ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “እውነተኛ የትህትና መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረትን ይፈጥራል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች፣ በዕለቱ ከሉቃ. 14፡ 1. 7-14 ተውስዶ በተነበበው የወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። በዚህ የስብከተ ወንጌል አስተንትኗቸው “እውነተኛ የትህትና መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረትን ይፈጥራል”። ብለዋል። ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን ወደ ሚያቀርቡበት ስፍራ ከተለመደው ሰዓት አሳልፈው የተገኙት ቅዱስነታቸው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ደርሰው የሚጠብቋቸውን በርካታ ምዕመናን እና እንግዶች ይቅርታ ጠይቀው የዘገዩበትንም ምክንያት ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናንትናው ዕለት ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!

ከሁሉ አስቀድሜ፣ በየሳምንቱ እሑድ ከምንገኛኝበት የተለመደ ሰዓት፣ 25 ደቂቃን አሳልፌ በመምጣቴ ይቅርታን እጠይቃለሁ። ያረፈድኩትም የነበርኩበት የተንቀሳቃሽ መወጣጫ በሃይል ማነስ ምክንያት ስለተቆለፈብኝ ነው። እግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና 25 ደቂቃን ከፈጀው የጥገና ሥራ በኋላ በሰላም ልወጣ ችያለሁ። ስለዚህ ለእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች አንድ ጊዜ እናጨብጭብ።       

የዛሬው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ኢየሱስ በአንድ ፈሪሳዊ ቤት በተዘጋጀ ድግስ ላይ መገኘቱን እና ወደ ድግሱ የተጋበዙት አንዳንድ ሰዎች የከበሬታ ሥፍራን ለመያዝ ሲሽቀዳደሙ መመልከቱን ይነግረናል። የእነዚህን ሰዎች ሁኔታ የሚመስል፣ በሌሎች ሰዎች መካከል ራስን ከፍ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት፣ የበላይነትን ለማግኘት የሚደረግ መሽቀዳደም በዘመናችንም የሚታይ ተግባር ነው። በሕብረተሰብ መካከል ሆነ በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ ራስን ከሌሎች ከፍ አድርጎ ለማስቀመጥ የሚደረግ ጥረት፣ ማሕበራዊ የወንድማማችነት ሕይወትን የሚያበላሽ በመሆኑ መልካም አይደለም። ሰዎች ራሳቸውን በክብር ቦታ ላይ ለማስቀመጥ የሚያደርጉትን መሽቀዳደም አስመልክቶ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሁለት አጫጭር ምሳሌዎቹ አማካይነት መሠረታዊ የሆኑ የመልካም ስነ ምግባር መንገዶችን ያስተምረናል። እነርሱም ትህትና እና ራስ ወዳድነት የሌለበት ልግስና ናቸው።

የመጀመሪያው የኢየሱስ ምሳሌ የሚመለከተው በግብዣ መካከል ራሱን ወደ ከበሬታ ሥፍራ ውስዶ ያስቀመጠውን ሰው ይመለከታል። ኢየሱስ በምሳሌው ሲናገር፣ በተጋበዝክበት ግብዣ ላይ ራስን በቀዳሚ ሥፍራ ማስቀመጥ እንደማይገባ፣ ምክንያቱም ካንተ የሚበልጥ ሌላ ሰው ወደ ግብዣው በገባ ጊዜ፣ ሌላው ሳይሆን ያ የጋበዘህ ሰው ወደ አንተ በመምጣት፣ የተቀመጥክበትን ስፍራ ለቅቀህ ወደ ሌላ ሥፍራ እንድትሄድ ስለሚጠይቅህ እና በዚያን ጊዜ ከታላቅ ሃፍረት ጋር የመጨረሻውን ቦታ ለመያዝ እንድትሄድ ስለሚያደርግ ነው። “አንድ ሰው ለሠርግ ግብዣ ሲጠራህ ተሽቀዳድመህ በክብር ስፍራ አትቀመጥ። ምናልባት ካንተ የበለጠ ክብር ያለው ሰው ተጠርቶ ይሆናል። ታዲያ ሁለታችሁንም የጋበዛችሁ ሰው ወደ አንተ መጥቶ ይህን ስፍራ ለዚህ ሰው ልቀቅለት ይልሃል። ያን ጊዜ በታላቅ ሕፍረት ወደ ዝቅተኛ ቦታ ወርደህ ትቀመጣለህ” (ሉቃ. 14. 8 እና 9)። ነገር ግን ኢየሱስ ከዚህ በተለየ መልኩ ይህን እንድናደርግ ስተምረናል። “ነገር ግን ለግብዣ ስትጠራ ሄደህ በዝቅተኛ ስፍራ ተቀመጥ፤ በዚያን ጊዜ የጠራህ ሰው ወደ አንተ መጥቶ ‘ወዳጄ ሆይ ወደ ከፍተኛ ስፍራ ወጥተህ ተቀመጥ’ ይልሃል፤ ያን ጊዜም በሌሎች ተጋባዦች ሁሉ ፊት ክብር ታገኛለህ” (ሉቃ. 14. 10)። ስለዚህ በሌሎች መካከል ራሳችንን ከፍ ማድረግ ይቅርብን። የሚሻለው እኛ ለራሳችን ክብር ከመስጠት ይልቅ ሰዎች ቢያከብሩን ይመረጣል። ኢየሱስ ዘወትር የትህትናን መንገድ ያሳየናል፣ ያስተምረናል። ስለዚህ የእርሱን የትህትና መንገድ መማር ያስፈልጋል። ከሰዎች ጋር እውነተኛ ወዳጅነት ሊኖረን የሚያደርግ የትህትና ሕይወት ነውና። ትህትናችንም ከአንገት በላይ ሳይሆን እውነተኛ መሆን አለበት።

