ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ወንድማዊነት ፍቅር የክፉ ሰዎችን አመጽ ያሸንፋል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአርጀንቲና ውስጥ በሚገኝ የአይሁድ እምነት ተከታዮች አንድነት ማሕበር አባላት ላይ ጥቃት የደረሰበትን 25ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ በላኩት መልዕክታቸው፣ ወንድማዊነት ፍቅር የእግዚአብሔርን ክብር የሚያሳንሱ ሰዎች የሚቀሰቅሱትን ማንኛውንም አመጽ ያሸንፋል ማለታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ዓርብ ሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ. ም. በአርጀንቲና ለሚገኝ የጋራ ማሕበር አባላት በላኩት የጽሁፍ መልዕክታቸው እንደገለጹት በየዓመቱ ሐምሌ 11 ቀን ከአደጋው ተጠቂ ሰዎች ቤተሰቦች፣ ከክርስቲያን እና ከአይሁድ እምነት ተከታዮች ጋር በጸሎት የሚተባበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሐይማኖት ስም የሚፈጸም አመጽ፣ በአመጹ ምክንያት የንጹሐን ሰዎች ሕይወት በከንቱ መጥፋት የእግዚአብሔርን ስም ማጥፋት እንደሆነ በአርጀንቲና ውስጥ ለሚገኝ የአይሁድ እምነት ተከታዮች አንድነት ማሕበር በላኩት መልዕክት አስረድተዋል። በሐምሌ 11 ቀን 1986 ዓ. ም. በርጀንቲና ዋና ከተማ በቦይነስ አይሬስ፣ ከ25 ዓመት በፊት ማለት ነው፣ በአይሁድ እምነት ተከታዮች ላይ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት 85 ሰዎች መገደላቸው ኣና ከ200 መቶ ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው እንደገለጹት ዕለቱ ማሕበሩ በከባድ ሐዘን ውስጥ የወደቀበትን፣  በሰብዓዊ ቤተሰብ መብቱ እና ግዴታ ላይ የተፈጸመዉን ጥቃት በድጋሚ የሚያስታውስበት ዕለት ነው ብለው፣ ጦርነትን የሚያነሳሳ እና ወደ ጦርነት የሚመራ ሃይማኖት ሳይሆን በጨለማ ውስጥ የሚገኝ የሰው ልብ የተሳሳተ ተግባር ነው ብለዋል።

በአርጀንቲና ጋዜጦችም ሊታተም የበቃው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት እንዳስገነዘበው ወይም ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው እንዳስገነዘቡት በየዓመቱ ከአደጋው ተጠቂ ሰዎች ቤተሰቦች፣ ክርስቲያኖች እና የአይሁድ እምነት ተከታዮች ጋር ሆነው በጥቃቱ ሕይወታቸውን ያጡትን በጸሎት የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸው የመቁሰል አደጋ ቢደርሳቸውም በሕይወት ሊተርፉ የበቁትን፣ ድንጋጤው እስካሁን ያልለቀቃቸውንም በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል። ይህን የመሰለ ጥቃት በአርጀንቲና ብቻ የተገደበ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በየቦታው የሚከሰቱት እነዚህ የአሸባሪዎች ጥቃት እንደ ሦስተኛ የዓለም ጦርነት ሊጠቀሱ የሚችሉ መሆናቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው ተመሳሳይ ጥቃት ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ባለ ትዳሮችን አንዱን ከሌላው በመለየት፣ ሕጻናትን ያለ ወላጅ በማስቀረት፣ ይህ ሁሉ የሚፈጸመው በእግዚአብሔር ስም እና የእግዚአብሔርን ስም በማርከስ እንደሆነ አስረድተው እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው፣ እኛም የተጠራንበት ሕይወት፣ የትም ይሁን የት በወንድማማችነት ፍቅር እንድንኖር ነው ብለዋል። ተራርቀን ብንኖርም አንድ ቤተሰብ አድርጎናል ብለው በሕብረት ያኖረንም ከሰብዓዊ ክብር እና ግዴታ ጋር እንደሆነ አስረድተዋል። በመሆኑም ሰላምን ማስከበር ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠን መብት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዳችን ግዴታ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል።        

13 July 2019, 16:44