ር. ሊ. ጳ  ፍራንችስኮስ በጃፓን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጃፓን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት፣ 

የር. ሊ. ጳ ፍራንቸስኮስ የ31 ዙር ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ታሪክ በአጭሩ።

በትውልድ አርጄንቲናዊ የሆኑት ካርዲናል ጆርጅ ማሪዮ በርጎሊ በመጋቢት 13/2013 ዓ.ም. 266ኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው በተመረጡበት ወቅት በ13ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው እና የድኾች አባት በመባል የሚታወቀው፣ እንዲሁም የፍራንችስካዊያን ማሕበር መስራች የነበረው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ፣ በሕይወቱ ዘመን ለድኾች ባሳየው ትህትና፣ ክብር፣ ፍቅር እና ልገሳ እርሳቸው በጣም ከሚያደንቁዋቸው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቅዱሳን መካከል አንዱ በመሆኑ የተነሳ፣ እርሳቸውም የቅዱስ ፍራንቸስኮስን አብነት በመከተል በጵጵስናቸው ዘመን ለድኾች፣ ለስደተኞች፣ እንዲሁም በዝቅተኛ ደረጃ ለሚኖሩ የማሕበረሰብ ክፍሎች፣ በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ እኩልነት እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ይሰፍን ዘንድ በማሰብ የቅዱስ ፍራንቸስኮስን ስም የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስናቸው ዘመን መጠሪያ እንዲሆን በማድረግ ፍራንቸስኮስ የሚለው ስም መጠሪያቸው እንዲሆን መምረጣቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃይለ ጊዮርጊስ - ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ በአራት አመት ውስጥ ብቻ ከጣሊያን ውጭ 21 ሐዋርያው ጎብኝቶችን ማድረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን በእነዚህ ሐዋሪያዊ ጎብኝታቸው ደግሞ በርካታ የካቶሊክ ምዕመናን ከሚገኙባችን የዓለማችን ክፍሎች አንስቶ እስከ 900 ያህል የካቶሊክ ምዕመናን ብቻ የሚገኙባትን አዘረበጃን ድረስ በመሄድ የሰላም እና የእርቅ መልእክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ከጣሊያን ውጪ የመጀመሪያውን ሐዋሪያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ብራዚል ነበር ያቀኑት። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከሐምሌ 22-29/2013 ዓ. ም. ድረስ በብራዚል ዋና ከተማ ሪዮ ዲ ጄነይሮ  28ኛው የዓለም የካቶሊክ ወጣቶች ቀን በተከበረበት ወቅት የመጀመሪያውን ሐዋሪያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደ ብራዚል ማቅናታቸው ይታወሳል። በጉብኝታቸውም ወቅት በወቅቱ የብራዚል ርዕሰ ብሔር በነበሩት በዲልማ ሩውሴፍ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በወቅቱም በብራዚል ኮፓካባና በተባለ ሥፍራ በሚገኘው ውብ በሆነ የባሕር ዳርቻ አመሻሹ ላይ ለተሰበሰቡት 3.5 ሚልዮን ወጣቶች ባደርጉት የመጀመሪያው ንግግር ወጣቶች part-time Christains "ሲመቻቸው ብቻ ክርስቲያን የሚሆኑ፣ ሳይመቻቸው ሲቀር ከቤተክርስቲያን የሚጠፉ” ወይም ደግሞ ገሚሱን ሕይወታቸውን ለዓለም፣ ገሚሱን ደግሞ ለቤተክርስቲያን የሚሰጡ ክርስቲያኖች ዓይነት መሆን እንደ ሌለባቸው አሳስበው፣ ወጣቶች ሙሉ ትርጉም ያለውን ሕይወት እንዲመሩ አደራ ማለታቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሁለተኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከግንቦት 24-26/2014 ዓ.ም. ድረስ ለማድረግ ወደ እስራኤል፣ ዮርዳኖስ እና ፍልስጤም ማቅናታቸው ይታወሳል። በዚህ የሦስት ቀን ጉብኝታቸው ወቅት በቅድሚያ ከዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላህ ሁለተኛ ጋር ከተገናኙ በኋላ በአማን በሚገኘው ዓለም አቀፍ ስታዲዬም ለተሰበሰቡ ምዕመናን መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል። ወደ እስራኤል በማቅናት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስተር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር ከተገናኙ በኋላ በምእራብ ጋዛ የሚገኘውን በተለያዩ የአሸባሪዎች ጥቃት ነፍሳቸውን ያጡ ሰዎች