ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጉባኤው ተካፋዮች ጋር ሆነው፣                                            ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጉባኤው ተካፋዮች ጋር ሆነው፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “በቤተክርስቲያን ዜማ በመታገዝ በታላቅ ደስታ ወንጌልን ለሌሎች እንግለጽ”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ጥቅምት 29/2012 ዓ. ም. የቤተክርስቲያን የዜማ አገልግሎትን እና ትርጉምን አስመልክቶ በተዘጋጀው ሦስተኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ለተገኙት አባለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ጉባኤውን ያዘጋጁትን በቅድስት መንበር የእምነት ባሕል የሚከታተል ጳጳሳዊ ምክር ቤትን እና የአምልኮ ስርዓት እና የዜማ አገልግሎት አስተባባሪ የሆነውን የቅዱስ አንሴልሞ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትን አመስግነዋል። ቅዱስነታቸው እነዚህን የቤተክርስቲያን አገልግሎቶች ማሳደግ በሚቻልበት መንገድ ላይ መወያየት አስፈላጊነቱ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል። ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎቻች ከዚህ በታች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች ያስተላለፉትን መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተን አቅርበንላችኋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!

“ቤተክርስቲያን፣ የዜማ አገልግሎት እና ተርጓሚዎች” በሚል ርዕሥ በተዘጋጀው ሦስተኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ለተገኛችሁ በሙሉ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የከበረ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ይህን ስብሰባ በንግግር ለከፈቱት ለብጹዕ ካርዲናል ራቫዚ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ጉባኤውን ያዘጋጁትን በቅድስት መንበር የባሕል ጉዳይ የሚከታተል ጳጳሳዊ ምክር ቤትን እና የቤተክርስቲያን አምልኮ ስርዓትን እና ዜማ አገልግሎት አስተባባሪ የሆነውን የቅዱስ አንሴልሞ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትን ላመሰግን እወዳለሁ። በእነዚህ ቀናት ውስጥ ሰፊ ውይይት በማድረግ ልምድ የተለዋወጣችሁባቸው የወንጌል አገልግሎት ልምድ፣ የቤተክርስቲያን የስርዓተ አምልኮ ሕይወት እና የአገልግሎት ባሕል ለእያንዳንዳችሁ ጥሩ ማነቃቂያ እንደሆናችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።

ብዙን ጊዜ አስተርጓሚን የትርጉም አገልግሎት የሚሰጥ፣ እርሱ የተረዳውን ሌሎችም መረዳት በሚችሉበት መንገድ አዘጋጅቶ የሚያቀርብ ሰው እንደሆነ እንገነዘባለን። በተለይ በቤተክርስቲያን የዜማ አገልግሎት ዘርፍ የተመለከትን እንደሆነ፣ የዜማ ደራሲው የስነ አርት ጥበብን በመከተል፣ ተደማጭነት እና ውበት እንዲኖረው በማድረግ የጻፈው የዜማ ድርሰት የጥበብ ስልትን እና ልምድን ተከትሎ ትክክለኛውን ትርጉም መስጠትን ይመለከታል።

የተዋጣለት የስነ ጥበብ ተርጓሚ የሚባል አንድ ሰው የራሱ የሥራ ውጤት ባልሆኑ የሌሎች የጥበብ ሥራ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ያለው እና ክብርንም የሚሰጥ ነው። ጎበዝ የሚባል የዜማ ተርጓሚ ለሌሎች የዜማ ሥራ የግል አድናቆትን እና ክብርን የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ዜማ በመንፈሳዊ ይዘቱ የምዕመናንን መንፈስ በመቀስቀስ፣ ለክርስቲያናዊ ሕይወት ማደግ እገዛን የሚያደርግ እና የሚያንጽ፣ ለስርዓተ አምልኮ አገልግሎትም ከፍተኛ እገዛን የሚሰጥ መሆኑን ከልብ የተገነዘበ መሆን ይኖርበታል። በዚህ ሁኔታ እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ዜማ ተርጓሚ ለዜማ ትርጉም ያለውን የጥበብ ችሎታ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ፣ መንፈሳዊ ዜማ ከሁሉ አስቀድሞ የምዕመናንን የጸሎት ሕይወት ለማነቃቃት እና ለመላው የክርስቲያን ማሕበርሰብ አገልግሎት የተሰጠ መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል። የቤተክርስቲያን ዜማ ተርጓሚ እነዚህን መመሪያዎች በብቃት ተግባራዊ ማድረግ የሚችለው በቤተክርስቲያን የስርዓተ አምልኮ አገልጎሎት ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ ከሆነ ነው።

