ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

«በጥንቃቄ ተሞልተን የእምነትን መልእክት ማሰራጨት እንችል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዲረዳን እንጠይቅ »

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በጥቅምት 26/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ የመጽሐፍ ክፍል ላይ ተንተርሰው ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥቅምት 26/2012 ዓ.ም ባደረጉት የክፍል ዐስራ አምስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደረገው  ስለዚህ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአቴና ሰዎች ሆይ፤ በማናቸውም ረገድ፣ በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን አያለሁ፤ እየተዘዋወርሁ ሳለሁ፣ የምታመልኳቸውን ነገሮች ስመለከት፣ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ ያለበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁና፤ እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ » (የሐዋ 17፡22-23) በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “በጥንቃቄ ተሞልተን በሰዎች ባሕል ውስጥ የእምነትን መልእክት ማሰራጨት እንችል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዲረዳን እንጠይቅ”  ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥቅምት 26/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መጽሐፍ ላይ የጀመርነውን “ጉዞ” ዛሬም እንቀጥላለን። በፊሊጲሲዮስ፣ በተሰሎንቄ እና በቤርያ ከኖሩ በኋላ ጳውሎስ የግሪክ አገር ልብ ወደ ሆነችው ወደ አቴና ደረሰ። በጥንት ጊዜ በታላቅ ክብር ጥላ ውስጥ ትገኝ የነበረችው ይህች በተማ የባሕል እና በፖለቲካው ዘረፍ የነበረውን ቀደምት ማንነቷን ጠብቃ የቆየች ከተማ ናት።  ጳውሎስ በአቴና ሲዘዋወር በነበረበት ወቅት፣ ከተማይቱ በጣዖት የተሞላች መሆኗን በማየቱ የተነሳ መንፈሱ ተበሳጨ (ሐዋ 17፡16)። ይህ የአረማዊያን “ተጽዕኖ” እርሱ ሁኔታውን ሸሽቶ ከመሄድ ይልቅ ከእዚያ ባህል ጋር ለመወያየት ድልድይ እንዲገነባ ይገፋፋዋል ።

ጳውሎስ ከከተማዋ ጋር በሚገባ ለመተዋወቅ ፈለገ በእዚህ መሰረት በጣም አስፈላጊ ቦታዎችን እና ሰዎችን መከታተል ጀመረ። የእምነት ሕይወት ተምሳሌት ወደ ሆነው ወደ ምኩራብ ሄደ፣ የከተማ ሕይወት መገለጫ ወደ ሆነው ወደ አደባባይ ይሄዳል፣ የፖለቲካ እና የባህላዊ ህይወት መገለጫ ምልክት ወደሆነው  ወደ አርዮስፋጎስ  ይሄዳል። ጳውሎስ በአቴና ባህል እና አካባቢ ውስጥ በሚገኙ “ቤቶች፣ በጎዳናዎቹ ፣ በመንደሩ እና በአደባባዩ ውስጥ የሚኖረውን እግዚአብሔር“ በአዕምሮ እይታ ማሰላሰሉን ቀጥሉዋል። ጳውሎስ የአቴናን ከተማ እንደ ባዕድ ከተማ አድርጎ በጥላቻ ስሜት አለተመለከታትም፣ ነገር ግን ከተማዋን የተመለከተው በእምነት ዐይን ነው። እናም ይህ እኛ የእኛን ከተሞች የምንመለከትበት መንገድ በጥያቄ ውስጥ እንድናስገባ ያደርጋል፣ ከተሞቻችንን በግድዬለሽነት ነው የምንመለከተው? በንቀት ነው የምንመለከተው? ወይስ ባልታወቁ የእግዚአብሔር ልጆች አምካይነት የተሰራጨውን እምነት ነው የምንመለከተው?።

በወንጌል እና በአረማውያን ዓለም መካከል ክፍተት እንዲፈጠር የሚያነሳሳውን እይታ ጳውሎስ ይመለከታል። በጥንታዊው ዓለም በጣም ታዋቂ ከሆኑት ተቋማት አንዱ በሆነው በአርዮስፋጎስ የእምነት ምልክት የሆነ ያልተለመደ ምሳሌ እንዳለ ይገነዘባል፣ ለጣዖት አምላኪዎች ኢየሱስ ክርስቶስን ያውጃል፣ ጣዖቶቻቸውን በማውደም ሳይሆን ጣዖቶችን የመሸጋገሪያ ድልድይ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል።