የተቀበሩበትን የመታሰቢያ ሐውልት ጎብኝተዋል። በእስራኤል፣ በዮርዳኖስ እና በፍልስጤም ያደርጉትን 2ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያጠናቀቁት ከፓትሪያርክ ቤርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ ጋር ከተገናኙ በኋላ ሲሆን በግንኙነታቸውም ወቅት በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም በኦሮቶዶክስ እና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያንት መካከል ያለውን ግንኙነት በውይይት ለማጠናከር ከተስማሙ በኋላ እንደ ነበረ ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ሦስተኛውን ሐዋሪያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከሐምሌ 14-18/2014 ዓ.ም. ለማድረግ ወደ ድቡብ ኮሪያ ማቅናታቸው ይታወሳል።  ቅዱስነታቸው በደቡብ ኮሪያ እንደ ደረሱ በወቅቱ የሀገሪቷ ርዕሰ ብሔር በነበሩት ፓርክ ጌሁን-ሄይ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በወቅቱ በሴዎል በሚገኘው ብሔራዊ ቤተመንግሥት ለተሰበሰቡ የሀገሪቷ ባለስልጣናት ባደረጉት ንግግር “እኔ ወደ ደቡብ ኮሪያ የመጣሁት በኮሪያን ባሕረ-ሰላጤ ሰላም እና ዕርቅ ይወርድ ዘንድ እንድታስቡ፣ የበኩላችሁንም ጥረት እንድታደርጉ ነው” ብለው እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን በዚሁ የአምስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ በወቅቱ በሴዎል ይከበር በነበረው 6ኛው የእስያ አህጉር የካቶሊክ ወጣቶች ቀን ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል። ከ50,000 በላይ የሚገመቱ ወጣቶች በተገኙበት ስፍራ ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ወጣቶች “ድህነትን የሚያስከትሉ እና ሥራ አጥነትን የሚያባብሱ አዳዲስ ኢሰብዓዊ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ-ሐሳቦችን መቃወም እንደ ሚገባቸው” አበክረው ማሳሰባቸው ያታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ አራተኛውን ሐዋሪያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በመስከረም 21/2014 ዓ.ም ለማድረግ የአልባኒያ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ቲራና የአንድ ቀን ሐዋሪያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደዚያው ባቀኑበት ወቅት በአልባኒያው ርዕሰ ብሔር ቡጃር ኒሻኒ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው እንደ ነበረ ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደርጉት ንግግር "በዚህ አጠር ያለ ጉብኝት የአልባንያ ቤተክርስቲያንን በእምነት ለማጠናከር እና ሕዝቡ ባለፉት ስርዓቶች ለነበረው ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ አልበግርም ማለቱን ለማድነቅ እና ለዚሁም ምስክርነቴን ለመስጠት ነው እዚህ የተገኘሁት” ማለታቸው ያታወሳል።

አምስተኛውን ሐዋሪያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በኅዳር 25/2014 ለማድረግ ወደ ፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ማቅናታቸው ያታወሳል። በዚያው የነበራቸው ጊዜ የአራት ሰዓት ቆይታ እንደ ነበር የተገለጸ ሲሆን ከዚያም በኅዳር 25/2014 ዓ. ም. በወቅቱ በፈረንሳይ ስትራስቡርግ ተብሎ በሚጠራው ከተማ ይካሄድ የነበረውን የአውሮፓ ፓርላማ ስብሰባ መካፈላቸው ይታወሳል። በአውሮፓ ፓርላማ ጉባኤ ላይ ባደርጉትን ንግግር በስደተኞች ላይ የሚደርገው ኢሰባዊ ድርጊት እንዲቆም መስራት እንደ ሚገባቸው አበክረው ገልጸው፣ ለሰራተኞች የተሻለ የሥራ ሁኔታ እንዲፈጥሩ እንዲሁም ሥራ አጥነትን ለመቀረፍ እንዲሰሩ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ስድስተኛውን ሐዋሪያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከኅዳር 28-30/2014 ዓ. ም. ወደ ቱርክ ዋና ከተማ እስታንቡል መሄዳቸው የሚታወስ ሲሆን በዚያም በቱርኩ ርዕሰ ብሔር፣ ሴጵ ጣይፕ ሄርዶጋን በብሔራዊ ቤተመንግሥት ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ያታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ባደርጉት ንግግር ቱርክ የአክራሪነት ጽንሰ-ሐሳቦችን ለመቃወም በተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መካከል ውይይት ይደረግ ዘንድ መንገዱን መክፈት እንደሚገባት መናገራቸው ሲታውስ በተጨማሪም በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ይፈጠር ዘንድ ቱርክ የበኩሏን ሚና እንድትጫወት አደራ ማለታቸው ይታወሳል። ከዚያም የቁስጢንጢንያው ፓትሪያርክ በርቴሎመዎስ ቀዳማዊ በተገኙበት መስዋዕተ ቅዳሴን ካሳረጉ ቡኃላ ወደ ቫቲካን መመለሳቸው ይታወሳል።

ሰባተኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከጥር 13-19 /2015 ዓ.ም. ሲሪላንካን እና ፊሊፒንን በቅደም ተከተል ለመጎብኘት ወደዚያው ማቅናታቸው ይታወሳል። ከጥር 13-15/2015 ዓ.ም. በስሪላንካ ቆይታ አድርገው በዚያ የሚገኙትን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያ ስም የተሰየሙትን ሁለት ታላላቅ የተቀደሱ የንግደት ሥፍራዎችን መጎብኘታቸው ያታወሳል። ቅዱስነታቸው በመቀጠል ወደ ፊሊፒን አቅንተው ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጎርጎሮሳዊያኑ 1970 ዓ. ም. በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ በመቀጠልም እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 1981 ዓ. ም. እና 1995 ዓ. ም. በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን ተከትለው በፊሊፒንስ ሐዋሪያዊ ጉብኝት ያደረጉ ሦስተኛው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መሆናቸው ታውቋል። ይህ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በፊሊፒንስ ያደረጉት ስድስተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዓለም ዙሪያ እስካሁን ድረስ ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ሁሉ በታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራን የሚሰጠው ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት በወቅቱ እርሳቸው በማኒላ ያደርጉትን ንግግር እና ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ ለመከታተል ከ6-7 ሚልዮን የሚጠጋ ሕዝብ በስፍራው በመታደሙ የተነሳ ነው ተብሏል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ስምነተኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ ሰኔ 6/2015 ዓ.ም. ወደ  ቦሲኒያ ሄርዘጎቪና ማቅናታቸው ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ዘጠነኛውን ሐዋሪያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከነሐሴ 5-13 /2015 ዓ.ም. ለማድረግ ወደ ቦሊቪያ፣ ኤኳዶር እና ፓራጉዋይ በቅደም ተከተል አቅንተው ነበር። በቅድሚያ በቦሊቪያ ባደርጉት ጉብኝት በርዕሰ ብሔሩ ሄቮ ሞራሌስ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባደርጉት ንግግር መንግሥት ሙስናን እንዲዋጋ፣ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ኢኮኖሚያዊ ስርዓት እዲገነባ ጥረት እንዲደረግ፣ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ያታወሳል።

በመቀጠልም በኤኳዶር ባደርጉት ጉብኝት በሀገሪቷ ርዕሰ ብሔር ራፋሔል ኮሬአ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር። ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደርጉት ንግግር “ኤኳዶር እያስመዘገበች ያላችውን ከፍተኛ  ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደ ሚያደንቁ ገልጸው ሕገመንግሥታችሁ፣ የሁሉንም ዜጋ መብት የሚያስከብር፣ የተፍጥሮ ሐብት እንዲጠበቅ የሚያስገድድ የተለያዩ የሲቪል ማህበራት በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ የሚያበረታታ መሆኑን በማውሳት አድናቆታቸውን መግለጻቸው ያታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ አስረኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ ከመስከረም 19-27/2015 ዓ.