ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለስሜን መቀዶኒያ ያስተላለፉት መልእክት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከሚያዝያ 27-29/2011 ዓ.ም ድረስ 29ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ቡልጋሪያ እና ሰሜን መቀዶኒያ በቅደም ተከተል እንደ ሚያመሩ መግለጻችን ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ቀደም እንደ ተለመደው ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማደርግ ወደ ሚሄዱባቸው አገራት አስቀድመው የቪዲዮ መልእክት እንደ ሚልኩ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም መሰረት የ29ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ መዳረሻ ለሆነችው ሰሜን መቀዶኒያ በሚያዝያ 26/2011 ዓ.ም በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት “ወደ ሰሜን መቀዶኒያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የግንኙነት እና የአንድነት ባሕል ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ዘር ለመዝራት ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዘገባ አቅራቢ መብራቱ ኃ-ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቡልጋሪያ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ካጠቃለሉ በኋላ ከባልካን አገሮች ውስጥ አንዷ የሆነችውን ሰሜን መቀዶኒያን በመጭው ማክሰኞ በሚያዝያ 29/2011 ዓ.ም እንደ ሚጎበኙ ለቅዱስነታቸው ከወጣው የጉዞ መርሃ ግብር ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ቅዱስነታቸው በዚሁ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ጨምረው እንደ ገለጹት “በሰሜን መቀዶኒያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት "በደስታና የፍቅር ስሜት” የሚከናወኑት ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደ ሆነም ጨምረው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት በሰሜን መቀዶኒያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአገሪቷ ውስጥ የግንኙነት እና የአንድነት ባሕል ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደ ሚረዳ ያላቸውን ተስፋ የገለጹ ሲሆን “እኔ ወደ እናንተ የምመጣው እናንተ መልካም አፈር መሆናችሁን በመረዳት በመካከላችሁ  ዘር ለመዝራት ነው፣ እናንተም ይህንን ዘር መቀበል እና ፍሬ ማፍራት እንደምትችሉ እርግጠኛ ነኝ” ማለታቸውም ተገልጹዋል።

ሰሜን መቀዶኒያ ልዩ የሆነ ውበት ያላት አገር እንደ ሆነች በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህም የሆነበት ምክንያት አገሪቷ የተለያየ ባህል፣ ጎሳ እና የሃይማኖት ተከታይ በሆኑ ሰዎች የተገነባች በመሆኗ የተነሳ ነው ብለዋል። “አብሮ መኖሮ ቀላል የሆነ ነገር እንዳልሆነ በሚገባ እንገነዘባለን” ያሉት ቅዱስነታቸው “ነገር ግን አብሮ ለመኖር እንችል ዘንድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፣ ምክንያቱም እጅግ ውብ የሆነ በጠጠር የሚሰራ የግድግዳ ስዕል ውበት የሚለካው ሰዕላዊ በሚጠቀምባቸው የተለያዩ ቀላማት ባላቸው ብዙ ጠጠሮች ምክንያት በመሆኑ የተነሳ ነው” ብለዋል።

እማሆይ ትሬዛ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዚህ በሰሜን መቀዶኒያ የሚያደርጉት 29ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በእዚያ አገር የሚገኘውን የካልካታዋን እማሆይ ትሬዛ ተወልደው ያደጉበትን ስኮፒዬ የተባለውን የትውልድ ሥፍራቸውን እንደ ሚጎበኙ ለጉዞዋቸው ከወጣው መረሃ ግብር ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ እንደ ገለጹት “በእግዚኣብሔር ጸጋ እርሳቸው በዓለም ውስጥ ብርቱ የክርስቶስ የበጎ ስራ ልዑክ በመሆን የድሃ ድሃ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ መጽናናትን እና ሰብዓዊ ክብራቸውን መልሰው እንዲጎናጸፉ አድርገዋል” ብለዋል። ቅዱስነታቸው በቪዲዮ ለሰሜን መቀዶኒያ ሕዝቦች ባስተላለፉት መልእክት ማጠቃለያ ላይ እንደ ገለጹት የሰሜን መቀዶኒያ ሕዝብ የእርሳቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሰላም ፍሬ ያፈራ ዘንድ በጸሎት መንፈስ ሆኖ አብሮዋቸው እንዲያከናውን ጥሪ አቅርበው “እግዚኣብሔር ይባርካችሁ” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በስድስት አመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ከጣሊያን ውጭ በቅርቡ በሞሮኮ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጨምሮ 29 ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በእነዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ከሚገኙት ከኬኒያ፣ ከሁጋንዳ እና ከመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ አንስቶ በኩባ፣ በአሜሪካ፣ በላቲን አመሪካ በምስራቅ አውሮፓ እና በኤሽያ አህጉር በመጓዝ የሰላም እና የአንድነት መልእክት ማስተላለፋቸው የሚታወስ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅርቡ ከመጋቢት 21-22/2011 ዓ.ም 28ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በሞሮኮ ማደርጋቸው ይታወሳል።

900 የካቶሊክ ምዕመናን ብቻ የሚገኙባትን እና አብዛኛው ሕዝብ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍል የሚኖሩባትን አዛረበጃንን ጨምሮ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ሕዝቦች የሚኖሩባቸውን ባንግላዲሽ እና ማያን ማር (የቀድሞ ስሟ በርማ) ድረስ በመሄድ የሰላም እና የአንድነት መልእክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅርቡ በመጋቢት ወር በሞሮኮ 28ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን ቀድም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን የዚህ የቅዱስነታቸው በሞሮኮ ያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሞሮኮ ያደረጉት ሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲሆን ከዚህ ቀደም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለኛ እንደ የጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በነሐሴ 19/1985 ዓ.ም በዚያው በሞሮኮ በሚገኘው የካዛ ብላንካ እስቴዲዬም ለተገኙ በርካታ የክርስታና እና የእስልምና እምነት ተከታይ ወጣቶች ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።

04 May 2019, 17:18