ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ከእግዚአብሔር ጋር ከሆንን ሐጢአት በሕይወታችን ውስጥ ሥፍራ የለውም”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሁድ መስከረም 4/2012 ዓ.ም፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ጋር በመሆን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አድረሰዋል። በዕለቱ ከሉቃ. ምዕ. 15:1-32 ተውስዶ በተነበበው የወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሰሙት ስብከታቸው “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለሆነ ፍርሃት ሊይዘን አይገባም፣ ሐጢአትም ዕድል የለውም ብለው በእግዚአብሔር ምሕረት ጠላታችን የሆነው ሰይጣን ተሸንፏል” ብለዋል። ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናንትናው ዕለት ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ፣

ከሉቃ. 15፤1-32 ተወስዶ የተነበበው የዛሬው የቅዱስ ወንጌል ንባብ፣ የኢየሱስን ትምህርት ለመስማት የተሰበሰቡት ቀራጮች እና ሃጢአተኞት በኢየሱስ ላይ የጀመሩትን ማጉረምረም በመጥቀስ ይጀምራል። እንዲህም አሉ፥ “ይህስ ሐጢአተኞችን ይቀበላል፣ ከእነርሱም ጋር አብሮ ይበላል”(የሉቃ. 15፤2)። ኢየሱስ ሐጢአተኞችን ይቀበላል፣ ከእነርሱም ጋር ይበላል የሚለው ሐረግ የኢየሱስን ማንነት ሌሎችም እንዲያውቁ ለማድረግ የተጠቀሙት አስደናቂ ንግግር ነው። እኛም ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ፣ በእያንዳንዱ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት የእርሱን ሥጋ እና ደም ለመቀበል እንቀርባለን። ራሱን ወደሚሰጠን ወደ እርሱ ማዕድ ስንቀርብ ኢየሱስ ደስ ይለዋል። በየአብያተ ክርስቲያናቱ በሮች ላይ “እዚህ ኢየሱስ ሐጢአተኞችን ይቀበላል፣ ወደ ማዕዱም ይጋብዛችኋል” የሚል ማስታወቂያ ጽፈን ማስቀመጥ እንችላለን። ኢየሱስ በእርሱ ላይ ያጉረመርሙ ለነበሩት፣ ከእርሱ እንደራቁ ለሚሰማቸው ሦስት አስደናቂ ምሳሌዎችን ተናግሯል። ዛሬ እያንዳንዳችሁ ቅዱስ ወንጌልን በመውሰድ፣ በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ 15 ላይ የተጻፉትን ሦስት አስደናቂ ምሳሌዎችን ብታነቧቸው ጥሩ ይሆን ነበር።  

በመጀመሪያ ምሳሌው እንዲህ ሲል ነገራቸው፥ ከእናንተ መቶ በግ ያለው ሰው አንድ በግ ቢጠፋበት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ዘጠና ዘጠኙን በዱር ትቶ ያን የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ሌፈልገው ይሄድ የለምን?”(15፤4) ለመሆኑ ከእናንተ መካከል ይህን የሚያደርግ ማን ነው? መልካም አስተሳሰብ ያለው ሰው ያቺን አንዷን በግ አጥቶ የተቀሩትን ዘጠና ዘጠኙን ማዳን ይመርጣል። ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲህ አያደርግም። እርሱ ላንተ ያለህ ፍቅር ምን ያህል ከፍተኛ መሆኑን ያላውቅህ ብትሆንም፣ እስካሁን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትህ መሠረት ያደረግክ ባትሆንም፣ ሐጢአትህን ማሸነፍ ያቃተህ ብትሆንም፣ በሕይወትህ ውስጥ ክፉ ገጠመኞች ኖሮህ በፍቅር የማታምን ብትሆንም፣ የእግዚአብሔር ፍቅር ወሰን ስለሌለው ብቻህን አይጥልህም ወይም አይተውህም። በሁለተኛ ምሳሌው፣ ጌታዋ ስትጠፋባት ሳያቋርጥ እንደምትፈልጋት ውድ የወርቅ መሐለቅ ስለሆንክ አንተ ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር እይታ ውስጥ ያለህ ብቸኛው ሰው ነህ። በእግዚአብሔር የፍቅር ልብ ውስጥ ሊተካህ የሚችል ሌላ ሰው የለም። በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ማንም ሊወስደው ወይም ሊተካህ የማይችል የግል ቦታ አለህ። እኔንም ቢሆን፣ በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ማንም ሰው ሊተካኝ አይችልም። በሦስተኛ ምሳሌው፣ እግዚአብሔር አባካኝ ልጁን ወደ እርሱ ተመልሶ እስኪመጣ በትዕግስት እንደሚጠብቅ አባት ነው። እግዚአብሔር ሳይሰለች ወደ እርሱ ተመልሰን የምንመጣበትን ጊዜ ዘወትር ይጠብቃል። ምክንያቱም እኛ አባቱ እጁን ዘርግቶ አቅፎት እንደተቀበለው አባካኝ ልጅ ነን፣ ጥፍታ እንደተገኘች ይወርቅ መሐለቅ ነን፣ ጠፍታ እንደተገኘች እና በትከሻው እንደተሸከማት በግ ነን። እግዚአብሔር ዘወትር የሚጠብቀው ፍቅሩን የምናውቅበትን ቀን ነው። “ብዙ ክፋትን ሠርቼአልሁ” ፣ “በብዙ ሐጢአት ወድቄአልሁ” እንል ይሆናል። ፍርሃት ሊይዝህ አይገባም፤ እግዚአብሔር እንደ ማንነትህ ይወድሃል፣ ምክንያቱም የእርሱ ፍቅር ብቻ ሕይወትህን ሊቀይረው እንደሚችል ያውቃልና።

