የሐዘንተኞች የአበባ ጉንጉን፤ የሐዘንተኞች የአበባ ጉንጉን፤  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጀርመን በደረሰው ጥቃት በማዘን ጸሎታቸውን አቀረቡ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጀርመን ውስጥ ሃሌ ከተማ በሚገኘው ምኩራብ በተሰነዘረው ጥቃት ሰለባ ለሆኑት በሙሉ ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው የአደጋው ዜና የደረሳቸው በቫቲካን ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኝ የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የዕለቱ ውሎ ከማጠናቀቁ በፊት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአይሁዶች ምኩራብ በተሰነዘረው ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸው፣ በርካቶችንም መቁሰላቸው ታውቋል። ጥቃቱን ያየረሰው የ27 ዓመት ዕድሜ ወጣት እና የኒዮ ናዚ እንቅስቃሴ አባል መሆኑ ታውቋል። ጥቃቱ የተሰነዘረው ሕጻናትን ጨምሮ በቁጥር ከሰባ በላይ የሚሆኑ የአይሁድ እምነት ተከታዮች በምኩራባቸው ውስጥ በዓላቸውን በሚያከብሩበት ሰዓት መሆኑ ታውቋል። ጥቃቱን ያደረሰው ወጣት የጸሎት ስነ ስርዓት ይካሄድ ወደነበረበት ስፍራ ለመግባት ያደረገው ሙከራ ሳይሳከለት መቅረቱ ታውቋል። የተኩስ ድምፅ የሰሙት የበዓሉ ተካፋዮች በሮችን ዘግተው ባያግዱት ኖሮ በሰው ሕይወት ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋ እጅግ ከፍተኛ ሊሆን እይችል ነበር ተብሏል። 

የጀርመን መንግሥት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳረጋገጡት ጥቃቱን የተሰነዘረው የ“ፀረ-ሴማዊ” ተነሳሽነት ባለው ወጣት ነው ተብሏል። የጀርመን ቻንስለር አንጌላ ሜርክል በበርሊን በተደረገው የመታሰቢያ ስነ ስርዓት ላይ መገኘታቸው ታውቋል። በብራሴልስ የተሰበሰቡት የአውሮጳ ፓርላማ አባላትም የአደጋው ዜና በሰሙ ጊዜ የአንድ ደቂቃ ጸሎት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ሌሎች የፖለቲካ እና የሐይማኖት መሪዎችም በአውሮፓ ውስጥ ፀረ-ሴማዊነት እድገትን ለመቋቋም አዲስ ጥረቶች እንዲደረጉ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በቫቲካን ውስጥ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የቀን ሥራውን ከማጠናቀቁ በፊት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በመሆን ለተጎጂዎቹ እና ለቤተሰቦቻቸው ጸሎታቸውን አቅርበዋል። በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዓመታዊውን የሮሽ ሐሻና እና ዮም ኪፑር የአይሁድ እምነት በዓላትን በማስመልከት በሮም የአይሁድ እምነት መሪ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት መላካቸው ይታወሳል።        

10 October 2019, 17:27