ም. ለማድረግ ወደ ኩባ እና ከእዚያም በመቀጠል ወደ ሰሜን አሜሪካ መጓዛቸው ይታወቃል። በኩባ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር በሀቫና ቆይታ አድርገው የነበረ ሲሆን፣ በሀገሪቷ ከሚገኙ የካቶሊክ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግል እና ምዕመናን ጋር ተገናኝተው በጋራ ጸሎት ማድረጋቸው ይታወቃል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በመስከረም 23/2015 ዓ.ም. ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በማቅናት በዚያ በወቅቱ የአሜሪካ ርዕሰ ብሔር ከነበሩት ባራክ ኦባማ ጋር በዋይት ሀውስ መገናኘታቸው ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዋይት ሀውስ ያደርጉት ጉብኝት ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1979 ዓ.ም. በወቅቱ የአሜርካ ርዕሰ ብሔር በነበሩት ጂሚ ካርተር እና በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ፣ ቀጥሎም በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2008 ዓ.ም. በወቅቱ የአሜሪካ ርዕሰ ብሔር በነበሩት በጆርጅ ደብሊዩ ቡሽ እና በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት በነዲክቶስ 16ኛ ጋር ከተደርገው ግንኙነት በመቀጠል በሦስተኛነት ዋይት ሀውስ የጎበኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መሆናቸውን ታሪክ ያስረዳል።  

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በወቅቱ በአሜሪካ ኮንግረስ ፊት በመቅረብ ንግግር ማድረጋቸው ሲታወስ በወቅቱ ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት የእናንተ ተግባር ልክ ሙሴ ለእስራኤላዊያን ሕዝብ ያደርገውን ዓይነት ተግባር እንዲሆን ይገባል ማለታቸው ይታወሳል። በመጀመሪያ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ በበረሃ አንድነታቸውን ተጠብቆ፣ የሚበሉትን እና የሚጠቱትን እንዳያጡ ተንከባክቦ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደ መራቸው ሁሉ እናንተም በተመሳሳይ መንገድ ሕዝባችሁን በሙሉ በአንድነት እና በሰላም መምራት ይኖርባችኋል ብለው ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ አንድነት ጠብቆ፣ የሚበሉትን እና የሚጠቱትን እንዳያጡ መከባከብ ብቻ ሳይሆን ወደ ተስፋይቱ ምድር የመራቸው ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት እየጠነከረ እንዲሔድ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገ ሁሉ እናንተም ልክ እንደ ሙሴ ሕዝባችሁ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት እየጠነከረ ይሄድ ዘንድ ሁኔታዎችን ታመቻቹ ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ ማለታቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በማግስቱ፣ በመስከረም 25/2015 ዓ. ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት በመገኘት ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል። በወቅት ቅዱስነታቸው ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ ያለው የኢኮኖሚ መዋቅር በጣም ብዙ የሚባሉ የዓለማችን ሀገራትን ያገለለ እና ተጠቃሚ ያላደረገ መሆኑ እንደሚያሳስባቸው ገልጸው፣ በዚህም ምክንያት ሕዝቦች ለሕገወጥ ዝውውር፣ የሰው ልጆች ክቡር የሆነ የአካል ክፍላቸው በሕገወጥ ሰዎች እንደ ሸቀጣሸቀጥ መሸጥ መጀመሩ፣ በሕጻናት ልጆች ላይ የሚደርገው ወሲባዊ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ፣ ሰዎች ለአስገዳጅ እና ነጻ የጉልበት ሥራ መዳረጋቸው፣ ብዙ ሴቶች እህቶቻችን ለወሲብ ንግድ መዳረጋቸው፣ የአደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚ ወጣቶች መበራከታቸው፣ የጦር መሣሪያ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፋፋመ መምጣቱ፣ አሸባሪዎች በዓለማችን ላይ የደቀኑት አደጋ እየበረከተ መሄዱ፣ የተቀናጀ ዓለማቀፍ ይዘት ያላቸው ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸው እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ በርካታ ስጋቶች በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ መደቀናቸውን አስታውሰው እዚህ የተሰበሰባችሁ የዓለም ሕዝብ ተወካዮች ለእነዚህ አንገብጋቢ ጉዳዮች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርባችኋል በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ 11ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከኅዳር 25-30/2016 ዓ.