ር. ሊ. ጳ. ፍራንቸስኮስ “የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበትን የቅዱስ ወንጌል ሕይወት መኖር ያስፈልጋል”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ነሐሴ 12 ቀን 2011 ዓ.ም፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ አብሮአቸው በመሆን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎትን ለማቅረብ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች፣ በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ከሉቃ. 12፡49-53 ላይ ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ንባብ በማስተንተን  ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ተተርጉሞ እንደሚከተለው ቀርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ፣

ከሉቃ. 12፡49-53 ላይ ተወስዶ የተነበበው የዛሬው የቅዱስ ወንጌል ክፍል፣ ሐዋርያቱ ውሳኔን የሚያደርጉበት የመጨረሻ ሰዓት መድረሱን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳሳሰባቸው ይናገራል። የእርሱ ወደ ዓለም መምጣትም፣ ሐዋርያቱ በቆራጥነት ተነስተው አገልግሎታቸውን ለማበርከት የሚያስችላቸውን ጠንካራ ውሳኔን ማድረግ ካለባቸው ወሳኝ ጊዜ ጋር አንድ ላይ ሆኗል። ሐዋርያቱም የወንጌል አገልግሎታቸውን በሌላ በምንም ዓይነት የአገልግሎት ዘርፍ መተካት የሚችሉበት ወቅት አልነበረም። ይህን መልዕክት በሚገባ ለመረዳት ከተፈለገ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ወደ ዓለም ያመጣውን እሳት መመልከት በቂ ይሆናል። ሐዋርያው ሉቃስ ኢየሱስ የተናገረውን እንዲህ በማለት ገልጾታል። “እነሆ እኔ በምድር ላይ እሳት አምጥቻለሁ፣ ታዲያ ቶሎ ቢቀጣጠልልኝ እንዴት በወደድኩ ነበር”። (ሉቃ 12፡49)። የኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የተናገረው፣ ሐዋርያቱን ወደ ኋላ ሊጎትት ወይም ሊያስቀር የሚችል ስንፍናን እና ግዴለሽነትን ወደ ጎን በመተው እንደ እሳት የሚያቃጥል የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲቀበሉ ለማድረግ ነው። ከእግዚአብሔር ስለ ተሰጠን ፍቅር ሐዋርያው ጳውሎስ በመልዕክቱ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል። “በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ሞላ ተስፋው አያሳፍርም” (ሮም 5፣5)። እግዚአብሔርን እና ባልንጀሮቻችንን እንድንወድ የሚያደርገን ሁላችን የተቀበልነው እና በውስጣችን የሚገኘው መንፈስ ቅዱስ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ የገለጠው ፍላጎቱ እና ምኞቱ፣ እኛም እንድናከናውነው የሚፈልገው ተግባር፣ የሰው ልጅ የዳነበትን የአባቱን ፍቅር ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ እንድናደርስ ነው። ይህን ፍቅሩን ወደ ዓለም ሁሉ በማዳረስ የእርሱ እውነተኛ ሐዋርያት መሆን እንችላለን። በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀጣጠለው የፍቅር እሳት ድንበር የሌለው ለመላው ዓለም የተላከ እሳት ነው። ከመጀመሪያዎች ክርስቲያኖች ጀምሮ በተግባር የታየው የወንጌል ምስክርነት፣ አገሮችን እና ሕዝቦችን በማቋረጥ፣ በሰዎች መካከል የሚታዩትን ማሕበራዊ ልዩነቶችን በማሸነፍ ሊዳረስ ችሏል። የወንጌል ምስክርነት በሰዎች መካከል የሚፈጠሩ ማንኛውም ልዩነቶችን በማስወገድ፣ ልግስና እንዲያድግ፣ በተለይም በችግር ላይ ለወደቁት፣ ለደሄዩት እና ከማሕበረሰቡ ለተገለሉት በሙሉ የሚደረግ ድጋፍ እና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም ያመጣው የፍቅር እሳት መላውን የሰው ልጅ የሚያዳርስ፣ ክብርን እና ውዳሴን ለእግዚአብሔር እንድናቀርብ የሚጠይቅ፣ ሌሎችን ለማገልገል ራሳችንን እንድናዘጋጅ የሚጋብዝ ነው።  እግዚአብሔርን ማወደስ እና ማክበር ማለት ደግሞ ባልንጀራችንን ለማገልገል ራስን ነጻ ማድረግ ማለት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ እግዚአብሔርን ማወደስ ማለት፣ ብዙን ጊዜ የምንዘነጋውን የወዳሴን ጸሎት መማር ማለት ነው። የውዳሴን ጸሎት እንድታዘወትሩ፣ መልካምነቱን እንድታውቁ የምጠይቃችሁ ለዚህ ነው።  በሁለተኛ ደረጃ እግዚአብሔርን ማወደስ ማለት፣ የእኛ ድጋፍ እና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለማገልገል ራስን ነጻ ማድረግ ነው። በዚህ የአውሮጳዊያኑ የበጋ ወራት በርካታ ወጣቶች በሚኖሩበት አካባቢ ሆነው ድሆችን፣ የታመሙትን፣ አቅመ ደካማ የሆኑ አረጋዊያንን እና የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች በመርዳት ላይ እንደሚገኙ አስባለሁ። እንደ ቅዱስ ቃሉ ለመኖር፣ የልግስናን አገልግሎትን በማበርከት ዓለማችንን የሚያጋጥማትን የተለያዩ ችግሮች ማቃለል የሚችሉ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዮች እንዲኖሩ ያስፈልጋል። በዚህ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ክብር እና ውዳሴን በማቅረብ፣ ባልንጀራንም በማገልገል፣ ዓለምን በመለወጥ ከጥፋት የሚያድን የፍቅር እሳት በተግባር ሊገለጥ የሚችለው ከእያንዳንዳችን የልብ መለወጥ በመነሳት ነው።

