ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ታይላንድ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት የቪዲዮ መልዕክት አስተላለፉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ከኅዳር 9-16/2012 ዓ.ም ድረስ 32ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ  ወደ ታይላንድ እና ጃፓን እንደሚያቀኑ ተገልጿል። ይህን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድመው ለሚሄዱባቸው አገሮች የቪዲዮ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ የሚታወቅ ሲሆን ወደ ታይላንድ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው አስቀድመው ለአገሩ ሕዝብ ያላቸውን ወዳጅነት የገለጹበት የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ታይላንድ የበርካታ ጎሳዎች፣ እምነቶች እና ባሕሎች አገር መሆኗ ይታወቃል። በሕዝቦቿ መካከል እንዲሁም ከደቡብ ምስራቅ የእስያ ሕዝቦች ጋር በሰላም አብሮ ለመኖር የሚያስችላትን ባሕል ለማሳደግ ብዙ ጥረቶችን አድርጋለች። ብዙ አለመግባባት፣ መለያየት ኣና የመገለል አዝማሚያ በሚታይበት ዓለም የእርስ በእርስ መከባበርን፣ የወንዶችን፣ የሴቶችን እና የሕጻናትን ሰብዓዊ ክብር ለማስጠበቅ በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች በኩል የሚደረግ ጥረት በሕዝቦች መካከል ሰላምን በማንገስ ከፍተኛ እድገትን፣ ሕብረትን፣ ፍትሕን ለማምጣት ያግዛል።

በታይላንድ በማደርገው ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ከካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር በመተባበር በእምነታቸው እንዲበረቱ፣ ለሕብረተሰባቸው የሚያበረክቱትን ድጋፍ እንዲያሳድጉ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚን እንደሚፈጥርልኝ እተማመናልሁ። የታይላንድ ሕዝብ ለአገራቸው እድገት በርትተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። የታይላንድ ካቶሊካዊ ምዕመናን፣ ወንድም እና እህት ከሆኑት የቡዳ እምነት ተከታዮች ጋር ያላቸውን ወዳጅነት እና አንድነት በማሳደግ መልካም ምስክርነትን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ተስፋ አደርጋለሁ። ወደ ታይላንድ የማደርገው ሐዋርያዊ ጉብኝቴ በተለያዩ የእምነት ተከታዮች መካከል ለሚደረገው የጋራ ውይይት፣ ለእርስ በእርስ መግባባት እና ወንድማዊ አንድነት በተለይም ለድሆች እና ለሰላም የሚደረገውን ጥረት ለማሳደግ መልካም አስተዋጽዖን ያበረክታል ብዬ አምናለሁ። አሁን የምንገኝበት ወቅት ከምን ጊዜም በበለጠ በጋራ ሆነን ለሰላም ጥረት ማድረግ ያለብን ወቅት ነው።

ወደ ታይላንድ የማደርገው ሐዋርያዊ ጉብኝት ፍሬያማ እንዲሆን ለማድረግ በርካታ ሰዎች በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ በመገንዘብ ለሁሉም ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በእነዚህ ቀናት ውስጥ ቤተሰቦቻችሁን እና አገራችሁን በጸሎቴ እንደማስታውሳቸው እያረጋገጥሁ እናንተንም ሳታቋርጡ በጸሎታችሁ እንድታስታውሱኝ አደራ እላለሁ፤ አመሰግናለሁ”፤ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ታይላንድ እና ጃፓን የሚያደርጉትን 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድመው የቪዲዮ መልዕክታቸውን ለታይላንድ ሕዝብ ልከዋል።

18 November 2019, 16:39