ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የስደተኞች ጉዳይ ማኅበራዊ ሳይሆን ሰብዓዊ ነው” አሉ።

እ.አ.አ በሰኔ 8/2013 ላፓዱዛ በመባል በሚታወቀው በአንድ የጣሊያን የወደብ ከተማ አቅራቢያ የዛሬ ስደትስ አመት ገደማ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች የተነሳ ቤት ንብረታቸውን ጥለው በመሰደድ አደገኛ የሆኑ መንገዶችን በማለፍ በሊቢያ በኩል ወደ ጣሊያን በጀልባ ለመግባት ሲሞክሩ በነበረበት ወቅት በጀልባው ላይ በደርሰው አደጋ ከ3000 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ይህ አደጋ በዓለም ዙሪያ የመነጋገሪያ አርእስት ሆኖ ማለፉ ይታወሳል። በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አደጋው በደርሰበት ላፓዱዛ በመባል በምትታወቀው የጣሊያን የወደብ ከተማ ተገኝተው በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች ጸሎት ማደርጋቸው እና እንዲሁም ከእዚህ አስከፊ አደጋ በተዐምር የተረፉ ስደተኞች በተገኙበት መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ከእዚያን ጊዜ አንስቶ በእዚህ  አሰቃቂ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ስደተኞችን በማስታወስ በእየአመቱ መስዋተ ቅዳሴ እንደ ሚያሳርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረ በሊቢያ በኩል አድርገው ወደ ጣሊያን ለመሻገር በሚሞክሩበት ወቅት እ.አ.አ. ልክ የዛሬ 6 ዓመት ገደማ ላፓዱዛ በመባል በምታወቀው የጣሊያን የወደብ ከተማ አከባቢ ሕይወታችውን ላጡ ሰዎች ስድስተኛ አመት መታሰቢያ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሪነት በሐምሌ 01/2011 ዓ.ም መስዋዕተ ቅዳሴ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “የስደተኞች ጉዳይ ማኅበራዊ ሳይሆን ሰብዓዊ ነው”  ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የዛሬ የእግዚአብሔር ቃል ስለ መዳን እና ነፃነት ይናገራል።

ደህንነት። ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ወደ ካራን በሚጓዙዝበት ወቅት በአንድ ገለልተኛ ቦታ ላይ ቆም ብሎ ለማረፍ ይወስናል። በሕልሙ እግሮቹን በምድር ላይ ጫፉ ደግሞ እስከ ሰማይ ዘልቆ ከሰማይ ጋር የተገናኘ አንድ መሰላል ያያል (ኦዘፍ 28፡10-22)። የእግዚአብሔር መልአክት ወደ ታች የሚወርዱበት እና ወደ ላይ የሚወጡበት መሰላል ሲሆን መለኮታዊ የሆነው ኃይል ከሰው ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያመለክት ሲሆን የአብ የፍቅር ስጦታ የሆነውን የመገለጥ እና የደኅንነት ስጦታ የሆነውን በታሪክ ውስጥ በክርስቶስ ሥጋ መልበስ የተነሳ የተፈጸመውን ትስስር የሚያመልክት ነው። መሰላሉ ሁሉንም የሰው ልጆች እንቅስቃሴ የሚቀድስ መለኮታዊ ድርጊት ምሳሌ ነው። ሰዎች በራሳቸው ኃይል እና ጥንካሬ ገንብተው ወደ ሰማይ ወጥተው ራሳቸው አምላክ ለመሆን ፈልገው ከገነቡት ከባቢሎን ግንብ የተለየ ነው። በዚህ ሁኔታ ግን ወደ ታች የሚወረደው እግዚአብሔር ነው፣ እራሱን የሚገልጸው ጌታ ራሱ ነው፣ የሚያድነውም እግዚአብሔር ራሱ ነው። አማኑኤል (እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ነው) በጌታ እና በሰው ዘር መካከል የተገባው የጋራ ቃል ኪዳን እንዲፈጸም ያደርጋል፣ ይህም የተትረፈረፈ ህይወት የሚሰጥ እና መሐሪ የሆነ የፍቅር ምልክት ነው።

