በባንኮክ አውሮፕላን ማረፊያ ለቅዱስነታቸው አቀባበል ሲደረግላቸው፣ በባንኮክ አውሮፕላን ማረፊያ ለቅዱስነታቸው አቀባበል ሲደረግላቸው፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ታይላንድ በሰላም ደርሰው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ጀመሩ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከኅዳር 09-16/2012 ዓ.ም ድረስ በታይላንድ እና በጃፓን በቅደም ተከተል የሚያደርጉትን 32ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በኅዳር 09/2012 ዓ. ም አመሻሹ ላይ መጀመራቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ቅዱስነታቸው እንደ ተለመደው ማንኛውንም ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው በፊት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወደ ሚያደርጉባቸው አገራት ከማቅናታቸው በፊት በቪዲዮ መልእክት እንደ ሚያስተላልፉ ይታወቃል፣ በእዚህም መሠረት ቅዱስነታቸው 32ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት መዳረሻ ወደ ሆኑ አገራት ከማቅናታቸው በፊት መልእክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለቅዱስነታቸው ከወጣው የጉዞ መርሃ ግብር ለመረዳት እንደተቻለው በኅዳር 09/2012 ዓ. ም በሮም ከተማ አቅራቢያ ከሚገኘው የሊዮናርዶ ዳቪንቺ ዓለማቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 03፡15 ላይ ተነስተው 9,332 ኪሎ ሜትሮችን በአየር ላይ ተጉዘው 11፡30 ደቂቃ በረራ ካደርጉ በኋላ የታይላንድ ዋና ከተማ ወደ ሆነቺው ባንኮክ መድረሳቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ባንኮክ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ እንደ ደረሱ የአገሪቷ ባለስልጣናት እና የሐይማኖት መሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። በአውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ለቅዱስነታቸው አቀባበል ካደረጉላቸው ከፍተኛ የአገሪቱ የመንግሥት ተወካዮች በተጨማሪ የአገሪቱ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት እና ባሕላዊ ልብሶችን የለበሱ 11 ሕጻናት፣ ሦስት መቶ ሺህ ምዕመናን ከሚገኙባት ከባንኮክ ሀገረ ስብከት የተወጣጡ ምዕመናን ለቅዱስነታቸው አቀባበል ማድረጋቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል።

ቅዱስነታቸው ከአውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት በባንኮክ ከተማ ወደሚገኘው የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት በመጓዝ እዚያ በተዘጋጀላቸው የእንግዳ መቀበያ ካረፉ በኋላ ለዚህ ሐዋርያዊ ጉዞ በተዘጋጀላቸው መርሃ ግብር መሠረት በግላቸው የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ማሳረጋቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በታይላንድ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት የተለያዩ ማሕበረሰቦችን በማግኘት የሚያደርጓቸው ንግግሮች ከነገ ሐሙስ ህዳር 11 ቀን 2012 ዓ. ም. ጀምሮ ይፋ እንደሚሆኑ የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። በዚህ 32ኛው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት መንሃ ግብር መሠረት ነገ ሐሙስ ህዳር 11/2012 ዓ. ም. የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀኔራል ፕራዩይ ቻን ኦካ እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በአገሪቱ ቤተመንግሥት ውስጥ የሚቀበሏቸው መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸውም በስፍራው ለሚገኙት ከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች እና የውጭ አገር ዲፕሎማቶች ንግግር የሚያደርጉ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመቀጠልም በአገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ እና የቡዳ እምነት መሪ ከሆኑት ሶምዲ ፋራ ማ ሙኒዎንግን  ጋር የሚገናኙ መሆናቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባንኮክ ከተማ በሚያደርጉት ቆይታ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1898 ዓ. ም. የተቋቋመውን እና በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚተዳደርውን የቅዱስ ሉዊስ ሆስፒታል የሚጎበኙ መሆናቸው ታውቋል። ሆስፒታሉ በአገሩ ውስጥ ከሚገኙ የሕክምና መስጫ ተቋማት መካከል በአገልግሎት ጥራቱ መልካም ስም ያለው መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በሆስፒታሉ በመገኘት የሕክምና አገልግሎትን በማግኘት ላይ የሚገኙት ደሃ ቤተሰቦችን የሚጠይቁ መሆናቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ ሐሙስ ህዳር 11/2012 ዓ. ም. የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚገባደደው ከአገሪቱ ንጉሥ ጋር በሚያደርጉት የግል ግንኙት እና በባንኮክ ከተማው በሚገኘው ብሔራዊ ስታዲዬም በሚያሳርጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት መሆኑን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለከታል። በመርሃ ግብሩ መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ዓርብ ህዳር 12/2012 ዓ. ም. በሀገሪቱ ከሚገኙ ካቶሊካዊ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ የዘርዓ ተምህርት ቤት ተማሪዎች እና ከትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር ከተገናኙ በኋላ ከመላው የታይላንድ እና የእስያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር በባንኮክ ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ቁምስና እና በብጹዕ ኒኮላ ቡንኬርድ ኪትባሙርግ ቤተክርስቲያን የሚገናኙ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ቀጥለውም በባንኮክ ከተማ በሚገኘው በፍልሰታ ማርያም ካቴድራል ውስጥ ለአገሩ ካቶሊካዊ ወጣቶች በሚያሳርጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በታይላንድ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚፈጽሙ መሆናቸውን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለክታል።            

የታይላንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በምዕመናኖቿ ቁጥር ትንሽ ብትሆንም ለአገሩ ሕዝቦች በምታበረክተው ሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎቷ የምትመሰገን መሆኗ ታውቋል። ቤተክርስቲያኒቱ ከኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጣት አደራ መሠረት የወንጌል ተልዕኮዋንም በትጋት እየፈጸመች ያለች መሆኗ ሲነገር ከዚህም በተጨማሪ በአገሩ ውስጥ ጥራት ያለውን ትምህርት በማዳረስ የምትታወቅ፣ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት ጋር ዘላቂ የጋራ ውይይቶችን በማድረግ መልካም ግንኙነትን በማሳደግ ላይ መሆኗ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
20 November 2019, 16:26