የኢድሊብ ከተማ እና አካባቢዋ ጥቃት፣  የኢድሊብ ከተማ እና አካባቢዋ ጥቃት፣  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሶርያ ሕዝብ በጎ እንዲደረግለት ተማጸኑ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለሶርያው ፕሬዚደንት ለአቶ በሽር አል አሳድ በላኩት መልዕክት በሶሪያ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም፣ በከንቱ የሚጠፋውን የሰው ሕይወት ለመታደግ ተጨባጭ ተነሳሽነትን እንዲያደርጉ ተማጽነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ላለፉት ስምንት ዓመታት ጦርነት እና አመጽ ባልተለያት ሶርያ ውስጥ የቦምብ ጥቃቶች ቀጥለው የሰው ሕይወት እየጠፋ፣ ንብረት እየወደመ በዚህም ምክንያት በኢድሊብ ከተማ እና አካባቢዋ የሚገኙ ወደ አስር የሚሆኑ የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መዘጋታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው እንደገለጹት ሕዝቡን ከሞት እና ከመቁሰል አደጋ እንዲተርፍ፣ የኢድሊብ ከተማ እና አካባቢዋ ሕዝብ ከመኖሪያው ቤቱ እንዳይፈናቀል፣ ከዚህ በፊት የተፈናቀሉትም ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙት ነጻ እንዲወጡ፣ በእስር የሚቆዩትም ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ዕድል እንዲያገኙ፣ የፖለቲካ እስረኞችም ሰብአዊ መብታቸው እንዲከብርላቸው እና ሊደረግላቸው የሚገባ እንክብካቤ እንዳይጎድልባቸው የሶርያው ፕሬዚደንት አቶ በሽር አል አሳድ ለሕዝባቸው በጎን በማድረግ እንዲተባበሩ አሳስበዋል። ጉዳዩ ከሚመለከታቸው እና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብን የሚያሳትፍ ውይይት ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መቅረብ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሶርያው ፕሬዚደንት አቶ በሽር አል አሳድ የላኩት መልዕክት ጭብጦች እነዚህ መሆናቸውን የቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባ አንድሬያ ቶርኔሊ የላከልን ዘገባ አስረድቷል።          

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ሰኔ 21/2011 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን በኩል ለሶርያው ፕሬዚደንት አቶ በሽር አል አሳድ የተላከላቸውን መልዕክት ፕሬዚደንቱ ትናንት ሐምሌ 15/2011 ዓ. ም. መቀበላቸው ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ያደረሱት ክቡር አባ ኒኮላ ሪካርዲ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ እና ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ፣ በሶርያ የቅድስት መንበር እንደራሴ መሆናቸውን የቫቲካን የዜና አገልግሎት አስታውቋል። የቫቲካን የዜና አገልግሎ በማከልም የቅዱስነታቸውን መልዕክትን አስመልክቶ ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ከብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ጋር ቃለ ምልልስ ማድረጉንም አስታውቋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የቅዱስነታቸውን መልዕክት መነሻ በማድረግ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ለሶርያ ሕዝብ አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ማስፈለጉ እና የኢድሊብ ከተማ እና አካባቢዋ ሕዝብ የሚገኝበት አስከፊ ሁኔታ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እና ቅድስት መንበርን ያሳሰባቸው መሆኑን አስረድተዋል። የኢድሊብ ከተማ እና አካባቢዋ ሕዝብ ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን በላይ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ከእነዚህ መካከል 1.3 የሚሆነው ደግሞ እስካሁን በሶሪያ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ከመኖሪያው ተፈናቅሎ ያለፈው ዓመት ከወታደራዊ ቀጠና ነጻ በተደረገው አካባቢ እንዲቀመጥ የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። በእነዚህ ተፈናቃዮች ላይ በቅርቡ የተፈጸመው ጥቃት የነበሩበትን የመከራ ሕይወት የባሰ በማድረጉ ብዙዎች ሥፍራውን ለቀው ወደ ሌላ ሥፍራ እንዲሸሹ ማድረጉን ካርዲናል ፓሮልን አክለው ገልጸዋል። ሕዝቡ የሚገኝበት ሁኔታ እና በጦርነቱ ምክንያት በሕጻናቱ ላይ የሚፈጠር ድንጋጤ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እጅግ ማሳሰቡን ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸዋል። በአካባቢው ጦርነቱ እንደቀጠለ፣ የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላትም ሙሉ በሙሉ አንዳንዶችም በከፊል በመውደማቸው ምክንያት ዕርዳታ ለሚያስፈልገው የአካባቢው ሕዝብ ምንም ዓይነት አገልግሎት መስጠት የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሶርያው ፕሬዚደንት አቶ በሽር አል አሳድ የሚያቀርቡትን ተማጽኖ ማሳደሳቸውን የገለጹት ካርዲናል ፓሮሊን ቅዱስነታቸው በአዲሱ ተማጽኖአቸው በኩል የሰው ሕይወት በከንቱ እንዳጠፋ፣ ንብረት እንዳይወድም፣ ዋና ዋና የሆኑ መሠረተ ልማቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና የጤና ጣቢያዎች እንዳይወድሙ መጠየቃቸውን እና በሶሪያ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም፣ በከንቱ የሚጠፋውን የሰው ሕይወት ለመታደግ ተጨባጭ ተነሳሽነትን እንዲያሳዩ የሶርያውን ፕሬዚደንት አቶ በሽር አል አሳድን መጠየቃቸውን እና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው መጠየቃቸውን ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል።            

