ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ቤተክርትያን እንድትንቀሳቀስና ከዓለማዊ መንፈስ ነጻ እንድትወጣ የሚረዳት መንፈስ ቅዱስ ነው”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በትላንትናው እለት ማለትም በግንቦት 18/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ከዮሐንስ 14፡23-29 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱ እንመጣለን፤ ከእርሱም ጋር እንኖራለን። የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም” በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ትኩረቱን ባደርገው አስተንትኖ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ቤተክርትያን እንድትንቀሳቀስ እና ከዓለማዊ መንፈስ ነጻ እንድትወጣ የሚረዳት መንፈስ ቅዱስ ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 18/2011 ዓ.ም ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዚህ የዛሬው የፋሲካ 6ኛው ሳምንት ቅዱስ ወንጌል (ዮሐ 14፡23-29) ኢየሱስ በመጨረሻው እራት ላይ ለሐዋርያቶቹ ያደርገውን የመጨረሻውን ንግግር ያቀርብልናል። እርሱም ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራ በመናገር “አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል” (ዩሐ 14፡26) በማለት መንፈስ ቅዱሱን እንደ ሚልክላቸው ቃል ይገባላቸዋል። በመስቀል ላይ የሚሰቀልበት ጊዜ እየተቃረበ በሚመጣበት ወቅት ኢየሱስ ሐዋርያቱን ብቻቸውን እንደ ማይተዋቸው ያረጋግጥላቸዋል፣ ከእነርሱ ጋር ሁል ጊዜ በመሆን ቅዱስ ወንጌልን በመላው ዓለም ለማስራጨት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ይወጡ ዘንድ የሚረዳቸውም መንፈስ ቅዱስ ጴራቅሊጦስ እንደ ሚልክላቸው ያናገራል። “ጴራቅሊጦስ” የሚለው ቃል ሥር መሰርቱ የግሪክ ቃል ሲሆን ከአጠገባችን ሆኖ ድጋፍ የሚሰጥ እና የምያጽናና የሚለው ትርጓሜ ያሰማል። ኢየሱስ ወደ አብ ተመልሶ ይሄዳል ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ተግባር አማካኝነት ደቀመዛሙርቱን ማስተማር እና ማንቀሳቀስ ቀጥሉዋል።

ኢየሱስ ሊሰጥን ቃል የገባው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የሚሰጠን ተልዕኮ ምንድነው? “መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል” በማለት ኢየሱስ ራሱ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሰጥቱዋል። ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ወቅት ሐዋርያቱ ሊተገብሩት የሚገባቸውን ነገሮች ሁሉ አስተላልፎ ሰጥቱዋችኋል: መለኮታዊውን ራዕይ ምልአት እዲኖረው አድርጉዋል፣ ይህም ማለት ደግሞ አብ ለሰው ልጆች ሊገልጸው የፈለገውን ነገር ሁል የአብ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ሰው በመሆን ገልጾታል። የመንፈስ ቅዱስ ተግባር ሰዎችን እንድናስታውስ ያፈርጋል፣ ያም ማለት ደግሞ የኢየሱስ ትምህርቶች በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበሩ እና ተጨባጭ በሆነ መልኩ በሕይወታችን እንዲገለጹ ማስታወስ ነው። እናም ይሄም የቤተክርስቲያኑ ተልዕኮ ነው፣ እሱም በተወሰኑ የህይወት ዘይቤዎች ተግባራዊ የሚደረግ ማለት ነው፣ በጌታ ማመን እና ቃሉን መጠበቅ ማለት ነው፣ ኢየሱስን ሕያው በሆነ መልኩ እና ከሙታን የተነሳውን ጌታ በእኛ መካከል መኖሩን ለሚገልጸው ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ በትህትና መገዛት ማለት ነው፣ እርሱ የሚሰጠንን ሰላም በደስታ መቀበል እና ይህንን ሰላም ራሳችንን ክፍት በማድረግ እና ከሌሎች ጋር በመካፈል ስለእርሱ መመስከር ማለት ነው።

ይህንን ሁሉ ለማሟላት ቤተክርስቲያን እንዲሁ ሳትንቀሳቀስ ቆማ መቅረት አትችልም፣ ነገር ግን በእያንዳንዱ ምስጢረ ጥምቀት በተቀበለ ሰው ንቁ ተሳትፎ ውስጥ አብራ በመንቀሳቀስ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመነሳሳት እና ሁሉም ነገር አዲስ በሚያደርገው በመንፈስ ቅዱስ ብርሀንና ብርታት ተደግፋ መንቀሳቀሱዋን ትቀጥላለች። ብዙውን ጊዜ በእምነት ጉዞ ላይ ሸክም ከሚሆኑብን እና የጌታን ቃል በትክክል እንዳናዳምጥ ከሚከለክሉን ከእኛ አመለካከት፣ ከእኛ ስልቶች፣ አላማዎቻችን፣ እራሳችንን በማላቀቅ ከዓለማዊ አስተሳሰቦች ራሳችንን ነጻ ማውጣት ማለት ነው። ትክክለኛውን የሚያምረውን እና የሚያበራውን የኢየሱስን ፊት መላበስ እስክንችል ድረስ የእግዚኣብሔርን ፊት ማንጸባረቅ እስክንችል ድረስ በዚህ መልኩ የእግዚኣብሔር መንፈስ እኛን እና ቤተክርስትያንን ይመራል።

መንፈስ ቅዱስ ለሚሰጠን ጸጋ ልባችንን ክፍት ማድረግ እንችል ዘንድ ጌታ ዛሬ ይጋብዘናል። እርሱም እለት ተእለት የቅዱስ ወንጌል አመክንዮ በሚገባ መረዳት እንችል ዘንድ ያስተምረናል፣ ሌሎችን በደስታ  መቀበል የሚያስችለንን የፍቅር አመክንዮ፣ ሁሉምን ነገር በሚገባ መረዳት እንችል ዘንድ ያስተምረናል፣ “ጌታ የተናግራቸውን ነገሮች ሁሉ በማስታወስ በተግባር ላይ እንድናውለው ያስተምረናል። በዚህ በያዝነው በግንቦት ወር ለየት ባለ መልኩ እያከበርናት የምንገኘው ሰማያዊቷ እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስትያንን እና መላውን የሰው ልጆች እንድትጠብቅ እንጸልይ። በትህትና በተሞላ እምነት እና ብርታት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተባብራ ለመሥራት ሙሉ ፈቃደኝነቷን በመግለጽ የእግዚኣብሔር ልጅ ማደሪያ ለመሆን የበቃችሁ እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እኛንም ቢሆን መንፈስ ቅዱስ እንዲያስተምረን እና እንዲመራን እንፈቅድለት ዘንድ እንድትረዳን የእግዚኣብሔርን ቃል ተቀብለን በሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግ እንድንመሰክ እንድትረዳን አማላጅነቷን መማጸን ያስፈልጋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 May 2019, 18:09