ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ሥራ በማጣታቸው የተነሳ እየተንገላቱ ለሚገኙ ሰዎች እንጸልይላቸው” አሉ

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማኅበረስብ ክፍሎች ዘንድ የግንቦት ወር በትላንትናው እለት መጀመሩ ይታወሳል። የዚህ የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ ግንቦት 1/2019 ዓ.ም በዓለማቀፍ ደረጃ የሰራተኞች ቀን ተከብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን በእለቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ሳምንታዊውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ካጠናቀቁ በኋላ በእለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረውን የሰራተኞች ቀን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት "በሚያሳዝን ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥራ አጥተው እየተቸገሩ ለሚገኙ ሰዎች እንጸልይላቸው" ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በእለቱ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የማርያም ወር ተብሎ በሚታወቀው የግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የተከበረውን የቅዱስ ዮሴፍ ዓመታዊ ክብረ በዓል ከግምት ባስገባ መልኩ ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት ሥራ የሰው ልጆች ሕልውና መገለጫ እና የሰው ልጆች ሰብዓዊ ክብር መሰረታዊ የሆነ ነገር እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

በእለቱ “የናዝሬቱ ትሑት ሠራተኛ” በመባል የሚታወቀው የቅዱስ ዮሴፍ አመታዊ በዓል እየተከበረ መሆኑን በድጋሚ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው የእርሱ አብነት ወደ ክርስቶስ ሊመራን እንደ ሚችል ገልጸው "ለዚህ ዓለም መልካም ነገሮችን የሚያደርጉትን ሰዎች " ይጠብቅ ዘንድ እና ከሥራ ገበታዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሱትን ሰዎች ወይም ደግሞ የሥራ እድል ለማግኘት ላልቻሉ ሰዎች ሥራ ያገኙ ዘንድ እንዲያማልድላቸው አማላጅነቱን መማጸን ያስፈልጋል ብለዋል።

ለወጣቱ ትውልድ የሥራ እድል መፍጠር ተገቢ ነው

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው እጅግ በጣም የሚያሳዝን ክስተት እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ቅዱስነታቸው በመሆኑም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተሰጣቸውን ማኅበራዊ ኃላፊነት በሚገባ በመወጣት ለወጣቱ ትውልድ ሥራ መፈጠር የሚያስችሉ ተገባራትን እንዲያከናውኑ እንደ ሚያበረታቱዋቸው ገልጸው ይህም ማለት “ለሰው ልጆች መሰረታዊ ሰብዓዊ መብት መቆርቆር ማለት ነው፣ በዚህ ረገድ ወጣቶች በፍጹም ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም፣ ቅዱስ ዮሴፍም ቢሆን በሕይወቱ ውስጥ አስቸጋሪ የሆኑ ጊዜያትን አሳልፉዋል፣ ነገር ግን በእግዚኣብሔር ላይ መተማመኑን በፍጹም አቋርጦ አያውቅም በዚህም የተነሳ ጭግሮቹን መወጣት ችሉዋል፣ እናንተ በተለይ ወጣቶች እግዚኣብሔር ብቻችሁን እንደ ማይተዋችሁ እርግጠኞች ሁኑ። በተለይም ደግሞ እናንተ ወጣቶች ዕለታዊ የሆኑ ግዴታዎቻችሁን፣ ትምህርታችሁን፣ ሥራችሁን፣ ከጓደኞቻችሁ ጋር ያላችሁን ግንኙነት፣ ሌሎችን ለመርዳት መነሳሳታችሁን የመሳሰሉትን ግዴታዎቻችሁን በተግባር ላይ አውሉት፣ የአሁኑ ግዴታችሁ የወደፊቱን ማንነታችሁን ይወስናልና በርትታችሁ አሁን ወርቃማ በሆነው በሕይወታችሁ የወጣትነት ዘመን ወጤታማ እንድትሆኑ የሚያደርጉዋችሁን ተግባሮች ከአሁኑ ማከናወን ይኖርባችኋል። የጋብቻ ቃል ኪዳን ለመፈጸም አትፍሩ፣ መጪውን ጊዜ በስጋት አትመልከቱ፣ ተስፋችሁን ሕያው አድርጉ፣ ሁልጊዜም ቢሆን ከላይ የሚመጣ ብርሃን ተመልከቱ” ብለዋል።

በባርነት ውስጥ የሚከቱዋችሁን ሥራ አትስሩ

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ውስጥ የሰው ልጆችን በባርነት ቀንበር ሥር የሚያስገቡ የሥራ ዘርፎች እየተበራከቱ እንደ ሚገኙ የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ እንደ ተናገሩት “በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለማችን አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆነው አስቸጋሪ በሆነ ባርነት በሚመስል መልኩ ሥራ በማከናወን ላይ የሚገኙ ሰዎች ብዙ እንደ ሆኑ ገልጸው ሥራ ለሰው ልጅ አገልግሎት መዋል ሲገባው በተቃራኒው ሰው የሥራ አገልጋይ በመሆን ላይ ኣንደ ሚገኝ ገልጸው በዚህ ረገድ በመላው ዓለም ውስጥ የሚገኘውን አስገዳጅ ሥራ በማስወገድ የሰው ልጆችን ሰብዓዊ መብት ያረጋገጠ እና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የሥራ መስክ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

02 May 2019, 17:23