ከዚህ ራዕይ ጋር ፊት ለፊት በተጋፈጠበት ወቅት ያዕቆብ በጌታ ላይ እምነቱን አደረገ፣ ይህም በደኅንነት ታሪክ ውስጥ ወሳኝ የሆነ ጊዜ ሲሆን ለሁኔታው እውቅና በመስጠት አምልኮ የጀመረበት ወቅት ነው። በእዚህ በማድረግ ላይ በሚገኘው አስቸጋሪ ጉዞ ላይ ጌታ እንዲረዳው “ወደ አባቴ ቤት በደኅና ቢመልሰኝ፣ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆናል” (ኦዘፍ. 28፡21) በማለት ይጠይቃል።

በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ አባቶቻችን ያሉትን ቃል በመድገም "አምላኬ ሆይ በአንተ እታመናለሁ" ብለን ነበር። እርሱ የእኛ መሸሸጊያ እና ብርታታችን፣ ጋሻችን እና የጦር መከታችን፣ በመከራችን ጊዜ መልህቃችን ነው። ጌታ በመከራ ወቅት እርሱን ለሚጠሩት ሰዎች ሁሉ መሸሸጊያ ነው። በእርግጥ ጸሎታችን ይበልጡኑ ንጹህ የሚሆነው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ በምንገባበት ወቅት ሲሆን ዓለም የሚያቀርበው ደህንነት ብዙ ዋጋ እንደ ሌለው ስንገነዘብ ቀሪ መሸሸጊያችን የሚሆነው እግዚአብሔር ብቻ ነው። በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች መንግሥተ ሰማይ የሚከፍተው እግዚኣብሔር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያድነው።

ይህ አጠቃላይ የሆነ እና ሙሉ በሙሉ በእግዚኣብሔር ላይ የተጣለው እምነት በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ልጁ የሞተችበት አንድ ሹም እና አንዲት የታመመች ሴት በሙክራብ ኢየሱስን ከተገናኙበት ሁኔታ ጋር ይዛመዳል (ማቴ 9፡18-26)። እነዚህ የነጻነት ትዕይንቶች ናቸው። ሁለቱም ማንም ሊሰጣቸው የማይችለውን ከእሱ ለማግኘት ወደ ኢየሱስ የቀረቡ ሲሆን: ከበሽታና ከሞት ነፃ መውጣት በማሰብ ወደ ኢየሱስ ይቀርባሉ። በአንድ በኩል የከተማዋ ሹም ሴት ልጅ ትገኛለች፣ በሌላው በኩል ደግሞ በሽታዋ የተነሳ ከሌሎች ሰዎች የተገለለች፣ የተናቀች፣ ንጹህ እንዳልሆንቸ ተደርጋ የምትቆጠር ሴት ትገኛለች። ኢየሱስ ግን ምንም ዓይነት ልዩነት አላሳየም፣ ነጻነት ለሁለትም በርኅራኄ መንፈስ ተሰጣቸው። ሁለትም ሴቶች ከነበሩበት ሁኔታ ለመውጣት የነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት እንዲወደዱ እና ከወደቁበት እንዲነሱ ምክንያት ሆኖዋቸዋል።

ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ በትንሹ ለየት ያለ አማራጭ እንደሚያስፈልጋቸው ገለፀላቸው፣ በበጎ አድራጎት ሥራ ወይም ተግባር ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው እነ ማን እንደ ሆኑ ያሳያቸዋል። ዛሬ ብዙ ዓይነት ድሆች አሉ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ይህንን በተመለከተ እንደ ጻፉት “ድሆች በተለያዩ ተጽህኖ ሥር የሚገኙ፣ በማኅበርሰቡ የተገለሉ፣ ጠያቂ የሌላቸው በእድሜ የገፉ አዛውንቶች፣ የታመሙ ሰዎች፣ ወጣት የሆኑ እና በሁሉም ሰዎች ዘንድ የተናቁ ሰዎችን ያካትታል” ብለው ነበር።

