ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከኢየሱሳውያን ማሕበር ጠቅላይ አለቃ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጥ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከኢየሱሳውያን ማሕበር ጠቅላይ አለቃ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጥ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለማሕበራዊ ፍትሕ እና ስነ ምህዳር ጽ/ቤት ተወካዮች መልዕክት አስተላለፉ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኢየሱሳውያን ማሕበር ሥር የማሕበራዊ ፍትሕ እና ስነ ምሕዳር ጽሕፈት ቤት የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ለተገኙት የጽሕፈት ቤቱ አባላት ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። ዛሬ ጥቅምት 27/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ለተገኙት የጽሕፈት ቤቱ አባላት ሰላምታቸውን በማቅረብ ንግግራቸውን ያሰሙት ቅዱስነታቸው፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙት ዓለም አቀፍ የገዳማውያን ማሕበራት መካከል አንዱ የሆነው የኢየሱሳውያን ማሕበር በቅዱስ ኢግናጢዮስ መስራችነት የተጀመረው ድሆችን ለማገልገል መሆኑን አስታውሰው የኢየሱሳውያን ማሕበር ዓባላት ዓላማ፣ የማሕበሩ መስራች እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1550 ዓ. ም. ባዘጋጀው ደንብ መሠረት እምነትን በመጠበቅ፣ ነፍሳት በእምነት የሚያድጉባቸውን ክርስቲያናዊ አስተምሕሮችን ማዳርስ መሆኑን አስታውሰዋል። በዘመኑ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ጁሊየስ 3ኛ በጎርጎሮሳዊው ሰኔ 21/1550 ዓ. ም. ያጸደቁት የኢየሱሳውያን ማሕበር ሰዎችን ለማስታረቅ፣  በእስር ቤቶች እና ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች በታማኝነት ለማገልገል የተመሰረተ ማሕበር መሆኑን አስታውሰዋል። ለማሕበሩ አባላት እነዚህን አገልግሎቶች ማቅረብ እንግዳ አልነበረም ያሉት ቅዱስነታቸው አስቀድሞም ቢሆን ከእግዚአብሔር የተቀበሉት የአገልግሎት ጥሪ መሆኑን አስረድተዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የማሕበሩ አባል በነበሩት በአባ አሩፔ በኩል ተጨማሪ ጥንካሬ እንዲደረግለት በቀረበው ሃሳብ አንዳንድ ማሻሻያዎች ቢደረጉም የማሕበሩ ዓላማ እና አገልግሎት ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ ተመሳሳይ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውቀዋል። “በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን፣ የስቃይ ጩሄት የሚያሰሙትን፣ ተረስተው እና ረዳት አጥተው በብቸኝነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙን እንዳገለግል የሚያደርገኝን እግዚአብሔር ሳስላየሁ ድሆችን ማገልገል እፈልጋለሁ” በማለት የማሕበሩ አባል የነበሩ አባ አሩፔ ጽፈው ያስቀመጡትን መልዕክት ቅዱስነታቸው ለጉባኤው ተካፋዮች አስታውሰዋል።

ሰዎች እንዲናቁ እና እንዲገለሉ የሚያደርግ ባሕል ላይ መድረሳችንን እንገነዘባለን ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የዚህ ባሕል ሰለባ የሆኑ በርካታ ሰዎች በመኖራቸው፣ እንድናስታውሳቸው እና እንድንራራላቸው የቻልነው በጸሎት ሃይል እንደሆነ አስረድተው የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባል የነበሩት አባ አሩፔ የጸሎት ሰው መሆናቸውን ገልጸዋል።   

በጋራ መኖሪያ በሆነው ዓለማችን ውስጥ ስንገኝ ፈውስ እና ዘለዓለማዊ ድነት የተገኘበትን የቅዱስ መስቀል ምስጢር ማስታወስ ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባላትም ሕይወታቸውን እስከ መጨረሻ ድረስ ድሆችን፣ የተጨቆኑትን እና ፍትሕ የጠማቸውን ሰዎች ለማገልገል እንዲያውሉት ጠይቀዋል።

በዓለማችን የሚታዩ በርካታ ኢፍትሃዊነት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች ባስተላለፉት መልዕክታቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል በከፍተኛ ስቃይ ላይ የሚገኙትን የዓለማችን ድሆች መርዳት እና ማሕበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ማሕበራዊ ችግሮቻችን ከሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጀምሮ ሰዎችን እስከ መጥላት እና በፍርሃት የተነሳ እስከ ማግለል ይደርሳል ያሉት ቅዱስነታቸው የጋራ መኖሪያ በሆነች አንድ ዓለማችን ውስጥ እየኖርን በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ላይ ስቃይ ሲደርስባቸው እናያለን ብለዋል። 

የሕዝብ ሐዋርያዊ አገልጋይ ማሕበራዊ ችግሮችን ለማቃለል ድህነትን ለመቀነስ ቢጠራም ድህነትን መቀነስ በቅድሚያ የድሆች ተነሳሽነት ካለ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው በጎርጎሮሳዊያኑ 2015 ዓ. ም. በቦሊቪያ የሚገኙትን ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እነዚህ እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን በማደራጀት፣ በማሕበረሰቡ መካከል የደሄዩትን ለመርዳት የተቋቋሙ እውነተኛ እንቅስቃሴዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

07 November 2019, 17:28