ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለግንቦት ወር ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየወሩ ለወሩ የሚሆን የጸሎት ሐሳብ በቪዲዮ መልእክት ይፋ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ለዚህ ከሁለት ቀናት በፊት ለተጀመረው የጎርጎሮሳዊያኑ የግንቦት ወር ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ በአፍሪካ አህጉር የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን በመላው የአፍሪካ አህጉር ለሚኖሩ ሕዝቦች የተስፋ እና የአንድነት ዘር መዝራት ትችል ዘንድ በአፍሪካ አህጉር ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ጸሎት የሚደረግበት ወር እንዲሆን ቅዱስነታቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ይፋ አድርገዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከሁለት ቀን በፊት በተጀመረው የግንቦት ወር የጸሎት ሐሳብ በቪዲዮ ይፋ ባደርጉበት ወቅት እንደ ገለጹት “በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙ ካህናት፣ ገድማዊያን ገዳማዊያት፣ ደናግላን እና ምዕመናን እያከናወኑት ስለሚገኙት ሐዋርያዊ አገልግሎት” ከፍተኛ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን በተለይም ደግሞ በሕዝቦች መካከል ውይይት እንዲካሄድ እና በአፍሪካ አህጉር ውስጥ በሚገኙ ማኅበርሰቦች ውስጥ እርቅ እንዲወርድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እያደርገች ስለሚገኘው አስተዋጾ ቅዱሰንታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

የአፍሪካን አህጉር በተስፋ መመልከት ይገባል

ቅዱስነታቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ጨምረው እንደ ገለጹት “በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ ካቶሊክ እምነት ተከታዮች በአህጉሩን በተስፋ እንዲመለከቱ ጥሪ አቅርበው በተጨማሪም መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሊደርሱባቸው ባልቻሉባቸው ቦታዎች እና አከባቢዎች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እጅግ በጣም ርቀው ወደሚገኙ የገጠራማ ስፋራዎች ድረስ በመሄድ እያበረከተች የምትገኘውን ማኅበራዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎት እንደ ሚያደንቁ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል።

በአፍሪካ የሚገኙ የካቶሊክ እምነት ቁጥር 228 ሚልዮን ደርሱዋል

የቅድስት መንበር እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2018 ዓ.ም ያፋ ባደረገችው መረጃ መሰረት ከአጠቃላይ የአፍሪካ ሕዝብ ቁጥር ውስጥ 17.6% የሆነው ሕዝብ የካቶሊክ እምነት ተከታይ መሆኑን ያፋ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን በዚህም መሰረት በአፍሪካ አህጉር የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥንካሬዋ እየጨመረ እና የምዕመናን ብዛት በአሰጋራሚ ፍጥነት እያደገ እንደ ሆነ የተገለጸ ሲሆን ለዚህም በዋቢነት የሚቀርበው ማስረጃ እ.አ.አ በ2010 ዓ.ም ከአጠቃላይ የአፍሪካ ሕዝብ ቁጥር ውስጥ 185 ሚልዮን የሚሆኑ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ መሆናቸው መገለጹ የሚታወስ ሲሆን ይህ ቁጥር እ.አ.አ በ2016 ዓ.ም አስገራሚ በሆነ መልኩ ጭማሪ በማሳየት 228 ሚልዮን መድረሱን ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ይህም በመቶኛ ሲሰላ 23% ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጹዋል። በዚህ ዘገባ መሰረት በአፍሪካ አህጉር ከፍተኛ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች የሚገኙባት ቀዳሚዋ አገር የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ስትሆን በዚህ አገር ብቻ 44 ሚልዮን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች እንደ ሚገኙ የተገለጸ ሲሆን ከኮንጎ ዲማክራቲክ ሪፖብሊክ በመቀጠል ከፍተኛ የካቶሊክ እመንት ተከታይ ያለባት አገር ናይጄሪያ መሆኗን ተያይዞ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በናይጄሪያ የሚኖሩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች በቁጥር 28 ሚልዮን መሆኑም ተገልጹዋል።

በሁጋንዳ፣ ታንዛኒያ ኣና በኬኒያ የካቶሊክ እምነት ተከታይ በቁጥር እያደገ ይገኛል

በሁጋንዳ፣ በታንዛኒያ እና በኬንያ የሚኖሩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑም የተገለጸ ሲሆን በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በንጽጽር ሲታይ ደግሞ በአፍሪካ አህጉር የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያ እምነት ተከታዮች 3% ቁጥራቸው ከፍ በማለቱ የተነሳ በአህጉሪቷ የእየተከናወነ የሚገኘው ሐዋርያዊ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እና ይህንን ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚያከናውኑ ቄሳውስት፣ ደናግላን፣ ምዕመናን እና የሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎት የሚያከናውኑ ሰዎች እና ግለሰቦች ተመጣጣኝ የሆነ ቁጥር ይኖራቸው ዘንድ የሚያሳስብ ክስተት እንደ ሆነም ተገልጹዋል። በአሁኑ ወቅት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ከሚገኝባቸው 15 አገራት ውስጥ አራቱ የሚገኙት በአፍሪካ አህጉር ሲሆን እነዚህም ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ፣ ናይጄሪያ፣ ሁጋንዳ እና አንጎላ በቅደም ተከተል ይገኙባቸዋል።

 

02 May 2019, 17:18