ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በበረራ ወቅት ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በበረራ ወቅት ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች ባሕሎችን ለሌሎች ማስተዋወቅ ያስፈልጋል”።

ከኅዳር 9 - 16/2012 ዓ. ም. ድረስ በሁለት የሩቅ ምሥራቅ እስያ አገሮች በሆኑት ታይላንድ እና ጃፓን 32ኛውን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደዚያው የተጓዙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጉዞ ወቅት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች የሚገኙ የተለያዩ ባሕሎችን ከሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ጋር ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ለጋዜጠኞች አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከሚያደርጉባቸው ሁለት የሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች መካከል የመጀመሪያ መዳረሻቸው ወደ ሆነችው ታይላንድ በሰላም መድረሳቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። ከታይላንድ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በመቀጠል ወደ ጃፓን እንደሚያመሩ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል። ወደ ታይላንድ ባደረጉት የአውሮፕላን ጉዞ ወቅት ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጋዜጠኞቹ በሙሉ ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ የጋዜጠኞቹ አብሯቸው መጓዝ ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸው ምስጋናቸውንም አቅርበውላቸዋል። የ32ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት መረጃዎችን ለዓለም ሕዝብ በማዳረስ ለሚያበረክቱት አገልግሎት ጋዘጤኞችን አመስግነው፣ ጋዜጠኞቹ ይህን ዕድል በመጠቀም ርቀው የሚገኙትን በርካታ የተለያዩ የሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች ባሕሎችን ለተቀረው የዓለማችን ክፍሎች እንዲያስተዋውቁ አደራ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በሮም ከተማ ከሚገኘው ሌዎናርዶ ዳቪንቺ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከመነሳታቸው በፊት በሥፍራው ለተገኙት ከፍተኛ የሕዝባዊ ተቋማት ተወካዮች እና ለቤተክርስቲያን ተወካዮች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በአሊታሊያ ኤር-ባስ A330 አዲስ አውሮፕላን ውስጥ የተዘጋጀላቸውን ስፍራ ከመያዛቸው በፊት ለበረራ አስተናጋጆች በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።            

ትናንት ከምሽቱ 3:15 ደቂቃ ላይ ሮም ከሚገኝ ፊውሚቺኖ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ በሰላም መድረሳቸውን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት የደረሰን ዘገባ አመልክቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ ሲደርሱ በዶን ሙያንግ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከአገሪቱ መንግሥት ምክር ቤት እንዲሁም በሥፍራው በተገኙት ካቶሊካዊ ምዕመናን በኩል አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ በባንኮክ ከተማ ወደሚገኘው የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ማምራታቸው ታውቋል። 

ቅዱስነታቸው ይህን 32ኛውን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው በፊት በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የድሆች ማረፊያ ውስጥ የሚኖሩትን አሥር አዛውንትን በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ መኖሪያቸው አግኝተው መባረካቸውን እና ሰላምታን መለዋወጣቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ አሌሳንድሮ ቡሶሎ የላከልን ዘገባ አመልክቷል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
20 November 2019, 16:35