ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለጃፓን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ንግግር ሲያደርጉ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለጃፓን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ንግግር ሲያደርጉ፣ 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጃፓን ብጹዓን ጳጳሳት ንግግር ማድረጋቸው ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለብጹዓን ጳጳሳቱ ባደረጉት ንግግር፣ ሕይወትን በሙሉ ከጉዳት በመጠበቅ እና በመንከባከብ፣ የርህራሄን እና የምሕረት ወንጌልን በማወጅ በየዕለቱ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነታቸውን እንዲያቀርቡ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው  በመልዕክታቸው “ሕይወትን በሙሉ ከጉዳት እና ከሞት አደጋ መከላከል ከወንጌል ምስክርነት ጋር አንድ ላይ የሚቀርብ፣ እርስ በእርስም የሚደጋገፉ፣ ሊነጣጠሉም የማይችሉ መሆናቸውን  አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ታላቅ የእምነት ምስክርነት፣

በአርጄንቲና የኢየሱሳውያን ማሕበር አባል ሆነው በጃፓን ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ለማበርከት ከፍተኛ ምኞት እንደነበራቸው ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለጃፓን ሕዝብ የክርስትናን እምነት የመሰከረውን የቅዱስ ፍራንሲስ ዛቪዬር ፈለግ ለመከተል ይመኙ እንደነበር አስታውሰ፣ ቅዱስ ፍራንሲስ በዚያች አገር ክርስትናን ለመመስከር ከተነሳ 470 ዓመታት መቆጠራቸውንም አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ከቅዱስ ፍራንሲስ ቀጥለው በጃፓን ውስጥ ለሰማዕትነት የደረሱትን ቅዱስ ጳውሎስ ሚኪን እና የምስክርነት ጓደኛውን ብጹዕ ዩስቶ ታካያማ ኡኮን አስታውሰዋል።

ሕይወትን ማዳን እና ወንጌልም መመስከር፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጃፓን ብጹዓን ጳጳሳት ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የጃፓን ቤተክርስቲያን በዕለታዊ ኑሮአቸው የወንጌል ምስክርነታቸውን እንዲያሳዩ፣ በሕይወት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከጥቃት አደጋን መከላከል እንዳለባቸው አሳስበዋል። ሕይወትን ከጥቃት መከላከል ማለት ከሁሉ አስቀድሞ መላውን የሰው ልጅ በፍቅር እንዲያገለግሉ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው አደራ ከልብ መገንዘብ መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጃፓን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የጋራ መኖሪያ በሆነች ምድራችን የሚገኙትን ፍጥረታት በሙሉ መንከባከብን እና መጠበቅን የሚያስታውስ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ወደ ጃፓን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ በምድራችን ለሚገኝ እያንዳንዱ ፍጥረት አስፈላጊው እንክብካቤን በማድረግ ከጥፋት ለመከላከል፣ ክርስቲያኖች ከፍጥረት ጋር በጸሎት እንዲገናኙ በማለት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል። በእርግጥም የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት በሰው ልጅ ክብር ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ በኒውክሌር መሣሪያ ምርቷ ጃፓን ልታስከትል የምትችለውንም ጥፋት ያገናዘበ መሆኑ ታውቋል።

ተስፋን፣ ፈውስን እና እርቅን ማድረግ ያስፈልጋል፣

ምስክርነትን የምትሰጥ ቤተክርስትያን ስለ ሰላም እና ፍትሕ በድፍረት መናገር ትችላለች ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ህዳር 14 ቀን 2012 ዓ. ም. በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በአቶሚክ የጦር መሣሪያ አማካይነት የሞት እና የጥቃት አደጋ የደረሰባቸውን በጸሎታቸው የሚያስታውሱ መሆናቸውን ገልጸዋል። በሁለት የኒውክሌር ቦምቦች ፍንዳታ፣ ከፍተኛ ውድመትን ያስከተለ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ በፉኩሺማ የኒውክሌር የጦር ማምረቻ ማዕከል በደረሰው አደጋ ምክንያት በከፍተኛ የአካል ጉዳት እና የመንፈስ መረበሽ ለደረሰባቸው ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መርዳት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው ብለው ከዚህም በተጨማሪ የማይናወጥ ተስፋ፣ እውነተኛ ፈውስ እና እርቅ የሆነውን የወንጌል መልዕክት ማዳረስ ያስፈልጋል ብለዋል።

ማሕበራዊ ሕመም፣

በጃፓን ማሕበረሰብ ውስጥ የተስፋፋውን ከፍተኛ ማህበራዊ ችግሮችን ከእነዚህም መካከል የብቸኝነት፣ የመከፋፈል፣ ራስን የማጥፋት እና የተደራጀ ወንጀል የወጣቶችን ሕይወት እጅግ የጎዳው መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል። የጃፓን ሕዝብ ባሕል ለዜጎቹ በሙሉ ክፍት በመሆን እድገትን እና ብልጽግናን፣ ልግስና እና ለራሱ የማይሰስት የፍቅር ባሕል እንዲሆን ለማድረግ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉ አስተዋጽዖን እንዲያበረክት አደራ ብለዋል።  

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጃፓን ሐዋርያዊ ጉብኝት እስከ ማክሰኞ ህዳር 16/2012 ዓ. ም. ድረስ የሚቆይ መሆኑን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለክታል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
23 November 2019, 16:59