ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከማዕከሉ ሕጻናት ጋር፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከማዕከሉ ሕጻናት ጋር፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በማፑቶ የ“ማቴዎስ 25” ማዕከልን ጎብኝተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞዛምቢክ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በወጣው መርሃ ግብር መሠረት፣ ትናንት ነሐሴ 30/2011 ዓ. ም. በዋና ከተማዋ ማፑቶ የሚገኘውን እና በሞዛምቢክ በሚገኝ የቅድስት መንበር ኤምባሲ የሚታገዝ የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናት እና ወጣቶች ዕርዳታ መስጫ ማዕከልን የጎበኙ መሆናቸውን፣ የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ፣ ሚኬለ ራቪያርት የላከልን ዘገባ አመልክቷል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ከሞዛምቢክ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ከዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና ከትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር ካደረጉት ቆይታ በኋላ በማፑቶ ከተማ፣ “ማቴዎስ 25” በመባል የሚታወቅ የወጣቶች እና ሕጻናት ዕርዳታ ማዕከልን ጎብኝተዋል። ማዕከሉ በማፑቶ ከተማ ውስጥ በጎዳና ተዳዳሪነት ለሚኖሩ ሕጻናት እና ወጣቶች ዕለታዊ ምግብን በማደል፣ የሕክምና እና የንጽሕና አገልግሎትን የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል።

ስሙን ከማቴዎስ የወንጌል ክፍል ያገኘው የወጣቶች እና ሕጻናት መርጃ ማዕከሉ በወንጌል ክፍሉ “እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ሲፈጠር ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፤ ምክንያቱም ተርቤ አብልታችሁኛል፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፣ እንግዳ ሆኔ ተቀብላችሁኛል፣ ታርዤ አልብሳችሁኛል፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛል፣ ታስሬ ጎብኝታችሁኛል (ማቴ. 25. 34-40) ተብሎ ከተጻፈው መሆኑ ታውቋል።

የስጦታ ልውውጥ፣

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ማዕከሉ ሲደርሱ የሞዛምቢክ ፕሬዚደንት ክቡር ፊሊፔ ናዩዚ አቀባበል ያደረጉላቸው መሆኑ ታውቋል። በማዕከሉ ውስጥ በሚገኝ ጸሎት ቤት በተከናወነው ስነ ስርዓት ላይ፣ ቅዱስነታቸው ወደ ማዕከሉ ላደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መታሰቢያ የሚሆን ድንጋይ ክቡር ፕሬዚደንት ፊሊፔ ናዩዚ መመረቃቸው ታውቋል። በመቀጠልም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ያለበትን ስጦታ ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለማዕከሉ መስጠታቸው ታውቋል።

በማዕከሉ ውስጥ የነበራቸው ቆይታ፣

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት በማዕከሉ ውስጥ አገልግሎት በማበርከት ላይ ያሉ  ደናግል እና ካህናት፣ ዕርዳታ የሚደረግላቸው ሕጻናት እና ወጣቶች፣ ከልዩ ልዩ የደናግል ማሕበራት አባላት ጋር የተገናኙ ሲሆን ከማዕከሉ ወጣቶች በኩልም የሙዚቃ ዝግጅቶች መቅረባቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
06 September 2019, 16:49