ም. ወደ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና የመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ በቅደም ተከተል ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህንን 11ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለመጀመር በቅድሚያ ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ አቅንተው የነበረ ሲሆን የጆሞ ኬኒያታ ዓለማቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ እንደ ደረሱም በሀገሪቷ ርዕሰ ብሔር ኡሁሩ ኬኒያታ፣ በሀገሪቷ የሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት እና ምዕመናን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ቅዱስነታቸው በኬንያ ብሔራዊ ቤተመንግሥት ተገኝተው በዚያው ለተሰበሰቡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ባደረጉት የ11 ደቂቃ ንግግር መንግሥት ድኽነት እንዲቀረፍ፣ እኩልነት እንዲረጋገጥ፣ እርቅ፣ ሰላምና መረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ በተለይም ለወጣቶች እና ለአከባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንዲሠራ እና አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበው ነበር።

በማግሥቱም በኅዳር 26/2016 ዓ.ም. ከተለያዩ የሐይማኖት ተወካዮች ጋር ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት በተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መካከል ውይይት ማድረግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስምረው ከገለጹ በኋላ ይህም አክራሪነትን ለመወጋት ከፍተኛ የሆነ ፍይዳ እንዳለው ገልጸዋል። በመቀጠልም 1.4 ሚልዮን የሚገመቱ ምዕመናን በተገኙበት መስዋዕተ ቅዳሴን ማሳረጋቸው ሲታወስ  በወቅቱ ባሳረጉት መሳዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ኬኒያዊያን ቤተሰብ የመደጋገፍ ልማዳቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ሁሉንም ያካተተ የማኅበረሰብ ክፍል መገንባት አስፈላጊ እንደ ሆነ” ገለጸው በተለይም ደግሞ "በሰዎች ላይ የእብሪት ተግባራትን የሚያራምዱ፣ ሴቶችን የሚጎዳ እና ሰብዓዊ ክብርን የሚነሱ እንዲሁም የንጹሃን ህፃናት ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን መወጋት እንደሚገባ” አበክረው መገልጻቸው ይታወሳል።

በኅዳር 28/2016 ዓ.ም. በኬኒያ ያደርጉትን ቆይታ አጠናቀው ወደ ኡጋንዳ ማቅናታቸው ሲታወስ እዚያም እንደ ደረሱ በሀገሪቷ ርዕሰ ብሔር በዩዌሪ ሙሴቪዬኒ፣ በሀገሪቱ በሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት እና ምዕመናን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር። ቅዱስነታቸው በእዚያ በነበራቸው ቆይታ በቅድሚያ የጎበኙት በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የክርስትናን እምነት በመቀበላቸው የተነሳ ከነሕይወታቸው የተቃጠሉ 45 ሰማዕታት አጽም የሚገኝበትን የሙንዮንዮን ሰማዕታት መታሰብያ ቅዱስ ስፍራ መጎብኘታቸው ይታወሳል። እነዚህን ሰማዕታት ለመዘከረ በማሰብ 1.5 ሚልዮን ምዕመናን በተገኙበት የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስርዓት የተካሄደ ሲሆን በእዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የኡጋንዳው ርዕሰ ብሔር ዩዌሪ ሙሴቪዬኒ መገኘታቸው ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት ኡጋንዳዊያን የእነዚህን 45 ሰማዕታት ለእምነታቸው የነበረቸውን ቅንዓት በመከተል "በዕድሜ የገፉ አዛውንቶችን፣ ድሆችን፣ መበለቶችን እንዲሁም ጠዋሪ የሌላቸውን ሰዎች መንከባከባቸውን እንዲቀጥሉ” ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ወደ መካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ባንጉዊ ማቅናታቸው ይታወሳል። በወቅቱ የመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ በክርስቲያኖች እና በሙስሊም እምነት ተከታዮች መካከል የተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭት ብዙዎችን ለስደት እና ለሞት መዳረጉ የሚታወቅ ሲሆን ቅዱስነታቸውም የክርስቲያን እና የሙስሊም እምነት መሪዎችን በአንድ ላይ አገናኝተው በማወያየት እርቅ ይፈጠር ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋጾ ማድረጋቸው ያታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 29/2008 ዓ.ም. ተጀምሮ በኅዳር 11/2009 ዓ.ም ላይ ከ349 ቀናት በኋላ የተጠናቀቀውን ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት ያወጁትም ከዚያው ከመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ ዋና ከተማ ባንጉዊ እንደ ሆነ የሚታወስ ሲሆን በእዚህም ለ349 ቀናት ያህል በቆየው ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት በመላው ዓለም በምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ልዩ ልዩ መንፈሳዊና አካላዊ የምሕረት ተግባራትን በመፈጸም አክብረውት እንዳለፉ ይታወቃል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አስራ ሁለተኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከየካቲት 12-18/2016 ዓ.ም. ድረስ ለማድረግ ወደ ሜክሲኮ ማቅናታቸው ያታወሳል። በዚሁ ለስድስት ቀናት ያህል በሚቆየው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት እገረ መንገዳቸውን በኩባ ዋና ከተማ ሀቫና ለአንድ ቀን ያህል ጎራ በማለት ከሞስኮና የመላው ሩስያ ፓትርያርክ ከሆኑት ፓትርያርክ ቄርሎስ ጋር በግል በመገናኘትና ከዚያም ወደ ሜክሲኮ ማቅናታቸው ይታወሳል። ይህን ጉብኝታቸውን ታሪካዊ ያሰኘው ደግሞ በሜክሲኮ የሚያደርጉት የመጀመሪያው ጉብኝት ሳይሆን ከሞስኮ እና የመላው ሩስያ ፓትርያርክ ቄርሎስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከዚህ በፊት በታሪክ ተከስቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአንድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና በአንድ የሞስኮ እና የመላው ሩሲያ ፓትሪያርክ መካከል በታሪክ አጋጣሚ በቀጥታ ፊት ለፊት ተገናኝተው ለመነጋገር መወሰናቸውና፣ ይህንንም እውን ለማድረግ ቀን ቆርጠው ለመገናኘትና ስለ ወደ ፊቱ በሁለቱ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያንት መካከል ሊኖር ስለ ሚገባው መልካም ግንኙነት ለመነጋገርና አንድ የጋራ የአቋም መግለጫ ለማውጣት  መወሰናቸው ግንኙነታቸውን ታሪካዊ አድርጎታል።  

እንደ ጉርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በየካቲት 14/2016 ቅዱስነታቸው በድህነት እና በአደንዛዥ እፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ ብጥብጥ እና ሁከት ያልተለያት፣ በሜክስኮ የምትገኘውን ኤካትፔክ ከተማ መጎብኘታቸው እና በዚያም የአደንዛዥ እፅ አዛዋዋሪዎች በከፈቱት ጥቃት የተገደሉትን ዜጎች ለማስታወስ መገኘታቸው ይታወሳል። የቅዱስነታቸው በዚህች በስርዓተ አልበኝነት የተጎሳቆለችው ከተማ መጎብኘታቸው በእዚያ የሚገኙትን በአብዛኛው በድኸነት ለተጎሳቆሉ የማኅበረሰብ ከፍሎች ትልቅ ተስፋን የጫረባቸው እንደ ነበረ በወቅቱ ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ 13ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሚያዚያ 16/2016 ዓ.ም. ለማድረግ ወደ ግሪክ ማቅናታቸው ይታወሳል። በእዚህም ጉብኝታቸው በግሪክ የወደብ ከተማ በሆነችው በሌስቦስ ተገኝተው በዚያ የሚገኙትን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ስደተኞች ታጭቀው የሚገኙባትን የወደብ ከተማ መጎብኘታቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በጉብኝታቸውም ወቅት የዓለም መንግሥታት ለስደተኞች ቀውስ አስፈላጊውን ምላሽ በአስቸኳይ ይሰጡ ዘንድ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ 14ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከሰኔ 24-26/2016 ዓ.ም. ለማድረግ ወደ አርሜኒያ ማቅናታቸው ይታወሳል። ቀጥለውም 15ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከነሐሴ 27-31/2016 ዓ.ም. በፖላንድ ማድረጋቸው ይታወሳል።

