ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ትናንት ማምሻውን ወደ ሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ ደርሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሐዋርያዊ ግብኝታቸው የመጀመሪያ አገር ወደ ሆነችው ሞዛምቢክ በሰላም መድረሳቸዋን የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ ጃዳ አኲሊኖ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። 10 ሰዓት ከፈጀ በረራ በኋላ በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 1 ሰዓት ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ትናንት በሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ወደ ማፑቶ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የክብር አቀባበል ያደረጉላቸው የሞዛምቢክ ፕሬዚደንት ክቡር ፊሊፔ ናዩዚ፣ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር በመሆን እንደነበር ታውቋል። በአውሮፕላን ማረፊያው የተለያዩ አገሮች ልኡካን፣ የአገሩ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት እና በቁጥር በርካታ ምዕመናን የተገኙ ሲሆን ቅዱስነታቸውን በባሕላዊ ጭፈራዎች የተቀበሉ የተለያዩ ጎሳ አባላት መገኘታቸው ታውቋል።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ይህ 31ኛው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ቅዱስነታቸው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡበት ከመጋቢት 4/2005 ዓ. ም. ወዲህ በአፍሪካ አህጉር ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አራተኛው ሲሆን ከዚህ በፊት እ. አ. አ በ2015 ዓ. ም ወደ ኬኒያ፣ ኡጋንዳ እና የመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክን መጎበኘታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 29/2011 ዓ. ም ጀምሮ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ሦስቱም የአፍሪቃ አገሮች በከፍተኛ ጉጉት ሲጠባበቁት እንደነበር  ከየአገራቱ የደረሱን ዘገባዎች አመልክተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ጠዋት ወደ አፍሪቃ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ባስተላለፉት መልዕክት “የሁላችን አባት የሆነው እግዚአብሔር በአፍሪቃ ምድር ብቸኛውን የዘላቂ ሰላም ተስፋ የሆነውን የወንድማማችነት እርቅ እንዲያወርድን በሕብረት ሆነን እንጸልይ” በማለት አሳስበዋል። ወደ ሞዛንቢክ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተዘጋጀው መሪ ቃል “ተስፋ፣ ሰላም እና እርቅ” የሚል እንደሆነ ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞዛንቢክ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለበርካታ ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትሰቃይ ለነበርች ሞዛምቢክ የእርቅ እና የይቅርታን መንፈስ እንደሚፈጥር ተስፋ ተጥሎበታል። በሞዛንቢክ ላለፉት 15 ዓመታት ያህል የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ በርካታ ሕጻናትን፣ አረጋዊያን እና ሴቶችን ለአካል ጉዳት የዳረገ መሆኑ ታውቋል። በጦርነቱ ምክንያት ከ4 ሚልዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው፣ ቤት ንብረታቸውን መውደሙ እና በአጠቃላይ አውዳሚ እና ከፍተኛ ጉዳትን ያስከተለ መሆኑ ታውቋል። የእርስ በእርስ ጦርነት ማብቂያን ያገኝ ዘንድ፣ ሙሉ እርቅ እና ሰላም ይወርድ ዘንድ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት አዎንታዊ ገጽታ እንደሚኖረው መላው የአገሩ ሕዝብ ታላቅ ተስፋን ያደረገበት መሆኑ ታውቋል።

የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፣ በነሐሴ ወር ውስጥ በሞዛምቢክ መንግሥት እና በተቃዋሚው የሬናሞ ፓርቲ መካከል በቅርቡ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት፣ ተስፋን ሳይቆርጥ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ሁለቱን ወገኖች በማደራደር ትልቅ ሚናን የተጫወተው፣ ዋና ጽሕፈት ቤቱ በሮም ከተማ የሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር መሆኑን አስታውሰዋል።

ርዕሠ  ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር መሠረት ወደ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ በመጓዝ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የሚያደርጉ መሆናቸው ታውቋል።

05 September 2019, 09:01