የደቡብ ሕንድ ነዋሪዎችን የጎዳው የጎርፍ አደጋ፣ የደቡብ ሕንድ ነዋሪዎችን የጎዳው የጎርፍ አደጋ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሕንድ የጎርፍ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡትን በጸሎታቸው ማስታወሳቸው ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በደቡብ ሕንድ፣ በተለያዩ ግዛቶች የጣለው ሃይለኛ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡትን በማስታወስ፣ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን የገለጹበትን መልዕክት፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ለሕንድ መንግሥት ባለ ስልጣናት መላካቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በደቡብ ሕንድ የጣለው ሃይለኛ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ እና የመሬት መደርመስ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡትን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። በአደጋው ቢያንስ 184 ሰዎች መሞታቸው፣ ከ400, 000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ታውቋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ፣ የደቡብ ክፍለ ሃገራት በሆኑት በኬራላ፣ ካራናታካ፣ ማራሽትራ እና ጉጃራት የጣለው ሃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ የበርካታ ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ፣ ቤት ንብረት እንዲወድም ማድረጉ ያሳዘናቸው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለአደጋው ሰለባ ለሆኑት ወላጆች እና ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እና ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣  በብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በኩል የተላከው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሐዘን መግለጫ መልዕከት፣ ቅዱስነታቸው በጎርፍ አደጋ ምክንያት በሐዘን እና በችግር ውስጥ ለወደቀው የሕንድ ሕዝብ በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ልከው መጽናናትንም የተመኙላቸው መሆኑን ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸዋል።            

የደቡብ ክፍለ ሃገር በሆነው በኬራላ ግዛት ጎርፉ ያደረሰው ጉዳት እጅግ የከፋ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በአካባቢው በአደጋው የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 76 መድረሱን፣ የአካል እና የንብረት ጉዳት የደረሰባቸውም 288,000 መሆናቸው ታውቋል። እንደዚሁም በካራናታካ ግዛት በደረሰው የጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 40 መድረሱን እና ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ወደ ሌላ ስፍራ እንዲዛወሩ የተደረጉት ሰዎች ቁጥር 582,000 መሆኑ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 August 2019, 17:14