ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የዩክሬን ግሪክ-ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትን በተቀበሉበት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የዩክሬን ግሪክ-ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትን በተቀበሉበት ወቅት፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስን የሚመራው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አስገነዘቡ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከነሐሴ 27/2011 ዓ. ም. ጀምሮ በሮም ጳጳሳዊ ጉባኤያቸውን ለማካሄድ የተገኙን የዩክሬን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትን በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል። የግሪክ-ካቶሊካዊ ስርዓተ አምልኮን ለሚከተሉ የዩክሬን ብጹዓን ጳጳሳት ባሰሙት ንግግር፣ የብጹዓን ጳጳስት ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ እንጂ እንደ ሕዝባዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግለሰቦች ሃሳብ እና አስተያየት የሚንጸባረቅበት እንዳልሆነ አስገንዝበዋል። በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መካከል መንፈስ ቅዱስ ካልተገኘ የጳጳሳት ሲኖዶስም ሊኖር አይችልም ብለዋል። የቤተክርስቲያን ማንነት የሚታወቀው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ የወንጌል አገልግሎት ሲኖር ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቁጥር ወደ ሃምሳ ለሚጠጉ የዩክሬን የግሪክ-ካቶሊካዊ ስርዓተ አምልኮን ለሚከተሉ ብጹዓን ጳጳሳት እና ሲኖዶሱን በእንግድነት ለሚካፈሉ የሌሎች አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ባሰሙት ንግግር፣ የጳጳሳት ሲኖዶስ ከመንፈስ ቅዱስ የማይነጣጠል፣ የቤተክርስቲያን ሕልውና የሚገለጸው፣ የወንጌል አገልግሎትም ትክክለኛ መንገድን የሚያገኘው ከመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአጽንዖት ማስረዳታቸውን የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ፣ ዴቦራ ዶኒኒ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። በሮም ሊካሄድ በተጀመረው የዩክሬን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መሪ ቃል የግሪክ-ካቶሊካዊ ስርዓተ አምልኮን በምትከተል የዩክሬን ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ውስጥ “የጋራ የወንጌል ምስክርነት ሕይወት” የሚል እንደሆነ ዘገባው አክሎ አስታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለብጹዓን ጳጳስቱ ባሰሙት አጭር ንግግር፣ ከዚህ በፊትም ማለትም በሰኔ 28/2011 ዓ. ም. ስለ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አካሄድ የተናገሩትን በማስታወስ እንደተናገሩት፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ትክክለኛ ሂደት የሚረጋገጠው የግል አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን ይዘው ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው ወደ ስምምነት መድረስ እንዳልሆነ አስረድተው፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ትክክለኛነት የሚረጋገጠው ሁሉን አንድ የሚያደርግ እና የሚያስማማ፣ የመንፈስ ቅዱስ መሪነት ሲኖር ነው ብለዋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ፣ ሊነሱ በሚችሉ የተለያዩ አስተያየቶች እና ሃሳቦች ላይ ለየተናጠል ውይይቶችን ካደረጉ በኋላ ወደ ጉባኤው ሲደርሱ ስምምነቶችን ማጽደቅ ትክክለኛ የጳጳሳት ሲኖዶስ አካሄድ እንዳልሆነ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል በእርግጥ በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወቅት በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ መወያየት ይቻላል፤ ነገር ግን እንደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም እንደ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሕዝብ ጥያቄችን ለማስተናገድ እንደሚደረግ ጥረት፣ ይህን መቀየር የምንችል ከሆነ፣ ወይም ያንን ማስወገድ የሚቻል ከሆነ እየተባለ ውይይቶች እንደሚደረጉ አይደለም ብለዋል። በእርግጥ የምዕመናኖቻችሁን ሃሳብ ማወቅ ይኖርባችኋል፤ ይህ ማለት ደግሞ ሃሳባቸውን እንዴት ብለን እናስተናግድ በማለት የግል የመፍትሄ መንገዶችን መፈለግ እና ጥረቶችን ማድረግ አይደለም። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ከዚህ የተለየ ነው። መወያየት እና መጠያየቅ አስፈላጊ ቢሆንም መልስ የሚሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው። በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መካከል መንፈስ ቅዱስ ካልተገኘ የጳጳሳት ሲኖዶስ ሊኖር አይችልም፣ ቤተክርስቲያን ሊኖር አይችልም፣ የቤተክርስቲያን ሕልውናም ሊኖር አይችልም ብለውል።

መሪው መንፈስ ቅዱስ ነው፣

የቤተክርስቲያን ጥሪ ወንጌልን መመስከር ነው በማለት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ መናገራቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የቤተክርስቲያን ማንነት የሚታወቀው በወንጌል አገልግሎቷ ነው ብለዋል። ጳጳሳዊ ጉባኤያችሁን በመንፈስ ቅዱስ በመመራት አከናውኑ በማለት ለዩክሬን የግሪክ-ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ምክራቸውን የለገሱት ቅዱስነታችሁ ብጹዓን ጳጳሳቱ በጸሎት የመንፈስ ቅዱስን እገዛ እንዲጠይቁ አደራ ብለዋል። “የኤፌሶን ክርስቲያኖችን ተመልከቱ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በመጨረሻም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ የአምላክ እናት በማለት እንዲጠሯት ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ እንደነበር ገልጸዋል። ትክክለኛውን መንገድ የሚያሳየን መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ “የቤተክርስቲያንን አንድነት የሚጠብቅ መንፈስ ቅዱስ ነው” ብለው “እኛ ያለን በአንዲት ቤተክርስቲያን ስር የሚገኝ የብጿዓት ጳጳሳት ሲኖዶስ እንጂ በጉባኤዎች የተከፋፈለች ቤተክርስቲያን የለንም” ብለው ይህን መንገድ አጥብቀው በመያዝ ወደፊት እንዲራመዱ የዩክሬን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትን አሳስበዋል።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነት ማድረግ የሚቻል መሆኑን መመስከር ያስፈልጋል፣

የዩክሬን ግሪክ-ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ለጉባኤው ተካፋይ ብጹዓን ጳጳሳት ባቀረቡት የሰላምታ ንግግራቸው እንደገለጹት፣ የሲኖዶሳችን አቋም እና አንድነት የሚገለጠው በዚህ ጉባኤ ወቅት ብቻ ሳይሆን ወደ ሀገረ ስብከቶቻችን ስንመለስም የጸና እንዲሆን እንፈልጋለን ብለው፣ በሕብረት ለመጓዝ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነው ብለዋል። በዩክሬን የኬቭ-ሃሊክ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ በመጨረሻም ሀገራቸው ታላቅ የሐዋርያዊ እንቅስቃሴ ለውጥ እየታየ መምጣቱን ገልጸው፣ ለሺህ ዓመታት የዘለቀ የሩሶ-ኬቭ ጥንታዊ ስርዓተ አምልኮ ባህል፣ ከመጀመሪያው ዘመን ጀምሮ ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር አንድነቷ ጠብቃ የኖረች ቤተክርስቲያን እንዳለች መናገር ብቻ ሳይሆን ይህን አንድነት፣ ይህን ጥንታዊ የሐዋርያት ባሕልን ለዘመናችን ትውልድ ማሳየት እና ማብራራት መቻል ይኖርብናል ብለዋል። ከዘለዓለማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ዛሬም ቢሆን መገናኘት ይቻላል ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ በማከልም “መንፈስ ቅዱስ በዘመናችንም ቢሆን አብሮን ይጓዛል፣ ሥራውንም አላቋረጠም” ብለዋል።

03 September 2019, 15:56