ብጹዕ ወቅዱስ ቤርቶሎሜዎስ ቀዳማዊወደ “የተሰጠኝ ገጸ-በረከት ለውህደታችን ከፍተኛ እገዛን ያደርጋል”። ብጹዕ ወቅዱስ ቤርቶሎሜዎስ ቀዳማዊወደ “የተሰጠኝ ገጸ-በረከት ለውህደታችን ከፍተኛ እገዛን ያደርጋል”። 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለፓትሪያርክ ቤርቶሎሜዎስ ስለላኩት ገጸ-በረከት ምንነት አስረዱ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የውሕደት ጎዳናን ለሚከተሉ የቁንስጥንጢንያው ፓትሪያርክ ለብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ በላኩት መልዕክታቸው፣ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ. ም. በተከበረው ዓመታዊው የቅዱስ ጴጥሮስ ወ ጳውሎስ መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ ለፓትሪያርኩ እንዲቀርብ የላኩትን ገጸ-በረከት በማስመልከት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውበታል። ቅዱስነታቸው ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ የላኩት ገጸ-በረከትም የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስ ቅዱስ አጽም ክፍል መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የገጸ-በረከቱ ዓላማ፣

ቅዱስነታቸው ለቁንስጥንጢንያው ፓትሪያርክ ለብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ በላኩት መልዕክታቸው፣ “ለረጅም ዘመናት ሳይቋረጥ በዘለቀው በሮም ቤተክርስቲያን ባሕል” መሠረት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ከሞተ በኋላ በቫቲካን ጉብታዎች መካከል በአንዱ መቀበሩን አስታውሰዋል። ከዚያም ሳይቆይ የቅዱስ ጴጥሮስ መካነ መቃብር ለመላው የዓለማችን ክርስቲያን ማሕበረሰብ የንግደት ስፍራ መሆኑን ገልጸው፣ ቀጥሎም ንጉሥ ቁንስጥንጢኖስ በመካነ መቃብሩ ላይ በሐዋርያው በቅዱስ ጴጥሮስ ስም ቤተክርስቲያን እንዲታነጽ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ቅዱስ አጽም ስለመገኘቱ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ በላኩት መልዕክታቸው፣ በሰኔ ወር 1931 ዓ. ም. የወቅቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ፣ ከስመተ ርዕሠ ሊቃነ ጵጵስናቸው ማግስት አሁን የሚታየው ባዚሊካ ከታነጸበት ቦታ ላይ የሚገኘው የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መካነ መቃብር እንዲቆፈር ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። ይህ የቁፋሮ ሥራ ከሁሉ አስቀድሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የተቀበረበት ትክክለኛ ስፍራ እንዲረጋገጥ ማድረጉን ገልጸው በ1944 ዓ. ም. ይፋ የሆነው የመካነ መቃብሩ ቁፋሮ ሥራ ውጤት መሠረት፣ በ150 ዓ. ም. በግሪክ ቋንቋ የተጻፈ እና “ጴጥሮስ እዚህ ነው” የሚል ጽሑፍ ያለበት እና አጽምን የያዘ ሳጥን መገኘቱን ገልጸዋል። በሳጥኑ ውስጥ የተገኙት አጽሞችም በበቂ ምክንያቶች በእርግጥም የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስ እንደሆኑ የታመነ መሆኑን አስረድተው የሐዋርያው ቅዱስ አጽም ባሁኑ ጊዜ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ መንበረ ታቦት ስር የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘጠኙ የአጽም ቁርጥራጮች፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ በላኩት መልዕክታቸው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ ከሐዋርያው ቅዱሳት አጽሞች መካከል በቁጥር ዘጠኙን ወስደው በጸሎት ቤታቸው በክብር እንዲቀመጡ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ዘጠኙ ቅዱሳት አጽሞች ከነሐስ በተሠራ ሳጥን ውስጥ መቀመጣቸውን እና እላዩ ላይ በላቲን ቋንቋ “እነዚህ ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ስር ከሚገኝ መካነ መቃብር ውስጥ ከነበሩ ቅዱሳት አጽሞች መካከል የተወሰዱ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ቅዱስ አጽሞች ናቸው” የሚል ጽሑፍ የሚነበብ መሆኑን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ በላኩት መልዕክታቸው በማከልም፣ የላኩላቸው ገጸ-በረክትም በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የግል ጸሎት ቤታቸው ውስጥ በክብር ተቀምጠው የነበሩ ዘጠኝ ቅዱሳት አጽሞች መሆናቸውን አረጋግጠውላቸዋል።

የፓትርያርኩ አጥናጎራስ ስጦታ።   

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካቶሊካዊት እና በቁንስጥንጢንያው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናት መካከል ሲካሄድ የቆየው መልካም የጋራ ውይይቶች ወደ ሙሉ ውህደት እያመራ መሆኑ ገልጸው፣ ከሃምሳ ዓመት በፊት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አጥናጎራስ ጋር በኢየሩሳሌም ለመገናኘት ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መልካም ውጤቶችን እያስገኘ በመሆኑ እግዚአብሔርን አመስግነው፣ በዚህ ታሪካዊ ጉብኝት ወቅትም ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አጥናጎራስ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ ሁለቱ ወንድማማቾች ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ እንድሪያስ የሚታዩበትን ቅዱስ ምስል ገጸ-መረከት ማቅረባቸውን አስታውሰው ይህም ሁለቱ የቤተክርስቲያን መሪዎች በእምነታቸው አንድ መሆናቸውን እና ለፈጣሪያቸው ያላቸውን የጋራ ፍቅር ያመለክታል ብለዋል።       

14 September 2019, 17:33