ከረጅም ዓመታት ጦርነት በኋላ በሶርያ ሕዝብ መካከል ጥላቻ ተወግዶ እርቅ እንዲደረግ፣ ሰላም እንዲነግሥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ጸሎት እና ምኞት መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ፕሬዚደንት በሽር አል አሳድ በሕዝባቸው መካከል እርቅ እና ሰላም እንዲወርድ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትም እንዲመለሱ በማመቻቸት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ በማበረታታት ላይ መሆናቸውን ገልጸው በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙት ቤተሰቦች ነጻ እንዲወጡ፣ የፖለቲካ እስረኞችም ሰብአዊ መብታቸው እንዲከብርላቸው እና ሊደረግላቸው የሚገባ እንክብካቤ እንዳይጎድልባቸው ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

ገለልተኛው ዓለም አቀፍ መርማሪ ኮሚሽን በየካቲት ወር 2010 ዓ. ም. የሶርያን ሁኔታ በማጣራት ባቀረበው ሪፖርቱ፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለ ማስረጃ በቁጥጥር ስር ውለው በድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ እና ስቃይ እንደሚደርስባቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ መከልከላቸውን መግለጹን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሶርያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች የሚገኙበት ሁኔታ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ያሳሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል። በሕዝቦች መካከል ለሚነሱት ግጭቶች እና ጦርነቶች ተግባራዊ የሚሆን ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲገኝ ቅድስት መንበር አጥብቃ እንደምትፈልግ የገለጹት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ይህ ሊሆን የሚችለው በአግሮች መካከል ዲፕሎማሲን በማዳበር፣ ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብን የሚያሳትፍ የውይይት መድረክ በማመቻቸት እንደሆነ አስረድተዋል። ምንም ጊዜም ቢሆን ጦርነት ጦርነትን፣ አመጽ አመጽን እንደሚወልድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሶርያው ፕሬዚደንት ለአቶ በሽር አል አሳድ በላኩት መልዕክት መናገራቸውን  ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል። ለሶርያ ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሔን ለማምጣት በጄኔቫ ሲደረግ የቆየው ውይይት መቋረጡ ቅዱስነታቸውን እንዳሳሰባቸው የገለጹት ካርዲናል ፓሮሊን ቢሆንም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተስፋን በማድረግ የሶርያው ፕሬዚደንት አቶ በሽር አል አሳድ ለሕዝባቸው በጎን በማድረግ እንዲተባበሩ እና ተጨባጭ ተነሳሽነትን እንዲያሳዩ መማጸናቸውን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
23 July 2019, 16:26