ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርቶሎሜዎስን በተቀበሏቸው ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርቶሎሜዎስን በተቀበሏቸው ወቅት፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርቶሎሜዎስ ጋር መገናኘታቸው ተገለጸ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ትናንት ማክሰኞ መስከረም 6/2012 ዓ. ም. የውሕደት ጎዳናን ከሚከተሉት የቁንስጥንጢንያው ፓትሪያርክ፣ ከብጹዕ ወቅዱስ ቤርቶሎሜዎስን ቀዳማዊ ጋር በቫቲካን መገናኘታቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል። ትናንት በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መካከል የተደረገው ግንኙነት ወንድማዊነት ፍቅር የታየበት መሆኑን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አክሎ አስታውቋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በተዘጋጀው ስነ ስርዓት ላይ በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች መካከል የስጦታ ልውውጥ የተደረገ ሲሆን ቀጥሎም ከሁለቱ ወገኖች ልኡካን ጋር የምሳ ግብዣ ስነ ስርዓት መከናወኑ ታውቋል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ከመገናኘታቸው አስቀድመው ከቅድስት መንበር የካርዲናሎች መማክርት ጉባኤ ጋር ሰላምታ የተለዋወጡ ሲሆን በዚህም ወቅት ለካርዲናሎች ባሰሙት ንግግር በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ የቤተክርስቲያኒቱ ታላቅ እሴት መሆኑን ገልጸው፣ ፓትሪያርኩ በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን ለካርዲናሎች መማክርት አረጋግጠውላቸዋል።

የቅድስት መንበር ካርዲናሎች መማክርት ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርቶሎሜዎስ ጋር፣
የቅድስት መንበር ካርዲናሎች መማክርት ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርቶሎሜዎስ ጋር፣

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቁንስጥንጢንያው ፓትሪያርክ፣ ከብጹዕ ወቅዱስ ቤርቶሎሜዎስን ቀዳማዊ ጋር ትናንት ካደረጉት ግንኙነት አስቀድመው ከዚህ በፊት ለፓትሪያርኩ የላኩትን ስጦታ በማስመልከት ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡበት መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ. ም. በተከበረው ዓመታዊው የቅዱስ ጴጥሮስ ወ ጳውሎስ መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ ለፓትሪያርኩ የላኩት ስጦታ ከሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ቅዱስ አጽም መካከል የተወሰነ ክፍል መሆኑ ይታወሳል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤቶሎሜዎስ ከቅዱስነታቸው የተላከላቸውን ስጦታ ተቀብለው በቅዱስ እንድርያስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በክብር ማስቀመጣቸው ታውቋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርቶሎሜዎስ የላኩት የተወሰኑ የቅዱስ አጽም ስጦታ የሚያመለክተው  ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት እስካሁን በሕብረት ባደረጉት የወንድማማችነት ጉዞ ወደ አንድነት መቃረባቸውን ያመለክታል ብለዋል። ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ የተላከው ስጦታ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ መንበረ ታቦት ስር ከሚገኝ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ አጽም መካከል ዘጠኙን ወስደው በግል ጸሎት ቤታቸው ውስጥ በክብር ያስቀመጧቸው መሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካቶሊካዊት እና በቁንስጥንጢንያው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናት መካከል ሲካሄዱ የቆዩት መልካም የጋራ ውይይቶች ወደ ሙሉ ውህደት እያመራ መሆኑ ገልጸው፣ ከሃምሳ ዓመት በፊት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አጥናጎራስ ጋር በኢየሩሳሌም ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መልካም ውጤቶችን እያስገኘ በመሆኑ እግዚአብሔርን አመስግነው፣ በዚህ ታሪካዊ ጉብኝት ወቅትም ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አጥናጎራስ ለቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ ሁለቱ ወንድማማቾች፣ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ እንድሪያስ የሚታዩበትን ቅዱስ ምስል በስጦታ ማቅረባቸውን አስታውሰው “ይህም ሁለቱ የቤተክርስቲያን መሪዎች በእምነታቸው አንድ በመሆን ለፈጣሪያቸው ያላቸውን የጋራ ፍቅር ያመለክታል” ማለታቸው ይታወሳል።       

18 September 2019, 17:39