16ኛውን ሐዋሪያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 2/2016 ዓ.ም. ለማድረግ ወደ ጆርጂያ እና አዘረበጃን በቅደም ተከተል ማቅናታቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ በጆርጂያ ዋና ከተማ በተብሊሲ ከመንግሥት ባለስልጣናት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደ ገለጹት “በእዚህች በተባረከች ምድር፣ በተለያዩ ባህሎች እና ስልጣኔዎች የግንኙነት ቦታ በሆነችው እንዲሁም ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በቅዱስ ኒኖ ተሰብካ ክርስትናን የተቀበለች እና የክርስትና እምነት ሥር መሰረት ያላት እና ጠንካራ የእምነት መሠረት ባላት ሀገር በመገኘቴ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።

“የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ሀገራችሁን ከጎበኙ በኋላ “የጆርጂያ ባሕል እንደ አበባ እንዲፈካ ያደረገው ዘር ክርስትና መሆኑን” ታዝበው ነበር። ይህም ዘር ፍሬያማ መሆኑን ቀጥሏል። ክቡር ፕሬዝዳንት በቫቲካን ባደረጉት ግንኙነት ወቅት ከጆርጂያ ጋር ቅድስት መንበር ያላት መልካም ግንኙነት የሚያጠናክር በመሆኑ ይህ ግንኙነት ቀጣይ እንዲሆን በማሰብ በጆርጂያ ሕዝብ እና ባለስልጣናት ስም ክቡር ፕሬዚደንቱ  እዚህ እንድመጣ ስለጋበዙኝ ከልብ ላመሰግኖት እወዳለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ 17ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከጥቅምት 31- እስከ ኅዳር 1/2016 ዓ.ም. ለማድረግ ወደ ሲዊድን ማቅናታቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ 18ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማደርግ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሚያዝያ 28 ወደ ግብፅ ማቅናታቸው ይታወሳል። የዚህ የቅዱነታቸው 18ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋንኛው ዓላማ በታላቁ በአል ዓዛር የእስልምና ማዕከል ዳይሬክተር ኢማም ሼህ አህመድ አል ጣይብ፣ የግብፅ ሪፖብሊክ ፕሬዚዳንት የሆኑት አብደል ፋታህ ሳሂድ ሁሴን ካሊል አል ሲሲ እንዲሁም የአጠቃላዩን የግብጽ ሕዝብ 30% የሚወክሉት የግብፅ የኮፕት የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ፓትሪያርክ ቴውድሮስ ዳግማዊ ባቀረቡላቸው ግብዣ እንደ ሆነ የታወቀ ሲሆን በተጨማሪም በዚህ ጉብኝታቸው እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1969 ዓ. ም. መቆርቆሩ የሚነገርለት የአል ዓዛር የእስልምና ማዕከል ባዘጋጀው ዓለማቀፍ የሰላም ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በግንቦት 12/2017 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 19ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ በፖርቱጋል ሀገር ፋጢማ በሚባል ልዩ ስፍራ የሚገኘውን እና የዛሬው 100 አመት ገደማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እረኛ ለነበሩ 3 ሕጻናት በተገለጸችበት ሥፍራ የሚገኘውን የፋጢማ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ለመሳለም መሄዳቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዚህ መንፈሳዊ ጉዟቸው ለማርያም ያላቸውን ፍቅር እና እምነት በመግለጽ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የግል ጸሎታቸውን ያቀረቡበት ወቅት መሆኑ ይታወሳል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከመስከረም 06-11/2017 ዓ. ም.  ድረስ በኮሎምቢያ 20ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደ ኮሎምቢያ ማቅናታቸው ይታወሳል።

