ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በማዳጋስካር ለከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ንግግር ሲያደርጉ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በማዳጋስካር ለከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ንግግር ሲያደርጉ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ለሁሉ አቀፍ እድገት የቆመ የፖለቲካ ሥርዓት ያስፈልጋል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማዳጋስካር ዋና ከተማ አንታናናሪቮ ለከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ለውጭ አገራት ዲፕሎማቶች እና ለሕዝባዊ ማሕበራዊ ተወካዮች ያደረጉት ንግግር ትርጉም እንደሚከተለው ይነበባል፥   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተከበሩ ፕሬዚደንት፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች እና ዲፕሎማቲክ አካላት፣ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች እና የሕዝባዊ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ክቡራት እና ክቡራን፣

ለማዳጋስካር ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት የከበረ ሰላምታዬን እያቀረብኩ፣ ይህን ውብ የሆነውን የማዳጋስካር ምድር እንድጎበኝ ስለጋበዙኝ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ለተደረገልኝም ደማቅ አቀባበል ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እንደዚሁም ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ለመንግሥት ምክር ቤት ተወካዮች እና ለዲፕሎማቲክ አካላት፣ እንዲሁም ለሕዝባዊ ማሕበራት ተወካዮች ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ለካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ለተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ወንድማዊ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ለዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝቴ መሳካት የበኩላቸውን ጥረት ላደረጉት፣ ከሁሉም በላይ ደማቅ አቀባበል ላደረገልኝ ለማዳጋስካር ሕዝብ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

በማዳጋስካር ሪፓብሊክ ሕገ መንግሥት ውስጥ የማዳጋስካርን ባሕላዊ እሴት የሚያስታውስ፣ የእርስ በእርስ መረዳዳትን እና የአንድነትን መንፈስ የሚያጎለብት አንቀጽ ተጠቅሶ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ የቤተሰብን ክብር፣ ወዳጅነትን፣ በሰዎች እና በተፈጥሮ መካከል ሊኖር ስለሚገባ መልካም መፈቃቀድ ተጠቅሶ ይገኛል። ይህም የማዳጋስካር ሕዝብ ማንነቱን ጠንቅቆ በማወቅ በየዕለቱ የሚደርስበትን ችግር እና መከራን ለመቋቋም ብዙ ጥረቶችን ማድረጉን ያመለክታል። በብዙ የተፈጥሮ ሃብት ስለ ታደለው እና ስለ ተቀደሰው የማዳጋስካር ምድር ማወቅ ካለብን የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባል የሆኑት አባ አንጦኒዮስ ዴ ፓዱ እንደተረዱት ሁሉ፣ የማዳጋስካርን ሕዝብ አንድ ላይ በማስተባበር በሕይወት ለመኖር ስላስቻላችሁ ባሕልም ማወቅ ይኖርብናል።

ማዳጋስካር ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት ጊዜ አንስቶ መረጋጋት እና ሰላም የነገሠባት አገር ናት። ፍሬያማ የሆነ የዴሞክራሲ ስርዓት የተዘረጋበት በመሆኑ የተለያዩ ተጨማሪ የማሕበራዊ ኑሮ አማራጮች እና እቅዶች ታይተዋል። ይህ ማለት ደግሞ ፖለቲካ በትክክል ሕዝብን ለማገልገል የቆመ ከሆነ ለማሕበራዊ ኑሮ ምሥረታ እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ያስረዳል። ሕዝብን በተለይም በማህበረሰቡ መካከል ለተቸገሩት እና እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች፣ እያንዳንዱ የማሕበርሰቡ ክፍል የእድገት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ከተፈለገ በፖለቲካ ስልጣን ላይ የሚገኙት ሰዎች የማያቋርጥ ጥረትን ይጠይቃል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እንደተናገሩት የአንድ አገር እድገት በኤኮኖሚ የተወሰነ ሳይሆን የእያንድንዱን ሰው እና ጠቅላላ ማሕበራዊ እድገት የማከለ መሆን ይኖርበታል ማለታቸው ይታወሳል።

በዚህ አጋጣሚ ለሁሉ አቀፍ ማሕበራዊ እድገት ጠንቅ የሆኑ እንቅፋቶችን መዋጋት እንደሚያስፈልግ፣ በተለይም ሙስናን እና ሕዝባዊ መረጋጋት እንዳይኖር የሚያደርጉ አመጾች እንዳይከሰቱ፣ ከፍተኛ የኑሮ አለ መመጣጠን እንዳይከሰት፣ በሕዝቦች መካከል መከፋፈል እንዳይኖር አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ላሳስብ እወዳለሁ። ይህን ማድረግ የሚቻል ከሆነ በሕዝቦች መካከል ፍትሃዊነት ያለው የተፈሮጥሮ ክፍፍል ማድረግ እንደሚቻል፣ በተለይም ደሃ የሆነውን የማሕበረሰብ ክፍል በማካተት የዕድገት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል። እድገት ማሕበራዊ ጥቅሞችን ለሕዝቡ ለማዳረስ በሚያስችሉ ውጥኖች ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ሕጋዊ መንገዶ የሚጠይቁትን ግዴታዎችን የሚፈጽም መሆን ይጠበቅበታል።

