ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ደስተኛ ለመሆን አስተንትኖ ማደረግ እና ያስተነተነውን በተግባር ላይ ማዋል ይገባናል”።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰብሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው የቅዱስ ወንጌለ አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት በትላትናው እለት ማለትም በሐምሌ 14/2011 ዓ.ም ቅዱስነታቸው ያሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 10፡38-42 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና ኢየሱስ በማርታና በማርያም ቤት ያደረገውን ቆይታ በሚያመልክተው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በደስታ ለመኖር ከፈለግን አስተንትኖ ማደረግ እና ያስተነተነውን ነገር ደግሞ በተቀናጀ መልኩ በሕይወታችን መተግበር ይኖርብናል ብለዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለተ ሰንበት የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ከሉቃስ ወንጌል (10፡38-42) ላይ የተወሰደ ሲሆን ኢየሱስ የአልዓዛር እህቶች በሆኑት በማርታ እና በማርያም ቤት አድርጎት ሰለነበረው ጉብኝት ይገልጻል። እነርሱም ኢየሱስን በቤታቸው ተቀበሉት፣ በወቅቱ ማርያም ትሥራው የነበረውን ሥራ ትታ ኢየሱስ ይናገረው የነበረው ንግግር እንዳያመልጣት በማሰብ በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጣ ታዳምጠው ነበር። እርሱ በሕይወት ሂደት ውስጥ እኛን ሊጎበኘን በሚመጣበት ወቅት ሁሉንም ነገር ወደ ጎን ትተን እርሱን ማዳመጥ ይኖርብናል፣ ምክንያቱም የእርሱ ከእኛ ገር መሆን እና የእርሱ ቃል ከሁሉም ነገር መቅደም ይኖርበታልና። ጌታ ሁሌም ያስገርመናል: በእውነት እርሱን ማዳመጥ ስንጀምር በዙሪያችን ከቦን የነበረው ደመና በኖ ይጠፋል፣ ጥርጣሬዎቻችን ለእውነት መንገድ ይለቃሉ፣ ስጋቶቻችን ወይም ፍርሃቶቻችን ወደ መረጋጋት፣ እንዲሁም የተለያዩ የህይወት ሁኔታዎች በሙሉ በትክክለኛው ቦታቸው ላይ እንዲገኙ ያደርጋል። ጌታ ሁል ጊዜም ወደ እኛ በሚመጣበት ወቅቶች ሁሉ ነገሮችን በሙሉ በሚገባ ያስተካክልልናል።

የቢታኒያ አገር ተወላጅ የሆነችው ማርያም በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጣ እንደ ነበረ የሚያሳየው ትይንት ውስጥ ቅዱስ ሉቃስ የአንድ አማኝ የሆነ ሰው የጸሎት ምልከታ ምን መሆኑን ያሳያል፣ እሱም ጌታውን ማዳመጥ እና ከእርሱ ጋር ለመጣጣም ያለውን ፍላጎት ያሳያል። ይህ ጉዳይ የሚያመልክተው ደግሞ በእየለቱ እረፈት ማደረግ እንደ ሚገባን እና ለጥቂት ደቂቃዎች ያህል በጸጥታ በመቆየት በየቀኑ በአጠገባችን በማለፍ ለሚያበረታታንን ኢየሱስ በቂ የሆነ ሥፋር መስጠት እንደ ሚገባን የሚያሳይ ሲሆን ብርታትን እንዲሰጠን ከእርሱ ጋር ለየት ያለ ቆይታ እንዲኖረን፣ እርጋታ እንዲኖረን እና በእለት ተእለት ተግባራችን ውጤታማ እንድንሆን እንዲያደርገን ጭምር ይረዳናል።

እየሱስ እርሷ “የተሻለውን መርጣለች” በማለት ማሪያምን በማድነቅ፣ በተጨማሪም እያንዳንዳችን  “ነገሮችን በማከናውን ከመጠመድ ይልቅ የእርሱን ቃል ለማዳመጥ ቅድሚያ መስጠት እንደ ሚገባን፣ ‘ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት እና ጽድቁን እሹ’ ሌላው ተጫምሪ ነገር ይሰጣችኋል እንደ ሚለው ሁሉ እለታዊ የሆኑ ተግባሮቻችንን በሚገባ ማከናወን እንችል ዘንድ የጌታን ቃል በቅድሚያ ማዳመጥ እንደ ሚገባን” ይነግረናል።

