ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ወደ ሙሉ ውህደት እንዲያመሩ አሳሰቡ።

በካቶሊካዊት እና በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናት መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ስነ መለኮታዊ ውይይት ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት  ለመግባባት የሚያደርጉትን ሲኖዶሳዊ ጥረት እያገዘ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው ይህን ያስታወቁት፣ የምስረታውን 50ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ ጉባኤ ላይ ለተገኙት የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሕግ ማኅበር አባላት መሆኑን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ዴቦራ ዶኒኒ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።     

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከምሥራቅ ካቶሊኮች ፣ ከኦርቶዶክስና ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ የመጡ በቁጥር 80 ለሚሆኑ የምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕግ ማኅበር አባላት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደገለጹት ማሕበሩ ከ50 ዓመታት ወዲህ የአብያተ ክርስቲያናትን ውህደት ለማፋጠን ሰፊ ጥናት ማድረጉን አስታውሰው በእነዚህ ዓመታት በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ከተደረጉ ስነመለኮታዊ፣ መንፈሳዊ ሕይወት እና ስርዓተ አምልኮ እንዲሁም የቤተክርስቲያንን ሕገ ቀኖናን ከተመለከቱ የጋራ ውይይቶች አንዱ ከሌላው ብዙ መማር የተቻለ መሆኑን አስታውሰው በተለይም የቤተክርስቲያን ሕገ ቀኖና፣ አብያተ ክርስቲያናት ለውህደት ለሚያደርጉት የጋራ ውይይቶች ትልቅ እገዛን ማበርከቱን አስረድተዋል።

ሕገ ቀኖና ለአብያተ ክርስቲያናት ውህደት የሚሰጠው ጥቅም፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም በሚገኘው የምስራቅ አብያተ  ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ተቋም ተገኝተው ለጉባኤው ተካፋዮች ባቀረቡት የሰላምታ ንግግራቸው እንደገለጹት፣ በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለ50 ዓመታት በተደረገው የጋራ ውይይት መካከል ሕገ ቀኖና ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ገልጸው ጠቀሜታውንም ለይቶ ለማወቅ የብጹዓን ጳጳሳት አንድነትን ወይም ሲኖዶስን መጥቀስ ያስፈልጋል ብለውል። ከሌሎች የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ልምድ ብዙ ባሕሎችን መማር እንደሚቻል የገለጹት ቅዱስነታቸው አክለውም የእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶሳዊ ሕይወት በክርስቲያን ምእመናን መካከል ያለውን መቀራረብ ለማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የምትመራ ቤተክርስቲያን መኖር የአብያተ ክርስቲያናትን ውህደት ለማምጣት እንደሚረዳ፣ በጎርጎሮሳዊያኑ 2015 ዓ. ም. የካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የደርጉትን ንግግር አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው በዚህ ንግግራቸው “የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የጋራ ሃብታቸን በሆነው በቤተክርስቲያን ሕገ ቀኖና ላይ ትኩረት በማድረግ በካቶሊካዊት እና በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርሲያናት መካከል የምናደረገው ስነ መለኮታዊ የጋራ ውይይት በቀዳሚነት ሲኖዶሳዊ የጋራ መግባባት ለማግኘት፣ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚገባ በማወቅ ለውህደት የሚደረገውን ጥረት ያሳድጋል። ውድ ወዳጆቼ! ሲኖዶሳዊ ባሕርን በመላበስ፣ በሕብረት ሆናችሁ የምታደርጉት ጉዞ እና መደማመጥ፣ በመካከላችሁ የምታደርጉት የባሕል እና የልምድ ልውውጥ ወደ ሙሉ ውህደት የምንደርስበትን መንገድ ለማግኘት ያግዛል። በሕብረት ሆናችሁ ለምታከናውኑት ጥናታዊ ሥራ ብስጋናዬን እያቀረብኩ ይህ ሥራችሁም ለቤተክርስቲያን ሕገ ቀኖና እድገት ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ ኢየሱስ ክርስቶስ “እነርሱም አንድ እንዲሆኑ” በማለት ወደ አባቱ ዘንድ ወዳቀረበው ጸሎት እንድንቀርብ ያግዘናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኣምሕበሩ አባላት ንግግራቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስተው ሕገ ቀኖና ለአብያተ ክርስቲያናት ውህደት አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበት፣ እስካሁን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከኦርቶዶክሳዊት እና ከምሥራቅ ኦርቶዶክሳዊት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ስታደርግ የቆየችው የውህደት ውይይቶች በቤተክርስቲያን ጥናቶች ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ሕገ ቀኖናዊ አቅጣጫም ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።           

የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሕግ ማኅበር፣ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በኋላ በ1961 ዓ. ም. የተመሠረተ መሆኑ ታውቋል። ማሕበሩን የመሠረቱት ክቡር አባ ኢቫን ዙዜክ ሲሆኑ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያንት ሕገ ቀኖና አንቀጾችን በማርቀቅ በርካታ ሥራዎችን ማበርከታቸው ታውቋል። ባሁኑ ወቅት ማሕበሩን በፕሬዚደንትነት የሚመሩት፣ የስነ መለኮት ሊቅ እና የሕገ ቀኖና መምህር ፕሮፌሰር አስትሪድ ካፕቲይን መሆናቸው ታውቋል። በሮም ከተማ ተገናኝተው 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩን በማክበራቸው የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በአጋጣሚው የማሕበሩን ምክትል ፕሬዚደንት እና የውሕደት ጎዳናን የሚከተሉ የቁንስጥንጢንያው ፓትሪያርክ፣ ብጹዕ ወቅዱስ ቤርቶሎሜዎስ ቀዳማዊን በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጳጳሳዊ መኖሪያቸው ማግኘታቸው ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸዋል። በቅድስት ማርታ ጳጳሳዊ መኖሪያ ውስጥ በተዘጋጀው ስነ ስርዓት ላይ በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች መካከል የስጦታ ልውውጥ የተደረገ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰኔ ወር 2011 ዓ. ም. ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ ስለ ላኩት መልዕክት ማብራሪያ የሰጡ መሆናቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

Pope Francis meeting participants in the congress of the Society for the Law of the Eastern Churches
20 September 2019, 17:06