ሁሉ አቀፍ ማሕበራዊ እድገት በምንልበት ጊዜ ሌሎችንም የእድገት አቅጣጫዎችን እንድንመለከት ያስገድደናል። ከእነዚህ የእድገት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ ለጋራ መኖሪያ ለሆነች ምድራችን የምናደረገውን ጥበቃ እና እንክብካቤ የተመለከተ ይሆናል። የተፈጠሮ ጥበቃ እና እንክባካቤ ሲባል በአካባቢያችን ለምናያቸው ፍጥረታት የሚሰጥ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ሥርዓት እና በማሕበራዊ ኑሮ ሥርዓት መካከል ያለውን ጠቅላላ ግንኙነት በመረዳት አስፈላጊውን መፍትሄዎችን የምናገኝበትን መንገድ ይመለከታል። የተደቀኑብን ችግሮች ተፈጥሮአዊ እና ማሕበራዊ ሲሆኑ እነዚህ ችግሮች በተናጠል መታየት የለባቸውም።

ውብ የሆነች የማዳጋስካር ደሴት በዕጽዋዕት እና በእንስሳት ሕይወት በጣም ሃብታም ናት። ቢሆንም ይህ ሃብታችሁ አስፈላጊው እንክብካቤ ሳይደረግለት ቀርቶ በርካታ ስፍራዎች ወደ በረሃማነት እየተቀየሩ ይገኛል። ደኖች እየተጨፈጨፉ ጥቂት ሰዎች ብቻ ተጠቃሚ ሆነዋል። የተፈጥሮ መመናመን የአገራችንን እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ወደ ጥፋት እየመራት ይገኛል። እንደሚታወቀው በርካታ ደኖች የወደሙት በሰደድ እሳት እና ገደብ በሌለው ጭፍጨፋ ምክንያት ነው። ደኖች እና የዱር እንስሳት ለሕገ ወጥ የውጭ አገር ላኪዎች ተጋልጠዋል። ይህ ተግባር ለብዙ ዜጎች የመተዳደሪያ መንገዶችን እንዳመቻቸላቸው የሚካድ አይደለም። በተፈጥሮ ላይ ጉዳትን የማያስከትሉ፣ ለሰው ልጅ እድገት የሚረዱ፣ ገቢ ማግኛ የሥራ ዕድሎችን በብዛት ማመቻቸት ያስፈልጋል። ማሕበራዊ ፍትህን ያልተከተለ የተፈጥሮ ሃብትን ከጉዳት ለመጠበቅ የሚስችሉ ውጤታማ መንገድ አሁንም የለም ወደፊት አይኖርም።

ይህን በመገንዘብ በዚህ ሥፍራ የሚገኙ የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ተወካዮች፣ ሌሎችም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች መተባበር ያስፈልጋል። ለማዳጋስካር ልማት ተብሎ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚመደብ የገንዘብ መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። የማዳጋስካር ሕዝብ ዓለም አቀፉዊ የኤኮኖሚ መርህ በመከተሉ ለጉዳት የሚዳረግ መሆን የለበትም። የኤኮኖሚ ‘ግሎባላይዜሽን’ ስርዓት በተቻለ መጠን በፍትሃዊ መንገድ ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድ ካለ፣ ሰብዓው ክብርን የጠበቀ ከሆነ በእርግጥም የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ድጋፍ ለአንድ አገር እድገት ብቸኛ አማራጭ ሳይሆን እያንዳንዱ ነዋሪም የበኩሉን ድርሻ በመውሰድ በማሕበራዊ እድገት ለውጥን ማምጣት ይችላል።

ለሕዝባዊ ማሕበራት እና ድርጅቶች ትኩረት የምንሰጠውም በዚህ ምክንያት ነው። ማሕበራዊ እድገትን ለማምጣት ጥረት ለሚያደርጉት እገዛን በማድረግ፣ ድምጻቸው እንዳይሰማ የተደረጉትም ድምጻቸው እንዲሰማ፣ ልዩ ልዩ የማሕበረሰብ ክፍሎችም አንድነታቸው የሚረጋገጥበት መንገድ ሊመቻች ይችላል። በማሕበረሰብ መካከል መከፋፍል ሳይታይ የእድገትን ውጤት በጋራ የሚካፈሉበትን መንገድ እንድትከተሉ አደራ እላለሁ። 

እንደ ቤተክርስቲያ፣ ለጋራ ውይይቶች ቅድሚያን የሰጠች እና ፣ ከሰላሳ አመት በፊት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብጽዕናዋን ይፋ ያደረጉላት የዚህ አገር ተወላጅ ብጽዕት ቪክቶር ራሶ አማናሪቮን ፈለግ መከተል እንፈልጋለን። ለአገሯ ያላትን ፍቅር በመመስከር፣ እምነቷን በኢየስሱ ክርስቶስ በማድረግ ለደሆች ያበረከተችውን አገልግሎት እኛም እንድናበረክት እግዚአብሔር ያግዘን።

ክቡር ፕሬዚደንት፣ በማዳጋስካር ያለች ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ ከሌሎች አቢያተ ክርስቲያናት ጋር በምታደርገው የጋራ ውይይት በመታገዝ፣ በማዳጋስካር ሕዝብ መካከል እውነተኛ ወንድማማችነት እንዲኖር፣ ሁሉ አቀፍ ማሕበራዊ እድገትም እንዲመጣ የበኩሏን ጥረት ታደርጋለች። ይህን ተስፋ በማድረግ እግዚአብሔር አምላካችን ለማዳጋስካር ሕዝብ ሰላምን እንዲያበዛለት፣ እድገትን እና ደስታን እንዲያመጣለት በጸሎቴ እጠይቀዋልሁ” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአንታናናሪቮ ለከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች እና ዲፕሎማቶች፣ ለሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች እና ለሕዝባዊ ድርጅቶች ተወካዮች በሙሉ ንግግራቸውን አቅርበዋል። 

07 September 2019, 18:02