በባንኮክ ለወጣቶች የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን ባሳረጉበት ወቅት፣ በባንኮክ ለወጣቶች የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን ባሳረጉበት ወቅት፣ 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መላውን የታይላንድ ሕዝብ አመሰገኑ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከህዳር 9/2012 ዓ. ም. ጀምሮ በታይላንድ ሲያደርጉ የቆዩትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ትናንት ህዳር 12/2012 ዓ. ም. መፈጸማቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በታይላንድ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት መሪዎች፣ ከውጭ አገር ዲፕሎማቶች፣ ከሕዝባዊ ማህበራት ተወካዮች፣ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ከታይላንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት እንዲሁም ምዕመናን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው እና መልዕክቶችን ማስተላለፋቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በታይላንድ ሲያደርጉ የቆዩትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ትናንት ህዳር 12/2012 ዓ. ም. በዋና ከተማ ባንኮክ በሚገኝ የፍልሰታ ማርያም ካቴድራል ውስጥ ለወጣቶች ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ማጠናቀቃቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በቅዳሴው ጸሎት ሥነ ሥርዓት ወቅት ባሰሙት የምስጋና ንግግር ሲመኙት የነበረውን የታይላንድ ሐዋርያዊ ጉብኝት እውን እንዲሆን ያደረጉትን፣ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ፍሬያማ እንዲሆን በሕብረት የሰሩትን በሙሉ አመስግነዋቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከታይላንድ ንጉሥ ግርማዊ ራማ 10ኛ እና ከአገሪቱ መንግሥት እንዲሁም ከተለያዩ የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በኩል ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ቀጥለውም ለአገሪቱ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ለብጹዕ ካርዲናል ፍራንሲስ ዛቬር፣ ካይህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት እንዲሁም ምዕመናን፣ በተለየ መልኩ ለታይላንድ ካቶሊካዊ ወጣቶች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ቅድመ ዝግጅት ላይ የተሳተፉትን፣ በጉብኝታቸው ወቅትም ከሌሎች ጋር በመታባበር ውጤታማ አገልግሎትን ላበረከቱ በጎ ፈቃደኞችን፣ በጸሎታቸው የተባበሩትን እና ጊዜያቸውን ጉልበታቸውን መስዋዕት ያደረጉትን፣ በተለይም በሕመም ላይ የሚገኙትን እና በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ለሚገኙት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።    

ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ሊገኝ የሚችለውን መጽናናት እና ሰላም ተመኝተው ምዕመናን በሙሉ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ በማለት በታይላንድ ያደረጉትን 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
23 November 2019, 16:23