“ዛሬ የምናከብረው ‘የሁሉም ቅዱሳን’ አመታዊ በዓል እኛም ወደ ቅድስና ሕይወት እንደ ተጠራን ያስታውሰናል”!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በዛሬው እለት ማለትም በጥቅምት 21/2012 ዓ.ም ማለት ነው “የሁሉም ቅዱሳን” ዓመታዊ በዓል በታላቅ መንፈሳዊነት ተከብሮ ማለፉ ይታወቃል። ይህ በዓል በቫቲካን በተከበረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይህንን “የሁሉም ቅዱስ” በዓል ለመታደም ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች በዕለቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተወስደው በተነበቡ ምንባባት ላይ ተመስርተው ባሰሙት አስተንትኖ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “ዛሬ የምናከብረው ‘የሁሉም ቅዱሳን’ አመታዊ በዓል እኛም ወደ ቅድስና ሕይወት እንደ ተጠራን ያስታውሰናል”  ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም በጥቅምት 21/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች በእለቱ የተከበረውን “የሁሉም ቅዱሳን” ዓመታዊ ክብረ በዓል አስመልክተው ያሰሙትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል አባራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ የምናከብረው የሁሉም ቅዱሳን አመታዊ በዓል እኛ ሁላችን ወደ ቅድስና ሕይወት እንደ ተጠራን ያስታውሰናል። ዛሬ ሁላችንም የምናከብራቸው ቅዱሳን በቀላሉ እንዲሁ ምልክት ሆነው ያለፉ፣ ከሰው ልጅ ታሪክ ርቀው የሚገኙ እና ተደራሽ ያልነበሩ ሰዎች አይደለም። በተቃራኒው፣ እንደ ማነኛችንም ሰዎች በእግራቸው መሬት ላይ የኖሩ ሰዎች ናቸው፣ ሁሌም ለመነሳት እና ጉዞው ለመቀጠል የሚያስችል ጥንካሬን በጌታ በማግኘት በእየለቱ ከሚያጋጥማቸውን ውድቀቶች እና ስኬቶች ጋር መኖር የተለማመዱ ሰዎች ነበሩ።ከዚህ በመቀጠል ቅድስና በአንድ ሰው ጥንካሬ ብቻ ሊከናወን የማይችል ግብ መሆኑን የተረዱ ሲሆን፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋ ፍሬ እና ለእርሱ ያለንን ነፃ ምላሽ የምንገልጽበት መሆኑንም ተረድተው ነበር። ስለዚህ ቅድስና ስጦታ እና ጥሪ ነው።

የእግዚአብሔር ጸጋ ማለትም ስጦታው፣ እኛ ልንገዛው ወይም ልንለውጠው የምንችለው ነገር አይደለም፣ ነገር ግን ከጥምቀታችን ቀን ጀምሮ በውስጣችን በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ እና በተመሳሳይ መልኩም በመለኮታዊ ሕይወት ውስጥ በመሳተፍ የሚገኝ ነገር ነው። ወደ ክርስቶስ የተሸጋገርን፣ አንድ የወይን ቅርንጫፍ ከግንዱ ጋር እንደ ተወሃደ ሁሉ እኛም የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን ከእርሱ እና ከእርሱ ጋር ብቻ መኖር መቻል ይኖርብናል። እናም ቅድስና አሁን በእዚህ ምጽሐተኛ በሆንበት ምድር ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር ሙሉ ህብረት ፈጥሮ መኖርን ያመለክታል።

ቅድስና ስጦታ ከመሆኑ በተጨማሪ በጋራ የክርስቶስ ሐዋርያ እንድንሆን የቀረበልን መንፈሳዊ ጥሪ ተብሎ ይጠራል፣ ወደ መጨረሻ ግብ ማለትም ወደ ዘላለም ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ህብረት ከእግዚአብሔር ጋር እያንዳንዱ ክርስቲያን በእምነት እንዲከተል የተጠራው ምልአት ያለው መንገድ ነው። ስለዚህ ቅድስና እግዚአብሔር ላቀረበልን ጥሪ የምንሰጠው ምላሽ ነው። በዚህ አተያይ፣ በሕይወታችን ሁኔታዎች እና ግዴታዎች ሁሉ ውስጥ፣ በሁሉም ነገር ውስጥ በፍቅር እና በርኅራኄ ለመኖር በመሞከር በእዚህ መልኩ በመጓዝ ለመቀደስ ከባድ እና ዕለታዊ ቁርጠኝነትን መውሰድ አስፈላጊ ነው።

ዛሬ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ የምናከብራቸው ቅዱሳን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሕይወታቸው ውስጥ ይህ መለኮታዊ ብርሃን እንደሚያስፈልጋቸው አምነው ተቀብለው በሕይወታቸው ውስጥ ተግብረው አልፈዋል። በመሆኑም አሁን ፣ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት (ራዕ 7: 15 ን ተመልከት) ፣ ክብሩን ለዘላለም ይዘምራሉ። እኛ ትክክለኛ ግባችን ብለን በተስፋ የምንጠብቀውን “ቅድስቲቷን ከተማ” ይመሠርታሉ፣ እኛ አሁን ምድራዊ በሆነው ከተማችን ውስጥ በምናደርገው አሰችጋሪ ጉዞ ውስጥ በተሰፋ እንድንጓዝ ይረዱናል። ሕይወታቸውን በመመልከት እነሱን ለመምሰል እንበረታታለን። በእኛ መካከል የሚኖሩ በሮቻችን አጠገብ ይሚገኙ የእግዚኣብሔር ተስፋ መገለጫ እና ነጸብራቅ የሆኑ ብዙ ቅዱሳን ምስክሮች አሉ።

ይህ ሁሉን ቅዱሳን የምናስብበት ቀን ዐይናችንን ወደ ሰማይ ከፍ እንድናደርግ ይመራናል፣ የምድርን እውነታዎች ለመርሳት ሳይሆን ይልቁንም በምድር ላይ የሚያጋጥሙንን ሁኔታዎች በድፍረት እና በተስፋ መጋፈጥ እንድንችል ይረዳናል። የመጽናና እና እርግጠኛ ተስፋ ምልክት የሆነችው ቅድስት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናትነት አማላጅነቷ ከልጇ ዘንድ እንድታማልደን ልንጸልይ ይገባል።

01 November 2019, 16:39