ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ለኤርትራ ሕዝቦች እጸልያለሁ” አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 30/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመስርተው ካደረጉት አስተንትኖ በመቀጠል በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በመስጠት ከሚደገሙ ጸሎቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰውን “የእግዚኣብሔር መልአክ ማርያምን አበሰራት” የሚለውን ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኋላ እንደ ተለመደው ለመላው ዓለም ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት እንደ ገለጹት በቅርቡ በሊቢያ በሚገኘው አንድ የስደተኞች ጣቢያ ላይ በአንድ የጦር አውሮፕላን አማካይነት በተቃጣው የቦንብ ጥቃት ሕይወታችውን ላጡ እና ለቆሰሉ ስደተኞች የተሰማቸውን ሐዘን የገለጹ ሲሆን ዓለም አቀፉ ማኅበርሰብ እንደ እነዚህ ያሉትን አስከፊ እና ከፍተኛ የሆኑ ጥፋቶችን እያየ ዝም እንደ ማይል ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። በእዚህ ጥቃት ለሞቱ እና ለተጎዱ ሰዎች ሁሉ ጸልያለሁ፣ የሰላም አባት የሆነው እግዚኣብሔር በእዚህ ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ነፍስ በመንግሥቱ ያኖር  ዘንድ እና የተጎዱ ሰዎች ደግሞ በፍጥነት ያገግሙ ዘንድ እንዲረዳቸው ጸሎቴ ነው ብለዋል። ሰብዓዊ የሆነ እርዳታ ስጪ ተቋማት በእዚህ ጥቃት ለተጎዱ ሰዎች እንክብካቤ እንደ ሚያደርጉ ተስፋ አለኝ ብለዋል። በተመሳሳይ መልኩ በሚያሳዝን ሁኔታ በተቃጡ ጥቃቶች በአፍጋኒስታን፣ በማሊ፣ በቡርኪና ፋሶ እና በኒጄር በደረሱ ጥቃቶች ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን በማስታወስ ጸሎት ማደረግ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው ሳምንታዊ መልእክታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት በወቅቱ ከተለያየ አከባቢ የመጡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎችን ያመሰገኑ ሲሆን በተለይም በወቅቱ እዚያ ለነበሩ በርካታ ኤርትራዊያን ሰላምታ አቅርበው ለአገራችሁ ሕዝብ ጸሎቴን አቀርባለው ካሉ በኋላ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተው እና እንደ ተለመደው እባካችሁን ለእኔ መጸለይ እንዳትዘነጉ ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ሳምንታዊ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

07 July 2019, 17:13