የማርያም እህት የሆነች ማርታ የምትባል ሴት በእዚህ ታሪክ ውስጥ ትገኛለች። ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እንደ ገለጸው ኢየሱስን ወደ ቤት የጋበዘችሁ እርሷ እንደ ነበረች ይነግረናል። ምን አልባትም ማርታ የማርያም ታላቅ እህት ልትሆን ትችል ይሆናል። በእርግጥ ማርያም በኢየስሱ እግር ሥር ተቀምጣ ታዳምጥ በነበረበት ወቅት ማርታ ብዙ ሥራዎችን በማከናወን ጉድጉድ ትል ነበር። ለእዚህም ነው ታዲያ “ማርታ፣ ማርታ፤ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ” በማለት ኢየሱስ የተናግራት በእዚህ ምክንያት ነው። ኢየሱስ እነዚህን ቃላቶች የተጠቀመው የማርታን ሥራ ለመኮነን ፈልጎ ሳይሆን ይልቁንም አንዳንድ ጊዜ ከሚፈጠረው ጭንቀት ማረፍ እንደ ሚገባን ለመግለጽ ፈልጎ የተናገረው ቃል ነው። እኛም ብንሆን የቅድስት ማርታን ጭንቀት እና አብነት እንጋራለን፣ በቤተሰቦቻችን፣ በማህበረሰባችን ውስጥ ሳይቀር እርስ በእርስ የመቀባበል፣ የወንድማማችነት ባህል በማጸባረቅ ሁላችንም እንግዳ ሆነን የሄድንበት ቤት እንደ ቤታችን ሆኖ እንዲሰማን ማደረግ በተለይም አቅመ ደካማ የሆኑ እና ድሆች በሮቻችን በሚያንኳኩበት ወቅት ተቀብለን ማስተናገድ ይኖርብናል።

ስለሆነም የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የሚተርክልን ነገር ቢኖር የልብ ጥበብ የሚለካው አስተንትኖ እና ተግባር” የተሰኙትን ሁለት መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን አጣምሮ በተግባር ላይ ማዋል ላይ የተመሰረተ ነው። ማርታ እና ማርያም ይህንን መንገድ ያሳዩናል። ሕይወታችን በደስታ የተሞላ ጣዕም እንዲኖራት የምንፈልግ ከሆነ እነዚህን ሁለት መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን አጣምረን መተግበር ይኖርብናል፣ በአንድ በኩል “በኢየሱስ እግር ሥር መቀመጥ” ሁሉም ምስጢር ይገለጽልን ዘንድ ማዳመጥ የሚገባን ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለሰዎች የምናስብ እና እንግዳ ተቀባይ መሆን፣ እርሱ በበሮቻችን አጠገብ በሚያልፍበት እና በሚያንኳኳበት ወቅት፣ እርሱ የድሆችን የፊት ገጽታ ተላብሶ እረፍት እና የወንድማማችነት ፍቅር ፍለጋ በበራችን ላይ በሚመላለስበት ወቅት እርሱን ተቀብለን ማስተናገድ ይኖርብናል። የእዚህ ዓይነት መስተንግዶ ማድረግ ይኖርብናል።

የቤተክርስቲያን እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚኣብሔርን፣ እህት ወንድሞቻችን ማርያም በነበራት ዓይነት ልብ እና ማርታ በነበራት ዓይነት እጅ መውደድ እና ማገልገል እንችል ዘንድ ከልጇ ዘንድ ጸጋ እንድታስገኝልን ልንማጸናት የሚገባን ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስን በማዳመጥ የሰላም እና የተስፋ ሐዋርያ እንድንሆን ጭምር እንድትረዳን ልንማጸናት የገባል። ይህ ደግሞ በጣም አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ነው፣ በእነዚህ ሁለት አመለካከቶች የሰላም እና የተስፋ መሳሪያዎች መሆን እንችላለን።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
21 July 2019, 13:25