ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮ “ክርስቲያን ሁል ጊዜ ወደ ፊት መራመድ የገባዋል” ማለታቸው ተገለጸ።

ከሐምሌ 25-28/2011 ዓ.ም ድረስ የሚስዮናውያን አገር አቀፍ ጉባሄ በኢንዶኔዥያ በመካሄድ ላይ እንደ ሚገኝ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በእዚህ የሚስዮናዊያን ጉባሄ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቪዲዮ መልእክት ማስተላለፋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው “ክርስቲያን ሁል ጊዜ ወደ ፊት መራመድ ይገባዋል” ማለታቸው ተገልጹዋል። ይህ በኢንዶኔዢያ ዋና ከተማ በጃካርታ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጉባሄ “ምስጢረ ጥምቀት እና ተልዕኮ”  በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኝ ጉባሄ እንደ ሆነ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ምስጢረ ጥምቀት የተቀበልነው በግል ሕይወታችን ውስጥ ብቻ በተግባር ላይ በማዋል ለመኖር ብቻ ሳይሆን ነገር ግን “እንደ እርሾ በመሆን የኢየሱስን መልእክት በማሕበርሰቡ ውስጥ ለማዳረስ ጭምር ሊሆን ይገባዋል” ብለዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእዚህ በኢንዶኔዢያ ዋና ከተማ በጃካርታ ከሐምሌ 25-28/2011 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው የሚስዮናውያን ጉባሄ ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት አንድ ምስጢረ ጥምቀት የተቀበለ ክርስቲያን ሊኖረው ሰለሚገባው መንፈሳዊ ተልእኮ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ቅዱስነታቸው ለእዚህ የሚስዮናዊ ጉባሄ በተመረጠው “ምስጢረ ጥምቀት እና ተልዕኮ” በሚለው መሪ ቃል ላይ ተመርኩዘው ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን “እኛ ምስጢረ ጥምቀትን ስንቀበል በተመሳሳይ ጊዜ ውድ ሐብት የሆነውን መንፈስ ቅዱስን እንቀበላለን፣ የኢየሱስን መልእክት እንቀበላለን፣ ቅዱስ ወንጌል በውስጣችን ይጻፋል” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን “አንድ ሰው በውስጥ መልካም የሆነ ነገር እንዳለ ከተሰማው ያንን መልካም ነገር ለሌሎች ለማካፍል መነሳሳት ይኖርበታል” ብለዋል።

የተጠመቀ ሰው የማሕበረሰቡ እርሾ ነው

“ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበሉ ሰዎች ሁሉ በማሕበርሰቡ ውስጥ እንደ እርሾ ሆነው ማገልገል ይኖርባቸዋል” ያሉት ቅዱስነታቸው በእዚህም የተነሳ “የተቀበልኩትን ምስጢረ ጥምቀት በምን ዓይነት መልኩ ነው መኖር የሚገባኝ?” በማለት ለራሳችን ጥያቄ ማቅረብ እንደ ሚገባ የገለጹት ቅዱስነታቸው ምስጢረ ጥምቀት የተቀበሉ ክርስቲያኖች ሁሉ የተቀበሉትን ታላቅ ጸጋ በግል ሕይወታቸው እና በማሕበረሰቡ ውስጥ ሳይቀር በተግባር ላይ ለማዋል ጥረት ማደረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል። “ክርስቲያን ሁልጊዜም ቢሆን ወደ ፊት ሊራመድ ይገባዋል” በማለት በመልእክታቸው አጽኖት ሰጥተው የተናገሩት ቅዱስነታቸው “እኛ ክርስቲያኖች ወደ ኋላ የምንራመድ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳችን እንደ ሚለው ወደ ፊት መጓዝ ይኖርብናል” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን ወደ ኋላ የሚራመድ ግን ራሱን ክርስቲያን ነኝ ብሎ ለመናገር ይከብደዋል” ብለዋል።

ወደ ፊት እንድንጓዝ የሚገፋፋን መንፈስ ቅዱስ ነው

“ወደ ፊት እንድንጓዝ የሚረዳን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው” በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህም ምስጢረ ጥምቀትን በተቀበልንበት ወቅት የተቀበልነውን ጸጋ ለሌሎች ማካፈል እንችል ዘንድ ወደ ፊት የሚገፋን መንፈስ ቅዱስ ነው ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን “መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን ብርታት ታግዘን ወደ ፊት መጓዝ ይኖርብናል፣ ይህንን ተልዕኮ እውን ለማደረግ እንችል ዘንድ እንድትረዳን እና እንድትጠብቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት እና እርዳታ መማጸን ያስፈልጋል” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል። 

02 August 2019, 12:43