሕይወት እንደሚጨነቁ ሁሉ ከእጮኛዋ ከዮሴፍ ጋር የነበራትን ግንኙነት ለማጠናከር ያልተጨነቀችው? ቅድስት ድንግል ማርያም ጥሪው ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ ልዩ ጥሪ መሆኑን በተረዳች ጊዜ ራሷን የእግዚአብሔር አገልጋይ መሆኗን ይፋ ለማድረግ ወይ ለማሳወቅ ወደ ኋላ አላለችም  “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች (ሉቃ. 1፡38)። በዚህ የተነሳ ከእርሷ የሚወለድ ሕጻን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅነቱን ለዓለም ይገልጻል። ታላቅነቱን የሚገልጸው ከማርያም በመወለዱ፣ ወይም በእርሷ እናትነት ሳይሆን ከሁሉም በላይ ማርያም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽማ ስለተገኘች ነው። ኢየሱስም እንዲህ አለ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው” አለ (ሉቃ. 11፡28) እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም ማለት ነው። ቅድስት ማርያም በሕይወቷ እየሆነ ያለውን ነገር በሚገባ ሳትረዳው ስትቀር በዝምታ በማሰላሰል፣ ለመለኮታዊ ሃይል ሥራ አድናቆቷን ታሳይ ነበር። በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሥር መገኘቷ ራሷን ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ማስገዛቷን ያረጋግጣል።

ቀጥሎም እጮኛዋ ዮሴፍን ስንመለከት፣ ቅዱስ ወንጌል አንዳች ነገር ስለ ዮሴፍ ባይነግረንም እርሱ የሚሆነውን ሁሉ እየተመለከተ መታዘዝን ብቻ መምረጡን እንገነዘባለን። እርሱ ዝምታን የሚመርጥ፣ መታዘዝን ብቻ የመረጠ መሆኑን እንመለከታለን። ዛሬ ከማቴ. 2፡ 13-15 እና ከ19-23 የተነበበው ቅዱስ ወንጌል የዮሴፍን ታዛዥነት ሥስት ጊዜ ያረጋግጥልናል። የመጀመሪያው ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግብጽ ምድር መሰደዱን፣ ቀጥሎም ከግብጽ ወደ እስራኤል ምድር መመለሱን ይነግረናል። ጥበቃ እንዲደረግለት ከእግዚአብሔር ዘንድ በተላከው ቅዱስ መልአክ በመመራት ቤተሰቡን ወደ ወደ ሩቅ አገር በመውሰድ ከሄሮድስ ጥቃት ሊያድን ችሏል። ይህን ክስተት በጥልቀት ስንመለከት ዛሬ በዘመናችን፣ በርካታ ቤተሰቦች ላይ የደረሰውን እና በመድረስ ላይ ያለውን የስደት ሕይወት የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብም መጋራቱን እንመለከታለን። የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ፣ በዓለማችን በአመጽ፣ በጦርነት፣ በተለያዩ የጭቆና አገዛዝ ምክንያት መኖሪያቸውን ለቅቀው ከሚሰደዱት ቤተሰቦች ጋር መሆናቸውን እንረዳለን።

በመጨረሻም ሦስተኛው የቅዱስ ቤተሰብ አባል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጸመበት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው ሁለተኛ መልዕክት እንደሚነግረን “ምክንያቱም እኔም ሆንሁ ሲላስና ጢሞቴዎስ፣ እኛ የሰበክንላችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አዎን’ እና ‘አይደለም’ አልነበረም፤ ነገር ግን በእርሱ ዘወትር፣ ‘አዎን’ ነው” በማለት የእግዚአብሔር ፈቃድ በእርሱ መገለጡን ይገልጽልናል።(2ቆሮ. 1፡19) የእግዚአብሔር ፈቃን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ውስጥ መገለጹን በተደጋጋሚ እናያለን። ከእነዚህም መካከል ጠፍቶባቸው በመጨነቅ ሲፈልጉት ለነበሩት ማርያም እና ዮሴፍ፣ ባገኙትም ጊዜ ለምን እንዲህ እንዳደረገ በጠየቁት ጊዜ እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። (ሉቃ. 2፡49) በዮሐ. 4፡34 ላይም “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው በማለት መለሰላቸው። በማቴ. 26፡42 ላይም “አባት ሆይ፤ ይህ ሳልጠጣው የማያልፍ ጽዋ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይፈጸም” ብሎ ጸለየ።

እነዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት ወይም ንግግሮች በሙሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ በእርሱ ፍጻሜን ማግኘቱን ያረጋግጣሉ። ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ ብሏል፤ “መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም፤ ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሚቃጠል መሥዋዕትና ለኀጢአት በሚቀርብ መሥዋዕት ደስ አልተሰኘህም። በዚያን ጊዜ እንዲህ አልሁ፤ ‘ስለ እኔ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈ፣ አምላክ ሆይ፤ እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ”። (ዕብ. 10፡5-7) እንደዚሁም  “እነሆ፤ መጥቻለሁ፤ ስለ እኔ በመጽሐፍ ተጽፎአል፤ አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ።” በታላቅ ጉባኤ ውስጥ ጽድቅን አበሠርሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ እንደምታውቀው፣ ከንፈሮቼን አልገጠምሁም። (መዝ. 40፡ 7-9)

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቅዱስ ዮሴፍ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱም የእግዚአብሔር ፈቃድ በግልጽ የተፈጸመባቸው የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተስብ አባላት ናቸው። ሦስቱም የእግዚአብሔር ፈቃድ በእነርሱ በኩል እንዲገለጽ አንዱ ለሌላው እገዛን አድርገዋል። ይህንንም በጸሎታቸው፣ በዕለታዊ ሥራዎቻቸው እና ባሳዩት የሕይወት ምስክርነት ገልጸዋል። ለመሆኑ ስንቶቻችን በቤተሰብ መካከል እርስ በእርስ በመነጋገር እና በመመካከር ራሳችንን መግለጽ እንችላለን። ወይም ብዙዎች እንደሚያደርጉ በገበታ ዙሪያ ለመግብ ተቀምጠው በስልክ ከጓደኞቻቸው ጋር እንደሚገናኙ ሰዎች ነን። በዚያ ቤተሰብ መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነት የለም፣ በዚያ ቤተሰብ መካከል ጸጥታ እንጂ የቃላት ልውውጥ የለም። በቤተሰብ መካከል ውይይት፣ ንግግር ሊኖር ይገባል። የቤተሰብ አባል የሆኑት በሙሉ፣ እናት፣ አባት፣ አያት ልጅ፣ እህት ወንድም እርስ በእርስ መነጋገር፣ መወያየት፣ መመካከር ይኖርባቸዋል። የናዝሬቱን ቅዱስ ቤተሰብ በምናስታውስበት በዛሬው ዕለት ማስታወስ ያለብን ቀዳሚ ተግባር በቤተሰብ መካከል መወያየት፣ መረዳዳት እና መመካከር እንዲኖር ማድረግ ነው። ለዚህም ዋና ምሳሌ የሚሆነው የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ በመሆኑ እገዛውን እንለምናለን”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች መልካም ምኞታቸውን ገልጸው በዕለቱ ያቀረቡትን ስብከተ ወንጌል ከማጠቃለላቸው በፊት፣ የቤተሰብ ንግሥት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በችግር ላይ ለሚገኙት ቤተሰቦች ረዳታቸው እንድትሆን፣ የእርሷ ጥበቃ ዘወትር እንዳይለያቸው በጸሎታቸው ተማጽነው የዕለቱን ስብከታቸውን ፈጽመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

30 December 2019, 16:48