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከሕዳር 26 - ታኅሳስ 2/2017 ዓ.ም. ድረስ በማያንማር (የቀደሞ ስሟ በርማ) እና በባንግላዲሽ ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገዋል። ማያንማር 54.4 ሚልዮን ሕዝብ ብዛት ያላት ሀገር ስትሆን በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የካቶሊክ ምዕመናን የሚገኙባት ሀገር ናት። በማያን ማር ያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት “የሰላም ልዑክ” የሚል መሪ ቃል ያነገበ እንደ ነበር የሚታወስ ሲሆን በመቀጠልም ቅዱስነታቸው በባንግላዲሽ አድርገውት ለነበረው 21ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት የመረጡት መሪ ቃል “ሰላም እና ሕብረት” የሚል መሪ ቃል እነደነበር ይታወሳል። ባንግላዲሽ 166 ሚሎዮን የሕዝብ ብዛት ያላት ሀገር ስትሆን ከጠቅላላ  የሕዝብ ብዛቷ ውስጥ 350,000 የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ሲሆኑ ይህም 0.24 % የካቶሊክ እምነት ተከታዮች መሆናቸውን ያገልጻል። አብዛኛው የባንግላዲሽ ሕዝብ የሙስሊም እምነት ተከታይ ሲሆን፣ የተቀሩት የቡዳ እና የሌሎች ባሕላዊ እምነት ተከታዮች መሆናቸው ታውቋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከጥር 15-21 ዓ. ም. 22ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደ ደቡባዊ አሜሪካ ሀገራት፣ ቺሊ እና ፔሩ ማቅናታቸው ይታወሳል። ር.ሊ.ጳ. ፍራቸስኮስ እ. አ. አ በሰኔ 21/2018 ዓ.ም 23ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ሲውዘርላንድ ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ እ.አ.አ ከነሐሴ 25-26/2018 ዓ.ም 24ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በአየርላድ፣ እ.አ.አ ከመስከረም 22-25/2018 ዓ.ም በኢስቶኒያ፣ በላቲቪያ እና በሊቱዋኒያ በቅደም ተከተል 25ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማደረጋቸው ይታወሳል።

እ. አ. አ ከጥር 23-27 ዓ.ም ድረስ በፓናማ 26ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ እ.አ.አ ከየካቲት 03-05/2019 ዓ.ም ድረሰ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ 27ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ እ.አ.አ ከመጋቢት 30-31/2019 ዓ.ም 28ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በሞሮኮ፣ እ.አ.አ ከግንቦት 05-07/2019 ዓ.ም 29ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በቡልጋሪያ እና በሰሜን መቀዶኒያ፣ እ.አ.አ ከግንቦት 31-ሰኔ 2/2019 ዓ.ም 30ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በሮማኒያ፣ እ.አ.አ ከመስከረም 04-10/2019 ዓ.ም ድረስ 31ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በሞዛንቢክ፣ በማድጋስካር እና በሞሪሺዬስ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ከኅዳር 19-26 ዓ.ም 32ኛውን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በታይላንድ እና በጃፓን በቅደም ተከተል የሚያደርጉ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በታይላንድ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመረጡት መሪ ሃሳብ “በታይላንድ ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች፣ እምነቶች እና ባሕሎች መካከል አንድነትን ማሳደግ” የሚል ሲሆን በጃፓን ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ግብኝት የመረጡት መሪ ሃሳብም “መላውን ሕይወት ከአደጋ መከላከል” የሚል እንደሆነ ለሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የወጣው መርሃ ግብር ያስረዳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የ32ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መጀመሪያ አገር ወደ ሆነችው ታይላንድ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ ሮም ከሚገኘው ፊውሚቺኖ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መነሳታቸው ታውቋል።

27 November 2019, 15:57