ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “እምነት አንዳችን ለሌላው ከምንሰጠው አገልግሎት የምናገኘው ደስታ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሁድ መስከረም 25/2012 ዓ.ም፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ጋር በመሆን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አድረሰዋል። በዕለቱ ከሉቃ. ምዕ. 17:5-10 ተውስዶ በተነበበው የወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሰሙት ስብከታቸው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ እምነት አንዳችን ለሌላው ከምንሰጠው አገልግሎት የምናገኘው ደስታ እንደሆነ አስረድተዋል ብለዋል። ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ንባብ ላይ በማስተንተን ለምዕመነና ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ የተነበበው የሉቃ. 17፤5-10 የሚናገረን ስለ እምነት ነው። ሐዋርያት ኢየሱስን ጌታ ሆይ “እምነታችንን ጨምርልን” በማለት የጠየቁትን ያስታውሰናል። በሉቃ. 17፤6 ላይ ኢየሱስም ሁለት ምሳሌዎችን በመናገር ይመልስላቸዋል። የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ አላቸው። የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ሾላ፣ ‘ተነቅለህ ባሕር ውስጥ ተተከል’ ብትሉት ይታዘዝላችኋል” አላቸው። የሾላ ዛፍ ግዙፍ፣ ሥሩም ወደ መሬት ውስጥ ዘልቆ የገባ ነው፤ ነፋስንም የሚቋቋም ነው። በዚህ ምሳሌው ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ማስረዳት የፈለገው ትንሽ እምነት ቢኖራቸው አቅማቸው ከሚችለው በላይ የሆነውን ነገር ያለ ችግር ማከናወን የሚችሉ መሆናቸውን ለማስረዳት ፈልጓል። በዚህ ብቻም አላበቃም፤ ያን ትልቁን የሾላ ዛፍ ተነቅሎ በባሕር ውስጥ እንዲተከል ማድረግ ፈጽሞ የማይታሰብ ከባድ ስራ ነው። እንግዲህ ከዚህ የምንገነዘበው ትንሽ እምነት ቢኖረን ምንም የሚሳነን ነገር አለመኖሩን፣ የምናከናውነው በራሳችን ሃይል ሳይሆን ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ሃይል መሆኑን ያስገነዝበናል።

ከሰናፍጭ ፍሬ ጋር የሚወዳደር እምነት ራንሱ በጣም ትንሽ እንደሆነ ስለሚገነዘብ ሃይልን እና እገዛን ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚያገኝ ሙሉ እምነት አለው። በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመንን፣ ሽንፈትንም ሆነ ስቃይን በትዕግስት እንድንቀበል፣ ክፋትም በእኛ ላይ ፈጽሞ የበላይነትን የሚያገኝ አለመሆኑን እንድናውቅ የሚያደርገን በእምነት ላይ በምናደርገው ተስፋ ነው።

ስለዚህ እምነት እንዳለን የምናውቀው እንዴት ነው? ያለን እምነት በጣም ትንሽ ቢሆንም እውነተኛ እምነት መሆኑን የምናውቀው እንዴት ነው? የእምነታችንን መጠን የምናውቀው ‘አገልግሎት’ ነው በማለት ኢየሱስ የሚከተለውን ምሳሌ በማቅረብ ያስረዳል። ለሰራተኛው የማይራራ፣ ድካሙንም የማቆጥለት አንድ ሃይለኛ አሰሪ በእርሻው ቀኑን ሙሉ ሲሰራ ውሎ ማታ ወደ ቤት የተመለሰውን አገልጋዩን ለሁለቱም ምግብ እንዲሰራላቸው እና ከበላ በኋላ ማረፍ እንደሚችል ያዘዋል። የአሰሪው ወይም የጌታው አቋም የምሳሌው ትክክለኛ ማዕከል የቱጋ እንደሆነ ግልጽ አድርጎ ያሳያል። ይህም አገልጋዩ ምንም ሳያንገራግር የጌታውን ትዕዛዝ መቀበሉ ነው። እምነት አለኝ የሚል ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስቀደመ፣ ያለ ምንም ጥያቄ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ለመፈጸም የተነሳ መሆን እንዳለበት ኢየሱስ በምሳሌው ይናገራል።

ከራሱ ይልቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስቀደመ ሰው በሚኖርበትን ማሕበረሰብ ውስጥ ምን ዓይነት ሕይወት እንዳለው፣ ምን ዓይነት አገልግሎትን እንደሚያበረክት በግልጽ ማየት ይቻላል። ያለንን የእምነት መጠን ማወቅ የምንችለው በአገልግሎታችን ነው ካልን፣ በምንኖርበት ማሕበረሰብ ውስጥ እርስ በእርስ በምናደርገው መረዳዳት፣ ለሌሎች በምናቀርበው አገልግሎት ደስታን እና የውስጥ እርካታን ብቻ እንጂ እውቅናን ወይም የክፍያ ምላሽን መጠበቅ እንደሌለብን ኢየሱስ ያስተምረናል። ስለዚህ እናንተም የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፣ ‘ከቊጥር የማንገባ አገልጋዮች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን ተግባር ፈጽመናል በሉ” (ሉቃ. 17፤10)

ከቁጥር የማንገባ፣ ምስጋናንም የማንጠብቅ አገልጋዮች ሆነን ስንቀርብ አገልግሎትን በትህትና ለማበርከት መዘጋጀታችንን የሚያሳይ፣ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየንን የትህትና አገልግሎት ምሳሌ የምንገልጽ ስለሆነ ለቤተክርስቲያን ሕይወትም መልካም ምሳሌ ሆኖ ይቀርባል። እግዚአብሔር ዛሬ በእምነት ጉዞ ላይ ከእርሱ ለተቀበልነው ስጦታው ቀና እና ነጻ ምላሽን መስጠት ወይም አለመስጠትን እንድናረጋግጥ አጥብቆ ያሳስበናል።

ራሷን በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ አድርጋ ከራሷ ምርጫ ይልቅ የእግዚብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም የወደደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም (ሉቃ. 1፤48) እኛም በማሕበረሰባችን ውስጥ በእምነታችን በመታገዝ የትህትና አገልግሎትን ማበርከት እንድንችል ታግዘን”።

07 October 2019, 18:05