ኢየሱስ በሁለተኛው ምሳሌ፣ በበዓሉ ላይ እንዲገኙለት ብሎ የተለያዩ ሰዎችን የጋበዘውን ሰው ይመለከታል። እንዲህም ይላል፥ “ነገር ግን ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ደሆችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ሽባዎችን፣ እውሮችንም ጥራ፤ ይህን ብታደርግ እነርሱ ውለታ ለመክፈል ስለማይችሉ ትመሰግናለህ፤ በጻድቃን ትንሳኤ ጊዜ እግዚአብሔር ይከፍልሃል”። (ሉቃ. 14. 13-14)። በዚህ ምሳሌው ኢየሱስ ከተለመደው የግብዣ ዓይነት በተለየ መልኩ፣ ሰብዓዊ ሳይሆን መለኮታዊ የሆነውን የእግዚአብሔር መንገድ በተከተለ መልኩ ተናግሯል። ምሳሌውንም መረዳት እንድንችል በቁ. 14 ላይ “በጻድቃን ትንሳኤ ጊዜ እግዚአብሔር ይከፍልሃል” በማለት፣ በሰዎች መካከል ለተናቁት፣ ለተረሱት፣ ለተዋረዱት፣ ለደሄዩት ሁሉ በምድር ላይ ለምናደርገው መልካም ተግባር ሁሉ፣ ሰዎች ሊሰጡን ከሚችሉት ምስጋና ወይም ሊከፍሉን ከሚችሉት ውለታ መጠን እጅግ በላይ አድርጎ እግዚአብሔር እንደሚሰጠን ይናገረናል። ሰዎች ለሌሎች ሰዎች ለሚያደርጉት ውለታ ተመጣጣኝ ምላሽን ወይም ክፍያን ይጠብቁ ይሆናል። የዚህ ዓይነታ ውለታ ክርስቲያናዊ ውለታ ሊሆን አይችልም። ምላሽን የማይጠብቅ የትህትና ልግስና ነው ክርስቲያናዊ ሊሆን የሚችለው። ብዙን ጊዜ በስዎች መካከል የሚደረግ ውለታ፣ በቸርነት የተሞላ ነጻ ውለታ ሊሆን ሲገባው ወደ ጥቅም ያዘነበለ በመሆኑ የተነሳ የሰዎችን ግንኙነት የሐሰት ግንኙነት ያደርገዋል። ከዚህ በተለየ መልኩ፣ ታላቅ ደስታ የሚገኘው በእግዚአብሔር ፍቅር በመመራት፣ እርሱ አዘጋጅቶ ወደሚጠብቀን ወደ ሰማያዊው ግብዣ ለመድረስ በሚያስችለን መንገድ መራመድ ይኖርብናል።  

በትህትና የተሞላች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በሰዎች መካከል ራሳችንን ከፍ የምናደርግ ሳንሆን ዝቅተኞች መሆናችንን እንድናውቅ፣ በእውነተኛ ቸርነት ደስታን ማግኘት እንድንችል ትርዳን”።    

02 September 2019, 17:07