ሊባኖስ የሰላም እና የፍትህ አገር እንድትሆን፣ ሊባኖስ የሰላም እና የፍትህ አገር እንድትሆን፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ሊባኖስ የሰላም እና የፍትህ አገር እንድትሆን ተማጸኑ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እሁድ ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ.ም፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ካቀረቡት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በመቀጠል የተወደደውን የሊባኖስ ሕዝብ አስታውሰው፣ በአገሪቱ ተስፋፍተው ይገኛሉ ያሉትን ማሕበራዊ፣ ሞራላዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሮችን በመቃወም ከቅርብ ቀናት ጀምሮ ወደ አደባባይ በመውጣት ድምጻቸውን በማሰማት ላይ የሚገኙትን የሀገሪቱ ወጣቶች በጸሎታቸው አስታውሰዋቸዋል። መላው የሀገሪቱ ሕዝቦችም ችግሮችን የሚያስወግዱበትን ፍትሃዊ መንገዶችን በጋራ ውይይት እንዲያገኙ ጠይቀው፣ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ፣ የሊባኖስ ሕዝብም በሰላም እና በመቻቻል አብሮ የሚኖርበት አገር እንዲሆን፣ የሰው ልጅ ክብር እና ነጻነት ተከብሮ፣ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በስቃይ የኖረ የመካከለኛ ምስራቅ አገሮች ሕዝቦችም ሰላምን እንዲያገኝ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታቸውን የሚያቀርቡ መሆናቸውን ተናገረዋል።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በስፍራው ለተገኙት፣ ከኢጣሊያ እና ከሌሎች አገሮች ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን በተለይም ከብራዚል፣ ከፖላንድ እና ከስፔን ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። የማሕበራቸው ምስረታ መቶኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን በማክበር ላይ የሚገኙትን የቅዱስ ልበ ኢየሱስ ደናግልን፣ ከሕንድ፣ ፓቲ ሀገረ ስብከት ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ በኢጣሊያ ከሬጆ ኤሚሊያ ለመጡት የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና የምስጢረ ሜሮን ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ፣ በኢጣሊያ የጋልሲኛኖ ወጣቶች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው ቀጥለውም በጎርጎሮሳዊ አቆጣጠር የወንጌል ተልዕኮ የሚታሰብበት እና የመቁጠሪያ ጸሎት የሚቀርብበት ወር የተገባደደ መሆኑን አስታውሰው የቤተክርስቲያን ተልዕኮን በማስታወስ ምዕመናን በያሉበት ሆነው የመቁጠሪያ ጸሎትን ማቅረብ እንዲቀጥሉበት አደራ ብለው በዚህ አጋጣሚ በተለያዩ የዓለማች ክፍሎች መከራ የሚደርስባቸው ሚሲዮናዊያንን እና ሚሲዮናዊያትን በጸሎት እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል። ለዓለም ሰላም ጸሎት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው በአደባባዩ ለተሰበሰቡት በሙሉ መልካምን ተመኝተውላቸው ሲያበቁ ምዕመናኑ ሳይዘነጉ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።   

28 October 2019, 18:52