ከዚህም ጋር ሌላው እና ሁለተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ፍላጎት ከሉቃ. 12፡49-53 በተወሰደው ንባብ ውስጥ በቁጥር 51 ላይ የተጠቀሰው ሁለተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር፣ “እኔ በምድር ላይ ሰላምን ያመጣሁ ይመስላችኋልን? እኔስ ያመጣሁት መለያየትን እንጂ ሰላምን አይደለም፣ እላችኋለሁ” (ሉቃ. 12፡51)። ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ዓይነት መለያየትን ይዞ መጣ ቢባል፣ እርሱ ያመጣው መለያየት መልካምን ከክፉ፣ ትክክለኛውን አካሄድ ከተሳሳተ አካሄድ ለማለያየት ነው የመጣው። ትክክለኛውን ክርስቲያናዊ ሕይወት ከሌላ የተሳሳተ ዓለማዊ ሕይወት ጋር ያዋሄዱ ብዙዎች አሉ። በአንድ ወገን ክርስቲያን ነን እያሉ በሌላ ወገን ወደ ጣኦትን ለማምለክ የሄዱ ብዙዎች አሉ። እግዚአብሔር ይህን የመሰለ የሕይወት አካሄድ አይፈልግም። የግብዝነት ሕይወትን አይፈልግም፣ አይፈቅድም። በክርስትና ሕይወት መሻት ያለብን፣ እንደ ቅዱስ ቃሉ መኖርን ነው።  ክርስቲያን ነን ማለት ጥሩ ነው። ነገር ግን ክርስትናችንን የምንገልጸው በቃል ብቻ ሳይሆን፣ ለእግዚአብሔር እና ለባልንጀሮቻችን የምናሳየውን የወንጌል ፍቅርን በተግባር በመመስከር መሆን ያስፈልጋል።

የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ወደ ዓለም ሁሉ ይዘን የምንሄድበት ንጹሕ ልብ እንዲኖረን በማድረግ፣ ቆራጥ የሕይወት ምርጫን እንድናደርግ እና ለሌሎችም መልካም ምሳሌ የምንሆንበትን ሃይል በመስጠት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን”።

19 August 2019, 17:35