ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ታይላንድን ሲሰናበቱ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ታይላንድን ሲሰናበቱ፣ 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ከታይላንድ ወደ ጃፓን መጓዛቸው ተገለጸ።

ከህዳር 9 - ህዳር /2012 ዓ. ም. ጀምሮ በታይላንድ የደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ትናንት ያገባደዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ወደ ጃፓን ማምራታቸዋን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ሮቤርቶ ፒዬርማሪኒ የላከልን ዘገባ አስታውቋል። ቅዱስነታቸው ዛሬ በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ወደ እኩለ ቀን ገደማ ወደ ጃፓን መድረሳቸውን የዜና አገልግሎቱ አስታውቋል። ቅዱስነታቸው በጃፓን በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት በአውቶሚክ ቦምብ ክፉኛ የተመቱትን ሁለት የጃፓን ከተሞችን እነርሱም ሂሮሺማን እና ናጋሳኪን የሚጎበኙ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ጉዞአቸውን ወደ ጃፓን ከማቅናታቸው በፊት በታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ በሚገኝ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በሚገኝ ጸሎት ቤት የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ማሳረጋቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከባብንኮክ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከመነሳታቸው በፊት ሊሸኟቸው በስፍራው ለተገኙት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ለካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ለተለያዩ  የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮችን ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በጃፓን ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መሪ ሃሳብ እንዲሆናቸው በማለት የመረጡትን “ሕይወትን በሙሉ ከጉዳት እና ከሞት አደጋ እንከላከል” የሚለውን መርህ ሃሳብ በማስቀደም በሁለቱ የጃፓን ከተሞች በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ነገ እሑድ ህዳር 14/2012 ዓ. ም. የሚጀምሩ መሆናቸው ታውቋል። ከጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ ተነስተው፣ ሁለት ሰዓት ያህል የሚፈጅ የበረራ ጉዞን ካደረጉ በኋላ ወደ ናጋሳኪ የሚደርሱመሆናቸው ታውቋል። በጃፓን ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በተቀመጠው መርሃ ግብር መሠረት ቅዱስነታቸው ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት፣ የሕዝባዊ ማሕበራት ተውካዮች፣ የሐይማኖት ተቋማትመሪዎች ጋር ተገናኝተው ሃሳብ የሚለዋወጡ እና መልዕክታቸውንም የሚያስተላልፉ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በጃፓን በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ቶኪዮን፣ ናጋሳኪን እና ሂሮሺማን የሚጎበኙ መሆናቸውን ዘገባው አክሎ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጃፓን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የጋራ መኖሪያ በሆነች ምድራችን የሚገኙትን ፍጥረታት በሙሉ መንከባከብን እና መጠበቅን የሚያስታውስ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ወደ ጃፓን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ በምድራችን ለሚገኝ እያንዳንዱ ፍጥረት አስፈላጊው እንክብካቤን በማድረግ ከጥፋት ለመከላከል፣ ክርስቲያኖች ከፍጥረት ጋር በጸሎት እንዲገናኙ በማለት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል። በእርግጥም የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት በሰው ልጅ ክብር ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ በኒውክሌር መሣሪያ ምርቷ ጃፓን ልታስከትል የምትችለውንም ጥፋት ያገናዘበ መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጃፓን ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተዘጋጀው አርማ ጃፓን የቤተክርስቲያን ምስረታ ወቅት መስዋዕትነትን የከፈሉ ሰማዕታትን የሚያስታውስ ሲሆን ዓርማው የተሳለባቸው ቀለማት እነዚህም የሰማያዊ ቀለም ነበልባል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መላውን የሰው ልጆች የምታቅፍ መሆኗን የሚያሳይ፣ የአረንጓዴ ቀለም ነበልባልም የጃፓን የተፈጥሮ ሃብትን የሚያመላክት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በጃፓን የሚደረገው የተስፋ ወንጌል ብስራትን የሚያመለክት መሆኑ ታውቋል። በቀይ ቀለም በጸሐይ ቅርጽ የተመለከተውም እያንዳንዱን ፍጥረት የሚያካትት የፍቅር ምልክት ሲሆን በተጨማሪም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ሲሰጡ የሚያሳይ ምስልም ያለበት መሆኑ ተመልክቷል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
23 November 2019, 16:41