ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ማርያም ፊት በማቅረብ ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ማርያም ፊት በማቅረብ ላይ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለእስያ ሐዋርያዊ ጉዟቸው መሳካት የእመቤታችን ማርያም ድጋፍ ተማጸኑ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኅዳር 9-16/2012 ዓ.ም ድረስ በሁለት የሩቅ ምሥራቅ እስያ አገሮች በታይላንድ እና ጃፓን የሚያደርጉት 32ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት የተሳካ እንዲሆን ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ አቅርበዋል። ከዚህ በፊትም ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድመው በሮም ከተማ በሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ በመሄድ ጸሎት የሚያደርሱ መሆናቸው ይታወቃል። ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ቫቲካን ከመግባታቸው አስቀድመው ወደ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ባዚሊካ በመሄድ የምስጋና ጸሎት እንደሚያቀርቡ ይታወቃል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ህዳር 9/2012 ዓ. ም. ወደ ታይላንድ እና ጃፓን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት በቲዊተር ገጻቸው በኩል ለታይላንድ እና ለጃፓን ህዝቦች በላኩት የወዳጅነት መልዕክታቸው፣ በሁለቱም አገሮች የሚያደርጉት የሐዋርያዊ ጉብኝት ቆይታ በእግዚአብሔር ጸጋ እና ደስታ የተሞላ እንዲሆኑ ጸሎታችንን እናቅርብ ብለዋል። 

ለሮም ከተማ ሕዝብ አዳኝ እመቤታችን የሚቀርብ ጸሎት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጸሎታቸውን ለማቅረብ ወደ ባዚሊካው ሲሄዱ እቅፍ አበባ በመያዝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን አቅፋ በምትታይበት ጸሎት ቤት ውስጥ የሚያኖሩ መሆኑ ታውቋል። የሮም ከተማ ሕዝብ ከአቅሙ በላይ የሆነ መቅሰፍት በወረደበት ጊዜ እጁን ዘርግቶ ሲጸልይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመገልጥ እንዳገዘቻቸው፣ ለሰው ልጆች የማይቻል ለእግዚአብሔር የሚቻል መሆኑን በማመን የሮም ከተማ ሕዝብ ለበርካታ ዘመናት ወደ እመቤታችን ባዚሊካ በመሄድ ለረዳታቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎት የሚያቀርብ መሆኑ ይታወቃል።

በሮም ከተማ በሚገኝ እመቤታችን ባዚሊካው ውስጥ ያለው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት እና ኢየሱሳዊያን የሚያከብሩት እና የሚወዱት ነው። ከዚህ በፊት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን የመሩት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ባዚሊካው ሲሄዱ ጸሎታቸውን የሚያቀርቡት እንዲሁም የኢየሱሳዊያን ማሕበር መስራች የሆነው ቅዱስ ኢግናሲዮስ የክህነት ማዕረግ ከተቀበለ በኋላ የመጀመሪያውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ያቀረበው በዚህ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል ፊት መሆኑ ይታወሳል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1950 ዓ. ም. የእመቤታችንን ፍልሰታ በቤተክርስቲያን ዶግማ ባጸደቁበት ወቅት ወደ እመቤታችን ባዚሊካ ሄደው ጸሎት ማድረሳቸው ይታወሳል። የሰዎችን ልመና ወደ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የምታደርስ እናት መሆኗን ወጣቶች በሚገባ እንዲያውቁ በማለት በ2000 ዓ. ም. የኢዮቤልዩ ዓመት በተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በእመቤታችን ባዚሊካ የሚገኘውን የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቅዱስ ምስል እና ቅዱስ መስቀል ለወጣቶች በስጦታ ማበርከታቸው ይታወሳል። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከዚህም በተጨማሪ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካላቸው ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ በባዚሊካው ውስጥ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል ፊት ቀን እና ሌሊት ሳይጠፋ የሻማ መብራት እንዲበራ ማዘዛቸውም ይታወሳል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
19 November 2019, 17:35