የቤተክርስቲያን ዜማ ተርጓሚ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ በአገልግሎታቸው የሚገናኙባቸው ብዙ መንገዶ አሉ። ከመንገዶቹ መካከል አንዱ የእግዚአብሔርን መልካም ዜና የማወጅ አገልግሎት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪም በዘመናት የሚታዩትን ምልክቶች በጽሞና ልብ ተመልክቶ ትክክለኛውን ትርጉም መስጠትን ያጠቃልላል። በስፋት ያየን እንደሆነ በዘመናችን የሚታዩትን ምልክቶች መመልከት መቻል ለተወሰኑት ሰዎች ብቻ የተሰጠ ችሎታ ሳይሆን እያንዳንዱ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሕይወቱ ወስጥ ለመረዳት ልብን ክፍት በማድረግ፣ ካወቀም በኋላ የደስታ ዜማን በማዜም ለእግዚአብሔር ምስጋናን እና ውዳሴን የሚያቀርብ መሆን አለበት። በዚህ የክርስቲያኖች የምስጋና እና የውዳሴ ዜማ በመታገዝ ቤተክርስቲያን በዘመናት ሁሉ የወንጌልን መልካም ዜና ለእግዚአብሔር ህዝብ የመግለጽ ጥበብን ታሳድጋለች።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይገለጽ ዘንድ የምስጋና ዜማን በማቅረብ ምሳሌ ሆናለች። ቅዱሳንም እንደዚሁም የእግዚአብሔርን ፈቃድ በተሰማሩበት የሕይወት ተልዕኮዋቸው በኩል በገሃድ እንዲገለጽ አድርገዋል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ1964 ዓ. ም. ከስነ ጥበብ ሰዎች ጋር በተሰበሰቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክታቸው “እንደምታውቁት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እና እቅድ በማያሻማ እና ግልጽ በሆነ መንገድ፣ በቀላሉ ሊያገኙት በሚቻልበት መንገድ ለምዕመናን ማቅረብ ነው፣ በዚህ አገልግሎታችሁ በመታገዝ ለሌሎች ተሰውሮ የቆየውን ይህን ዓለም ግልጽ በማድረግ ጥበብ ተክናችኋል። ለእናንተ የተሰጠው የአገልግሎት ጥሪ፣ ተልዕኮ እና ጥበብም እነዚህን ከሰዎች አእምሮ ተሰውረው የቆዩትን የዘመኑን ምልክቶች ለተመልካች ወይም ለአድማጭ በሚገቡ ቃላት፣ ቀለማት እና ቅርጽ አዘጋጅቶ ማቅረብ ነው” በማለት ማሳሰባቸው ይታወሳል። በዚህ ዓይነት አካሄድ የቤተክርስቲያን ዜማ ተርጓሚዎችም ሌሎች የስነ ጥበብ ሰዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ የማያቋርጥ ውክልና  የያዘውን የ“ቅዱሳት ምስጢራትን” ትርጉምን በቀላሉ ማስተላለፍ የሚችሉ ቃላትን በመጠቀም ለሌሎች ማስተላለፍ ነው።

የመንፈሳዊ ዜማ አገልግሎትን በተመለከተ የስነ ጥበብ ሰው፣ የዜማ ትርጓሚ እና የዜማ አድማጭ በሙሉ አንድ ዓይነት የሆነ ተመሳሳይ ፍላጎት አላቸው። ይህ ፍላጎታቸውም እግዚአብሔርን እና ሥራዎቹን ማወቅ የምንችልባቸውን መንፈሳዊ ዜማ ውበት በልባችን ውስጥ ማኖር ነው። እንደሚመስለኝ ከምን ጊዜ በላይ ሰዎች በሙሉ ይህን ጥበብ በሚገባ ለመረዳት ፍላጎት አድሮባቸዋል። የጊዜውን ሁኔታ፣ የዘመኑን ምልክቶች ተረድቶ ትክክለኛውን ትርጉም መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በዚህ ዙሪያ ብዙ ጊዜን በመስጠት በቤተክርስቲያን የዜማ አገልግሎት እና በአምልኮ ስርዓት ላይ ላደረጋችኋቸው ሰፊ ውይይቶች አሁንም በድጋሚ ላመሰግናችሁ አውዳለሁ። የእኔ ምኞትም እያንዳንዳችሁ በአገልግሎታችሁ አማካይነት ቅዱስ ወንጌልን በግልጽ የማብራራት ችሎታችሁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲመጣ ነው። እግዚአብሔር አብ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የገለጠልንን የወንጌል መልካም ዜና ለሌሎች መመስከር የሚያስችላችሁ ጥበብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያድግ እና በጥበብ በመታገዝ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ምስጋና በዝማሬ ማቅርብ፣ የእርሱን አባትነት በዝማሬ የመመስከር ብቃት እንዲኖራችሁ ነው። ይህን ጉባኤ ለተካፈላችሁት በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬዬን በመስጠት በጸሎታችሁ እንድታስታውሱኝ አደራ እላለሁ”።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
09 November 2019, 16:25