ጳውሎስ “የማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ ያለበት አንድ መሠዊያ በከተማው መሃል ይመለከታል፣ እናም ከአድማጮቹ ጋር ለመግባባት ያስችለው ዘንድ ያንን አጋጣሚ በመጠቀም እግዚአብሔር “በዜጎች መካከል እንደሚኖር” ያውጃል። “በቅን ልቦና ለሚፈልጉት ሰዎች ራሱን አይደብቅም” በማለት ይናገራል። ጳውሎስ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም “እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ » በማለት ያውጃል።

አቴናውያን የሚያከብሩትን አምላክ ማንነት ለመግለጥ ፣ ሐዋርያው ከፍጥረት ይጀምራል ፣ስለ አምላክ መገለጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነቶችን በመገልጽ ወደ መዳን እና ወደ ፍርድ ለመድረስ የሚያስችለውን እርሱም ትክክለኛው የክርስቲያን መልእክት የሆነውን ያውጅላቸዋል።  በፈጣሪ ታላቅነት እና በሰው በተገነቡት ቤተመቅደሶች መካከል ያለውን ልዩነት ያሳያል ፣ እናም ፈጣሪ ሁል ጊዜ የሰው ልጆችን ለምን እንደ ሚፈልጋቸው ይገልጻል። በዚህ መንገድ ጳውሎስ “ሰዎች የሚያውቁትን ነገር ግን ችላ ያሉትን ያውጃል”።  ከዛም ሁሉንም “ከድንቁርና ጊዜያት” አልፎው እንዲሄዱ እና በቅርብ ጊዜ ከሚመጣው ፍርድ አንጻር መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት ይችሉ ዘንድ  እንዲወስኑ ሁሉንም ሰው ይጋብዛል። በዚህ መንገድ ጳውሎስ የክርስቶስን ስም በቀጥታ ሳይገልጽ በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጦአል።” (ሐዋ 17፡31) በማለት ክርስቶን ከማወጅ ወደ ክርስቶስን መመስከር ይሸጋገራል።

የጳውሎስ ስብከት ፣ እስከዚህም ድረስ አጋሮቹ አፍነው ዝም ብለው ይዘውት የቆዩትን እስትንፋስ እንዲተነፍስ ያደረጋል፣ ይህም እንቅፋት ይሆናል፣ የክርስቶስ ሞት እና ትንሣኤ “ሞኝነት” (1 ቆሮ 1፡23) ነው ብለው ስላሰቡ አፌዙ እንዳንድቹ ደግሞ ተሳለቁበት። በእዚያን ጊዜ ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጥቶ ሄደ - ሙከራው የተሳካለት ይመስላል፣ አንዳንዶች ቃሉን ሰምተዋል፣ እራሳቸውን ለእምነት ከፍተዋል። በአቴና ደግሞ ወንጌል ሥር ይሰድዳል፣ እናም ቅዱስ ወንጌል በሁለት ድምጾች ማለትም በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት ድምጽ አማካይነት መሰራጨቱን ይጀምራል !

በዛሬው ጊዜም መንፈስ ቅዱስ ከባህላችን ውጪ ከሆኑ፣ ከማያምኑ ወይም ከእኛ የተለየ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር መወያየት እንችል ዘንድ ድልድይ እንድንገነባ እንዲያስተምረን እንጠይቃለን። በከፍተኛ ጥንቃቄ ተሞልተን በሰዎች ባሕል ውስጥ የእምነትን መልእክት ማሰራጨት እንችል ዘንድ፣ በእመት ድንቁርና ውስጥ ያሉ ሰዎች ክርስቶስን የማያውቁ ሰዎች ክርስቶስን በልባቸው ማሰላሰል እንዲጀምሩ በፍቅር ኃይል ልባቸው እንዲንቀሳቀስ፣ ደንዳና የሆነ ልብ እንኳን ሳይቀር በፍቅር ሙቀት እንድለሰልስ እና የእመንት ምልእክት ቀስ በቀስ እንዲቀበሉ ማደረግ እንችል ዘንድ እንዲረዳን የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንጠይቅ።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
06 November 2019, 11:58