በቅዱስ ወንጌል ውስጥ በቀዳሚነት የተገለጸውን እና ለእኛ ለሐጢአተኞች የቀረበውን የእግዚአብሔር ፍቅር ችላ እንል ይሆናል። ጠፍቶ በተገኘው ልጅ ምሳሌ ውስጥ፣ ታላቅ ወንድሙ ለታናሽ ወንድሙ የተደረገለትን ባየ ጊዜ በቁጣ የአባቱን ፍቅር ችላ ብሏል። ምህረት ከሚያደርግ አምልክ ይልቅ በሃብት በሚመካ አምላክ መተማመን፣ ክፋትን በምሕረት ከማሸነፍ ይልቅ በኃይል ለማሸነፍ በሚነሳ አምላክ የማመን ፈተና በእኛ ላይም ሊታይብን ይችላል። የእግዚአብሔር የማዳን ሃይል የሚገለጸው፣ ምህረቱንም የሚሰጠን በፍቅር እንጂ በሃይል አይደለም። ይህንንም የሚያደርገው ምርጫን በማቅረብ እንጂ በማስገደድ አይደለም። የአባቱን ምሕረት መቀበል ያልፈለገው ታላቅ ልጅ፣ ልቡን ዝግ በማድረጉ ራሱን ወደ ባሰ ስሕተት ውስጥ በመክተት፣ የራሱን አስተሳሰብ ብቻ መከተልን መረጠ። ይህን ባደረገ ጊዜ የበለጠ ከታናሽ ወንድሙ ጋር ወደ መጣላት ደርሷል። “ይህ ልጅህ ግን ሃብትህን ከአመንዝራ ሴቶች ጋር አባክኖ በተመለሰ ጊዜ የሰባውን ሰንጋ አረድክለት” (ሉቃ. 15፤30) በማለት ከአባቱም ጋር ተጣላ። ይህ ልጅህ ነው ያለው እንጂ ወንድሜ ብሎ ሊጠራውም አልፈለገም። በታናሽ ወንድሙ ላይ በመፍረድ፣ ትክክለኛው እና ብቸኛ ልጁ እርሱ ብቻ እንደሆነ ቆጠረ። ራሳችንን ብቻ ትክክለኛ እና መልካም አድርገን ስንቆጥር፣ ሌሎችን ግን ክፉዎች አድርገን በምንመለከትበት ጊዜ እኛም እንሳሳታለን። ሁል ጊዜ መልካም እና ትክክለኛ የሆነው የእግዚአብሔር እገዛ፣ ያለ እርሱ እርዳታ ብቻችን ሆነን ምንም መልካም ነገር ማከናወን አንችልም። ዛሬ ቅዱስ ወንጌልን ወስዳችሁ፣ በሉቃስ ወንጌል፣ በምዕ. 15 ላይ የተገለጹትን ሦስት ምሳሌዎችን ማንበብ ይኖርባችኋል። ይህ የወንጌል ክፍል መልካም ግንዛቤን በመስጠት ወደ መልካም መንገድ ይመራችኋል።

ክፋትን የምናሸንፈው እንዴት ነው? ክፋትን የምናሸንፈው በእግዚአብሔር ምሕረት በመታገዝ፣ ለበደሉን ሁሉ ምሕረትን በማድረግ ነው። ሐጢአታችንን ስንናዘዝ ክፉ ሥራዎቻችን በሙሉ የሚሸነፍበትን የእግዚአብሔር ፍቅር እንቀበላለን። በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ሐጢአታችንን ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ ይረሳዋል። እግዚአብሔር ምሕረቱን ሲሰጠን በደላችንን በሙሉ ይረሳዋል። እግዚአብሔር ስለሚወደን ፍቅሩን እውነተኛ ምሕረት በማድረግ ይገልጽልናል። እግዚአብሔር እንደ እኛ የሰዎችን በደል አይቆጥርም። ውስጣችንን ከሐጢአት በማንጻት፣ ከሐዘን፣ ከልብ መሰበር እና ከጥርጣሬ ተላቅቀን፣  በደስታ የተሞላን አዲስ ፍጥረት እንድንሆን ያደረገናል።

ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ በርቱ! ከእግዚአብሔር ጋር ከሆናችሁ ሐጢአት ምንም ዕድል የለውም። ችግሮቻችንን የምትፈታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ደንዳና የሆነውን ልባችን በማስወገድ፣ ምሕረቱን ሊሰጠን እጁን ዘርግቶ ዘወትር ወደሚጠብቀን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የምንቀርብበት ልብ እንድትሰጠን እንለምናታለን”።     

16 September 2019, 17:37