ላፓዱዛን ከጎበኘውበት ከስድስት አመታት በኋላ በእየለቱ ወደ እግዚኣብሔር ለቅሶዋቸውን የሚያቀርቡ “ሚስኪን” የሚል መጠሪያ የተሰጣቸውን ሰዎች እያሰብኩ እግዚኣብሔር ከእዚህ ከተደቀነባቸው መጥፎ አደጋ ይታደጋቸው ዘንድ ጸሎቴ ነው። እነዚህ “ሚስኪን” የሆኑ ሰዎች ተረሰተዋል በማታለል እና በውሸት በበራሃ ውስጥ በስቃይ እንዲያልፉ ተደርገዋል፣ እነዚህ “ሚስኪን” ሰዎች ተገርፈዋል፣ በእስረኞች ካምፖች ውስጥ ታጉረው ተሰቃይተዋል፣ እነዚህ ምሲክን የሆኑ ስደተኞች ምሕረት የለሽ በሆነው የባሕር ሞገድ ተመተዋል፣ ሞተዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ እነዚህ ሚስኪን የሆኑ ሰዎች በስደተኛ ማጎሪያ ካፖች ውስጥ ጊዜያዊ ፈቃድ ሳይሰጣቸው ለረዥም ጊዜ ታጉረው ኑረዋል። እነደንዚህ ዓይነቱን ምሲክን የሆኑ ሰዎችን እንድንወድ እና እንድናነሳቸው ኢየሱስ ይጠይቀናል። በሚያሳዝን ሁኔታ በከተሞቻችን ጥግ ወይም ጫፍ ላይ የሚገኙ ሕንፃዎች በእነዚህ በተጣሉ፣ በተበዘበዙ፣ በተረሱ በተጨቆኑ በድሆች እና በሚሰቃዩ ሰዎች የተሞሉ ናቸው። ኢየሱስ በተራራው ላይ ባደርገው ስብከት የምሕረት መንፈስ ተሞልተን እነዚህን ሰዎች ልናጽናናቸው ይገባል፣ ለፍትህ ያላቸውን ረሃብ እና ጥማት ማርካት ይኖርብናል፣ የእግዚኣብሔርን አባትዊ እንክብካቤ ይቋደሱ ዘንድ ልንረዳቸው የገባል፣ ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚወስደውን መንገድ ልናሳቸውም ይገባል። እነርሱ የሰው ልጆች ናቸው፣ ይህ ጉዳይ ማኅበራዊ ወይም የስደተኞችን ጉዳይ ቢቻ የሚያመልክት ሁኔታ አይደለም። “ይህ ሰደተኞችን ብቻ የሚመለከት ጉድያ አይደለም” ይህንን በአጠቃላይ ስንምለከተው በቅድሚያ ስደተኞ የሰው ልጆች በመሆናቸው የተነሳ በዛሬው ዓለም አቀፍ ማኅበርሰብ ውስጥ የተገለሉ ሰዎችን ሁሉ የሚወክሉ ናቸው።

በእዚህ ረገድ ያዕቆብ በሕልሙ በራይ ወዳየው መሰላል እንመለስ። በክርስቶስ አማካይነት በሰማይ እና በምድር መካከል ያለው የመገናኛ መስመር አሰተማማኝ በሆነ መልኩ መከፈቱን ያሳያል፣ ይህም መስመር ለሁሉ ሰዎች ተደራሽ የሆነ መስመር ነው። ወደ ታች የሚወርዱት እና ወደ ላይ የሚወጡ መላእክት በክንፋቸው ከለላ ውስጥ ሚስኪን የተባሉ ሰዎችን፣ የተማሙ ሰዎችን፣ የተገለሉ ሰዎችን ይዘው እንደ ሚሄዱ አድርጌ አስባለሁ።

ይህ ደግሞ የሁሉ የሰው ልጆች ላይ የተጣለ ታላቅ ኃላፊነት ሲሆን ጌታ ራሱ የፈጸመውን እና እኛም ከእርሱ ጋር በእዚህ ተግባር ተባብረን እንድንሠራ የሰጠን የማዳን እና ነጻ የማውጣት ተልዕኮ የተጣለብን ታላቅ ኃላፊነት ነው። እናንተ ዛሬ እዚህ የተገኛችሁ ስደተኞች ከመጣችሁ ብዙ ጊዜ የሆናችሁ አይመስለኝም፣ ነገር ግን ከእናንተ በኋላ የመጡትን ስደተኞ እያገዛችሁ እንደ ሆነ አውቃለሁ። በእዚህ ረገድ እያሳችሁት ለምትገኙት በጎ ሰብዓዊ ተግባር ላመሰግናችሁ እፈልጋለሁ።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ስደተኞች በተገኙበት መስዋዕተ ቅዳሴ ባደረጉበት ወቅት
08 July 2019, 17:16